ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት የሚያደርገውን ሽግግር በእቅዱ መሠረት ያጠናቅቃል

አዲስ አበባ፡አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝነት የሚያደርገው ሽግግር በእቅዱ መሠረት በተቀመጠው ጊዜ ገደብ የሚጠናቀቅ መሆኑን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲውን የራስ ገዝ ዝግጅት በተመለከተ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት የሚያደርገው ሽግግር በእቅዱ መሠረት እያከናወነ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲወጣ በተወሰነው መሠረት የዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝነት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ 1294/2016 መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ 537/2016 አግባብ (መልሶ) ተደራጅቷል ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ፤ ወደ ራስ ገዝነት የሚደረገውን ሽግግር የሚመራ አዲስ የአመራር ቡድን ከመስከረም 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

አመራሩም ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ሥራ ራስ ገዝነት እሳቤ ላለፉት 18 ወራት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶና በሥራ አመራር ቦርድ ፀድቆ እየተተገበረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በስትራቴጂክ እቅዱ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት የሚያደርገው በአካዳሚክ ልህቀት፣ በምርምርና ጥናት ተገቢነት፣ የላቀ የጤና አገልግሎት፣ የማህበረሰብ እና ኢንዱስትሪ ጉድኝት ለችግር ፈቺነት፣ ውጤታማ የተቋም አስተዳደር እና ምቹ፣ ፅዱና አረንጓዴ ስማርት የትምህርትና የሥራ ከባቢ መፍጠር ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

ስትራቴጂክ እቅዱን በላቀ ውጤታማነት ለመተግ በርም በሥራ ላይ ያሉትንና አዳዲስ ፖሊ ሲዎችን፣ ሕግ ማዕቀፎችን፣ መመሪያዎችን የማርቀቅና የማፅደቅ ሥራ የተሠራና በመሠራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል (ዶ/ር) ገለጻ፤ ቀደም ሲል የነበሩትን ከ500 በላይ የቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች በመገምገም ወደ 416 ተጠቃለው በሰባት ኮሌጆችና በአንድ የሕግ ትምህርት ቤት ሥር እንዲሆኑ ተዋቅሯል። በተመሳሳይ የምርምር ሥራዎች አፈፃፀምና የምርምር ኢንስቲትዩቶች አሠራር ተገምግሞ በሰባት የምርምር ኢንስቲትዩቶች ተደራጅቷል።በዚሁ መነሻ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውስጥ መዋቅሩ በጥናት ተደግፎ ተከልሷል።ይህም ከጥር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን ኢንትሪም ኃላፊዎች ተመድበው በመሥራት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ለተልዕኮ ሥራዎች አስፈላጊ የሆነ የሰው ኃይል ብዛት ጥናት፣ የሥራ ምዘናና የደረጃ አሰጣጥ ጥናት እና የመክፈል አቅምን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥናት መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፤ በቅርቡ በሚመለከታቸው አካላት ውይይት ተደርጎበትና ዳብሮ በሥራ አመራር ቦርዱ ሲጸድቁ የሚተገበሩ ይሆናል ብለዋል።

ባለፉት 18 ወራትም ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት የሚያደርገውን ሽግግር ያግዛሉ ተብለው የተለዩ ተግባራትን አጠናክሮ የማስቀጠል ሥራም መሠራቱን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝነት ሽግግሩን ለማገዝ በተለያዩ አጀንዳዎች አካዳሚክ ኮንፈረንሶችና ፓናሎች ተካሂደዋል። ከሀገር ውስጥና የውጭ አጋሮች ጋር የትብብር ፊርማዎች ተፈርመዋል ነው ያሉት።

በአዋጁና በደንቡ ውስጥ በተደነገገው መሠረት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ያከማቻቸውን የላቀ ልምድና እውቀት ተጠቅሞ የሀገራችን የመፍትሔ ክምችት አንድ አቅም እንዲሆን ራስ ገዝነቱ ልዩ እድል እንደሚሰጠውም ተጠቁሟል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You