
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከኖሩበት አካባቢ ወደሌላ ስፍራ ይንቀሳቀሳሉ። በተለይም የልማት ተነሺዎች በዘመቻ ከአንድ አካባቢ ወደሌላ የመኖሪያ መንደር ይዘዋወራሉ። ቤተሰቦቻቸው እና እቃቸውን ወደስፍራው ከመውሰዳቸው በፊትም የሚገቡበትን አዲስ ቤት እንደየ አቅማቸው ያድሳሉ ወይም ያስተካክላሉ።
በተመሳሳይ እንዲሁ ነጋዴዎች ለንግድ የሚሆኑ ጅምላ ንብረቶቻቸውን የሚከማቹባቸው መጋዘኖች ስለሚኖሯቸው በየጊዜው የጫኝ እና አውራጅ ግልጋሎትን ይፈልጋሉ። በዚህ ጊዜ አዲስ ሊገቡበት ያሰቡትን ቤት ለማስዋብም ሆነ ለመኖሪያ ምቹ ለማድረግ የግንባታ ግብዓቶችን በስፍራው ሲያደርሱ በአካባቢው የሚገኙ የጎበዝ አለቆች ንብረታቸውን ማውረድ እንደማይችሉ ይነግሯቸዋል።
ለዚህም ምክንያቱ ‹‹እኛ በጫኝ እና አውራጅ አደረጃጀት ተደራጅተናል። ከኛ ውጭ ይሄንን እቃ ወደ ቤቱ የሚያስገባ የለም›› የሚል ነው። እንዲህ የሚሉትን የጎበዝ አለቆች መደራደር ከባድ ነው። የሚጠሩት ዋጋ እና የሚያነሱት አምባጓሮ በርካቶችን አስመርሯል። ሰው በገዛ ንብረቱ ላይ የመወሰን መብት እንደሌለው እንዲሰማውም እያደረገ ነው።
ይህንን የሕዝብ እሮሮ የተረዳው መንግሥት ከዚህ ቀደም የነበሩትን የጫኝ እና አውራጅ ማኅበራት አፍርሶ በአዲስ አሠራር እና በአዲስ መንገድ አዋቅሯል። ሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመቀነስም አዲስ ሕግ አውጥቶ ወደ ሥራ አስገብቷል።
የጫኝና አውራጅ ማኅበራት ሕጋዊነት አገልግሎት አሰጣጥ እና የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የወጣው መመሪያም የጫኝና አውራጅ ማኅበራት ለተቋቋሙለት ዓላማ ብቻ በሕግና በሥርዓት እንዲሠሩ፤ የሌሎች አካላት መጠቀሚያ በመሆን የፀጥታ ስጋት እንዳይሆኑ ለማድረግ የወጣ ነው። በተጨማሪም ማኅበራቱ ያሉባቸው የዕውቀትና የአመለካከት ክፍተቶች ለማረምና ለማስተካከል ክትትልና ቁጥጥር ማድረግንም ዓላማ ያደረገ ነው።
የመመሪያው በጫኝና አውራጅ የሚደራጁ ግለሰቦች በጥሩ ሥነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ፤ የወንጀል ድርጊቶች የፀጥታ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንዲቀርፉ፤ የነዋሪው በንብረቱ ላይ የመወሰን መብቱን እንዲያከብሩለት እና የሕግ የበላይነትንና ማስከበር መርሑ ያደረገ ነው።
መመሪያውም የክፍያ ሥርዓት በተመለከተ የተዘጋጀ የዋጋ ተመን ዝርዝር የተካተተበት በመሆኑ አገልግሎት ፈላጊዎች ከዋጋ ተመኑ በላይ ሲጠየቁ አቅራቢያቸው ላለ የፀጥታ አካል ወይም ለቢሮው ማሳወቅ ይችላሉ። ይህ መመሪያ ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ መድረኮች ለማኅበራቱ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚደክሳ ከበደ የጫኝ እና አውራጅ ማኅበራት የአገልግሎት አሠጣጥ መመሪያው መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ መሻሻሎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ማኅበራቱ በአዲስ መልክ ከተደራጁ ወዲህ በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን አብራርተዋል።
ምክትል የቢሮው ኃላፊው የጫኝ እና አውራጅ ማኅበራት አገልግሎት ካሁን ቀደም የነበረው ሕዝብን ከማማረር ወደ ሕዝብ አገልጋይነት እየተቀየረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን የሚያመላክት የኢንስፔክሽን ውጤት እንዳለም ገልጸዋል።
በአንዳንድ ማኅበራት ላይ አሁንም መስተካከል ያለባቸው አሠራሮች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በሱፐርቪዥን ወቅት ከታዩ መልካም አፈፃፀሞች መካከል ሕግ፣ መመሪያና ደንብን ተከትለው ተቋም መሥርተው እየሠሩ ያሉ ማኅበራት መኖራቸው፣ ከራሳቸው አልፈው ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ ማኅበራት መኖራቸው ትልቁ የመመሪያው ስኬት መሆኑንም አስታውቀዋል።
በማኅበራቱ ከታዩ የአፈፃፀም ክፍተቶች መካከል ራሳቸው መሥራት ሲገባቸው ቀጥረው የሚያሠሩ መገኘታቸው፣ በመመሪያው ላይ በተቀመጠው የዋጋ ተመን መሠረት የማይሠሩ መኖራቸው፣ በመመሪያው የተቀመጠውን ክልከላ ጥሰው የተገኙ መኖራቸውንም አሳውቀዋል።
ኅብረተሰቡም መብቱን እንዲጠይቅ ግዴታውን እንዲያከብር፤ ከመመሪያው ውጭ የሆነ አካሄድ የሚሄዱ ማኅበራት እና ግለሰቦች ሲያጋጥሙት ለቢሮው ጥቆማ እንዲያደርስ ጥሪ አቅርበዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም