
ቢሾፍቱ፡– የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉባዔ በፍትህ ሥርዓቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ሰባተኛው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉባዔ ትናንት በቢሾፍቱ ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ ጉባዔው በፍትህ ሥርዓት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሃሳብ የሚፈልቅበት፤ የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶችን ተሳትፎና ትስስርን የሚያጠናክር ነው።
ጉባዔው የፍርድ ቤቶችን አሠራር የሚያዘምኑ መመሪያዎች፤ ደንቦችና ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እና ሕግ ለማውጣትና ለማሻሻል የሚጠቅሙ ሃሳቦች የሚፈልቁበት መድረክ መሆኑን ጠቁመው፣ የፌዴራልና የክልል የዳኝነት አካላት በፍትህ ሥርዓቱ ያላቸውን ሚና ለመለየት የሚያስችል እውቀትና ልምድ ይገኝበታል ነው ብለዋል።
በመድረኩ የሚነሱ የመወያያ ሃሳቦች እና በተሳታፊዎች የሚሰጡ አስተያየቶች እጅግ ጠቃሚ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የፍርድ ቤቶችን አሠራርን በማሻሻል ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመዘርጋት እንዲሁም ያለውን ውስን ሀብት፣ እውቀትና ጉልበት በአግባቡ ለመጠቀም የሚረዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጉባዔው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2017 ዕውቅና ተሰጥቶት የሚካሔድ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በፍትሕ አስተዳደር ረገድ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሔ መስጠት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አሠራር ሊያሻሽሉ የሚችሉ መመሪያዎችንና ውሳኔዎችን ማሳለፍ፣ የሕግ ማውጣት ወይም ማሻሻል ሃሳብ ማመንጨት፣ የዳኝነት ሥራን ለማቀላጠፍ የሚረዱ ተግባራትን ማከናወን ዋና ዋና ኃላፊነቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ጉባዔው በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት አንጻር እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት በቂ አለመሆናቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት የጉባዔውን ቀጣይነት በሚያረጋግጥ መንገድ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በጉባዔው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የፌዴራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተወካይ ዳኞች፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችን ተሳትፈዋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም