ለብዙዎች ተስፋ የፈነጠቀው የበጎ አድራጎት ሥራ

ወይዘሮ መስከረም ነጋሲ ትባላለች። በቶራ የእናቶችና ህጻናት በጎ አድራጎት ማህበር ድጋፍ ወደ ሥራ ከገቡ እናቶች አንዷ ናት። ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ስትሆን፤ ሦስተኛ ልጇን ነፍሰ ጡር እያለች ባለቤቷ በሥራ ቦታ ባጋጠመው ችግር ለእስር በመዳረጉ ለችግር ተጋልጣ እንደነበር ታስታውሳለች።

በወቅቱም የቤተሰቡ ኑሮ በባለቤቷ ገቢ ላይ የተመሠረተ እንደነበር ጠቅሳ፤ ለመውለድ ሁለት ወራት ሲቀረኝ ባሌ መታሠሩ ሕይወቴን አክብዶት ነበር ትላለች። ችግሯን የተረዱት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ከቶራ የእናቶችና ህጻናትና በጎ አድራጎት ማህበር ጋር እንድትገናኝ እንዳደረጓት ታስታውሳች።

ማህበሩን ከተቀላቀለች በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል የአስቤዛና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ስታገኝ መቆየቷን አስታውሳ፤ በአሁኑ ጊዜም አስፈላጊ ግብዓቶች ተሟልተውላት የባልትና ውጤቶችን መሥራት ጀምራለች። እሷ ሥራ ላይ በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ ልጇ በማህበሩ የማቆያ አገልግሎት ታገኛለች።

ያገኘችውን እድል በመጠቀም ሥራዋን አስፍታ ነገን ይበልጥ ብሩህ ለማድረግ እንደምትፈልግ ጠቁማ፤ ያለባት መሸጫ ቦታ ችግር ተግዳሮት እንደሆነባትና የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጣት ጠይቃለች ።

የቶራ የእናቶችና ህጻናት በጎ አድራጎት ማህበር ሥራ አስከያጅ ወይዘሮ ገነት ገብረማርያም እንደሚሉት ፤ ማህበሩ ከተቋቋመበት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወላጅ የሌላቸው ህፃናትን በማሰባሰብ ድጋፍ በማድረግ አምስት ዓመታት ዘልቋል። ሥራውን በሰባት ህጻናት የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም በተለያዩ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ 36 ህጻናትን ከመንግሥት ተረክቦ በማሳደግ ላይ ነው ይላሉ።

ለሁለት ዓመታት ደግሞ ለችግር የተጋለጡ 30 እናቶችን በየወሩ አስቤዛና የጽዳት እቃዎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው፤ ለ58 ልጆቻቸውም የትምህርት ቁሳቁስ በመስጠትና ዕድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሱ ሕፃናትን በነፃ የሕፃናት ማቆያ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

እነዚህ እናቶች ከተረጂነት ወጥተው በራሳቸው ገቢ እንዲተዳደሩ ለማስቻል የተለያዩ የሙያ እና የክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው፤ ገንዘብ፣ለሥራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ድጋፍ ራሳቸው በመረጡት በመለስተኛ የንግድ ሥራ ላይ እንዲሠማሩ ማድረጉን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ጨምረው ገልጸዋል። በዚህም በእንጀራ መጋገር፣ በባልትና፤ በዶሮ ርባታና በሌሎችም የሙያ ዘርፎች ተሠማርተው ውጤት ማምጣት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

ቶራ የእናቶችና ህጻናት የበጎ አድራጎት ድርጅት ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ማስቆጠሩና አዲስ መሆኑ በሥራው ላይ ተግዳሮት እንደሆነበት አመላክተው፤ በቀጣይነት ሥራውን አስፍቶ ለመሥራት እና ቋሚ ገቢ ማግኘት የሚያስችለውን ሥራ ለመሥራት አቅዷል። መልካም ዓላማውን የሚደግፉ ኢትዮጵያውያም ባላቸው አቅም ሁሉ ከማህበሩ ጎን ሆነው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የህጻናት ጥበቃ ድጋፍና ክብካቤ ባለሙያ እየሩሳሌም ጫኔ በበኩላቸው፤ ቢሮው በእናቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር በቅርበት ይሠራል ይላሉ። በከተማዋ በየጊዜው ተጥለው የሚገኙ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንድ እናት ካልተቸገረች በስተቀር ልጇን ትጥላለች ተብሎ አይታሰብም። ማህበሩ የሚሠራው የበጎ አድራጎት ሥራም ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናት በተሻለ መልኩ እንዲያድጉ እድል ይፈጥራል። የተሻለ የትምህርት እድልና እንክብካቤ እንዲያገኙም ያስችላል ብለዋል።

ህጻናት ከመጣላቸው በፊት የእናቶችን አቅም የማጎልበት ሥራ እንደሚያከናውን የገለጹት ባለሙያዋ፤ ለዚህም መንግሥታዊ ካልሆኑና መንግሥታዊ ከሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ሥራዎች እንደሚያከናውኑ አመላክተዋል።

ቶራ የእናቶችና ህጻናት በጎ አድራጎት ማህበር በቅርቡ የተመሠረተበትን አምስተኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ያከበረ ሲሆን፣ በቀጣይ ሥራውን አስፍቶ ለመሥራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተመላክቷል።

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You