የአርብቶ አደር አካባቢ እናቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤና መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፡የእናቶችና ህጻናት ጤናን ለመጠበቅ በተንቀሳቃሽ ክሊኒክ ህክምና አገልግሎት እና አልሚ ምግብ አቅርቦት የሚደረግበት መርሃ ግብር በሱማሌ፣ በአፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

መርሃ ግብሩ ድጋፍ የተደረገው በጌትስ ፋውንዴሽን እና በተባበሩት መንግሥታት የፆታና ሥነ ተዋልዶ ጤና ኤጀንሲ (ዩኤን ኤፍፒኤ) ሲሆን ለሶስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ተንቀሳቃሽ የክሊኒክ እና የአልሚ ምግብ አገልግሎቱ በተመረጡ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን ተደራሽነት በማሻሻል የሚሞቱ እናቶችና ህፃናትን ቁጥር ለመቀነስ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

ለሙከራ ትግበራ የተመረጠባቸው አካባቢዎች በተለይ መሠረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው እና ትራንፖርት በማይገባባቸው፣ የጤና አገልግሎት ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ላይ ፈጣን አገልግሎት ለማዳረስ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፤ ተደራሽ ላልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል ፍትሃዊነት እንዲሰፍን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ በወሊድ ምክንያት የሚከሰትን የእናቶችና የሕጻናት ሞትን በመቀነስ ሂደት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ነው ያመለከቱት፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀልጣፋ፣ ምቹ፣ ጥራት ያለው እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁንም በዘርፉ በርካታ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡

ትግበራው በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር በመቅረፍ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማዳረስ የሚደረገውን ሥራ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚደግፍም ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ ህክምና እንዲያገኙ በማገዝ የእናቶችን እና የህጻናት ጤናን ለመጠበቅ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት፡፡

የጤና አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎች ላይ ለማዳረስ፣ ሴቶች እንዲበቁ፣ ልጆቻቸውም ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ የሙከራ ትግበራው ትኩረት አድርጎ የተጀመረው አርብቶ አደር በሆኑት አፋር፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በተመረጡ ወረዳዎች ላይ ይሁን እንጂ በቀጣይ ተግባሩ እንዲሰፋ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ እናቶች በወቅቱ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ፣ ጤናማ ማህበረሰብ እንዲፈጠርና አስፈላጊ ህክምና በወቅቱ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ትራንስፖርት ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት በርካታ እናቶች ለተለያዩ ችግሮች እንደሚጋለጡ አመልክተው፤ በተለይ ወላጆች ቶሎ ወደ ህክምና ተቋማት ባለመድረሳቸው ልጆቻቸውን እንዲያጡና ለጤና ችግር እንዲጋለጡ ምክንያት እንደነበርም ነው የተናገሩት፡፡

ትግበራው ጤናማ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ከማገዙም ባሻገር፤ ሴቶች ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማስፈን እንደሚያስችላቸው፣ በፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነትም ትልቅ ተጽእኖ እንደሚኖረውም አመልክተዋል፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You