ትዳር ተፋቅሮና ተሳስቦ ለመኖር ለራስና ለወዳጅ ዘመድ ደስታ የሚሰጥ፤ የትውልድ ቀጣይነት እንዲኖረው አበርክቶ ያለው ነው። ኅብረተሰብ የአገር መሠረት መሆኑ ስለታመነበትም በእምነት እና በአስተዳደ ር ሕግጋት ጥበቃ ይደረግለታል።
ትዳር እንዲጸና የአገር ባህል የእምነት እና የመተዳደሪያ ልማዶች ሁሉ ይተባበራሉ። እንዲሁም ሆኖ በድህረ ዘመናዊነት በሚሰኘውና የቆዩ አሰራሮችና ልማዶችን በአብዛኛው እየተጻረረና እያፈረሰም በሚገኘው በእዚህ ዘመን ትዳር የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል። አንዳንድ የትዳር ተጣማሪዎች ድል ያለ ድግስ ደግስው ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ በሆነ ግርግር ተጋብተው ወር ሳይሞላ የሚፋቱበት ጊዜ እያጋጠመ ነው። አንዳንድ አገሮች እንዲያውም ከሁለት ዓመት በታች ፍች እንዳይፈቀድ ደንግገዋል።
ይሁንና በተቃራኒው ብዙ ትዳሮች ቱፊት ሕግና ስርዓታቸውን ጠብቀው በባልና በሚስት መተሳሰብ ፍቅር መተጋጋዝና መረዳዳት ደምቀው ይገኛሉ። ዛሬም እንደ ጥንቱ እምነት ባህላቸውን ጠብቀው የአኗኗር ሕይወታቸውን አሳምረው ከእዚህም ጋር መልካም ልጆችን ያፈሩ ባለ ትዳሮች ሞልተዋል። ልጆችና የልጅ ልጆችን በስጋ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ በተፈጥሮ ግብር ብቻ ሳይሆን በስነምግባር በእውቀት እና በማስተዋል ወልደው አሳድገው ወግ ማዕረግ ያዩ አያሌ ናቸው።
መልካሙ ጋብቻ
ከእንዲህ ዓይነት የተቀደሱ ትዳሮች አንዱ የወይዘሮ ሰዊተ ደምሴ እና የቀኝ ጌታ ኅሩይ ተፈራ አንዱ ነው። ይህ ትዳር ባሳለፍነው ሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓም የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩውን አክብሯል። ትዳሩ የተመሰረተው በ1961 ዓ.ም ሐምሌ 13 ቀን ነው።
የእነ ቀኝ ጌታ ኀሩይ ተፈራና ወይዘሮ ሰዊተ ደምሴ ከአዲስ አበባ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በቀድሞ አጠራሯ አዲስ አለም የአሁኗ ኤጄሬ በቀበሌ 03 በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በደስታ እና በፌሽታ ተሰርጎ ነው የተዳሩት። ዘንድሮ ደግሞ 50ኛ ዓመቱን ልጅ እና የልጅ ልጅ ወልደው አሳድገው አስተምረው ኩለው ድረው ለስራ እና ለኀላፊነት አብቅተው ባሉበት በራሳቸው መኖሪያ ቤት ዳግም ሰርጋቸው ተከብሯል።
የእነ ወይዘሮ ሰዊተ ትዳር መተሳሰብ መፈቃቀር እና መከባበር የሰፈነበት መልካም ትዳር ተብሎ ተመስክሮለታል። በዕለቱ የወንጌል ትምህርት የሰጡት የሀይማኖት አባት ”ጋብቻን መልካም ያለው እግዚያብሔር ነው”ካሉ በኋላ ወይዘሮ ሰዊተ ደምሴ እና ቀኝ ጌታ ኅሩይ ተፈራ መልካሙን ትዳር በመጠበቃቸው ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቻቸው ለትውልዱም መልካም አርአያ መሆናቸው ተናግረዋል። እንዲህ ያለ መልካም ጋብቻ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለው እንደሆነ ጠቁመው ወጣቱ ትውልድ እነ ቀኝ ጌታን ኅሩይ ተፈራ አርአያ አድርጎ በትዳር እንዲኖር መክረዋል።
እንኳን ሰው ሌሎች እንስሳ እንኳን በትዳር ተጣማሪዎቻቸው ላይ ጨዋ እንደሆኑ ገልጸው ማንኛውም ሰው ጋብቻ ከመሰረተ በኋላ እግዚያብሔር “መልካም” ነው ይህንን ተቋም አክብሮ ሊኖር ይገባል። “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚለውም የጋብቻን አስፈላጊነትንም ለማመልከት ነው” ብለዋል።
ከጋብቻ ወደ ፍቅር
የዘመናችን ጋብቻ ተዋውቆ እና ተፈቃቅዶ ነው። አንዲት ለትዳር የደረሰች ልጃገረድ ከአንድ ወጣት ተዋውቀው ተፋቅረው ለመጋባት ሲወስኑ ለቤተሰብ ያሳውቃሉ (ሽማግሌ ይልካሉ)። ከዚያ እንዲያው “ለወጉ” ሽማግሌ ይልኩና ይጋባሉ፤ በአሁኑ ወቅት ያለው ጋብቻ ፍቅር መጀመሪያ ቀጥሎ ጋብቻ ይከተላል። የጥንቱ የጠዋቱ ትዳር ግን አመሰራረት ደግሞ ከወቅቱ የትዳር አመሰራረት በተቃራኒው ነው። ጋብቻ ይቀድማል ፍቅር መተሳሰብ ይከተላል።
የጥንት የጠዋቱ ትዳር አመሰራረት ቤተሰብ እና ቤተሰብ በተለያዩ መለኪያ እና መሟላት ባለባቸው መስፈርቶች ተጠያይቀው “ልጅህን ለልጄ” ተባብለው ልጆቻቸውን ያጋባሉ። የወንዱ ቤተሰብ ሽማግሌ ልኮ የሴቷ ቤተሰብ ሽማግሌዎችን በአክብሮት ተቀብሎ ጥያቄያቸውን ይሰማል፤ ይስማማሉ፤ ሰርግ ተደግሶ ትዳር ይመሰረታል።
ማንኛውም ሰው ዘመኑን ተከትሎ እንደዘመኑ ነው የሚወጣው፣ የሚጋባው … በአጠቃላይ የሚኖረው። እነ ቀኝ ጌታ ኅሩይም በቤተዘመዶቻቸው እንደነበረው ስርዓት በቤተሰብ እምነት እና ስምምነት ነው ጋብቻቸው የተፈጸመው።
ቀኝ ጌታ ኅሩይ ግንቦት 28 ቀን 1934 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን ባለቤታቸው ወይዘሮ ሰዊተ ደግሞ 1946 ዓ.ም ይህን ምድር ተዋውቀዋል። ወጣቱ ቀኝ ጌታ ኅሩይ ተፈራ የ24 ዓመት አካባቢ ዕድሜ ፤ ልጃገረዲቱ ሰዊተ ደምሴ ደግሞ የ14 ዓመት ዕድሜ ላይ እያሉ “ሙሽራዬ…” ተባለላቸው።
እዚያው በተወለዱበት ፣በአደጉበት በሚያውቁት ከተማ ከወላጆቻቻው ሳይርቁ በቀድሞ አዲስ ዓለም በአሁኗ ኤጄሬ ከተማ ጎጆ ቀልሰው ኑሮን ቀጠሉ።
ምንም እንኳን በቤተሰብ ትጭጭቱ ቢፈጸምም ቀኝ ጌታ ኅሩይ ተፈራ በሚስጥር ወይዘሮ ሰዊተን ለማየት ጥረት አድርገው ከጋብቻ በፊት ሊያይዋቸው ችለዋል። በድብቅም ቢሆን ከቤተሰብ ምርጫ ጋርም የእርሳቸው ፍቀደኝነትና ውዴታም አለበት። በ50ኛ ዓመቱ ክብረ በዓል ላይ ባሳለፍናቸው የትዳር ዓመታት ለእኔ ከሆነችው አንጻር ከነብሴ ወደድኳት። ከእራሴ በላይ ያሉት ቀኝ ጌታ ኅሩይ ፤ በትዳሩ መጀመሪያ ወቅት እንዳኮረፈ ሰው ሆነው ወይዘሮ ሰዊተ ለአንድ ሁለት ቀን ማስቸገራቸውን ያስታውሳሉ። ባለቤታቸውን ያሳዩት ትዕግስት አድንቀው ወደፍቅር ሕይወት ማምረታቸውንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሰዊተ እንደ ቀኝ ጌታ ኅሩይ የወደፊቱን ባለቤታቸውን ከጋብቻ በፊት የማየት ዕድል አልገጠማቸውም። ይሁንና “ቤተሰብ የመረጠልኝን አሺ! ብዬ ነው የተቀበልኩት” ያሉን ወይዘሮ ሰዊተ ከቤተሰባቸው ሲለዩ መጨነቅ ማልቀስ ባይቀርላቸውም ቀኝ ጌታ ኅሩይን ግን ወደዋቸዋል። ከአዩአቸውና ከአገቧቸው በኋላም ደስ ብለዋቸዋል። “ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ !” አይደል የሚባለው …
“ሙሽሪት ልመጂ!
ሙሽሪት ልመጂ!
ከእናትሽ ከአባትሽ
ባልሽን ውደጂ! ቢባል ልክ ነው ማለት ነው።
የንግግር ተራ
ቁጣ የሰው ልጅ ከሚያሳያቸው ያልተገባ ጠባያትና የስሜት መግለጫ መንገድ አንዱ ነው። የማይቆጣ ሰው ይኖራል ለማለት ያስቸግረኛል። በተለያዩ የማይስማሙ ጉዳዮችና አጋጣሚዎች እንቆጣለን። አንዱ ለሌላው የተሰማውን መጥፎ ስሜት በቁጣ በሃይለ ቃል ይገልጻል።
ቅዱስ መጽሐፍ “ተምዑ ወኢተአብሱ … ተቆጡ ኃጢያትን ግን አታድርጉ !” ይላል። ሰው መቆጣቱ እንደማይቀር አስገንዝቦ “ተቆጡ” አለና “አጢያት ግን አታድርጉ” ብሎ ደግሞ ከቁጣ ወደ ቁጣ ከኃይለ ቃል ወደ ኃይለ ቃል ተግባር መሄድ እንደማይገባ ያስገነዝባል። ወይዘሮ ሰዊተ እና ቀኝ ጌታ ኅሩይ እንደማንኛው ሰው ይቆጣሉ። ነገር ግን ቁጣቸው ችግር አያስከትልም። አንደኛ እንደ ቤተክርስቲያን አገልጋይነታቸው ተቆጥተው መጥፎ ነገር አይሰሩም። ሁለተኛ የሚነጋገሩት በተራ ነው።
ወይዘሮ ሰዊተ ሲቆጡ ቀኝጌታ ቁጣው የሚበርድበትን መልካም ቃል ያወጣሉ። አቶ ኅሩይ ሲቆጡ ወይዘሮ ሰዊተ በሰላማዊ ምላሽ ከቁጣቸው ያበርዷቸዋል። መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች ማለት ይሄ ነው ሁለተኛው ልጃቸው አቶ እማዕላፍ ህሩይ “አብረው ሲጨቃጨቁ ወይም ሲቆጡ አላየሁም ፤ አንዳቸው ሲበሳጩ ወይም ሲቆጡ ሌላው ተረጋግቶ ይመልሳል። የሚገርመኝና ትልቁ ስጦታቸው በተራ መናደዳቸው ነው” ይላል ።
ወይዘሮ ሰዊተ እንዲህ አሉ” ህይወት ከባድ ናት ማለፊያ መንገድ ግን አላት” ለምሳሌ ንዴትና ቁጣ ሲመጣ ባልና ሚስት በእኩል ሰዓት መናደድ የለባቸውም ፤ አንዱ ሲቆጣ ሌላው ችሎ ለብቻ ንዴቱ ከበረደ በኋላ ለብቻ መወያየት ነው ያውም ልጆች በሌሉበት ።
ፈታኝ ጊዜ
ትዳርም ሆነ ኑሮ እንዲሁም ህይወት እንከን አልባ ሆነው አያውቁም የእነ ወይዘሮ ሰዊተ ትዳርም እነርሱን ፣ቤተሰባቸውን ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ሁሉ ያሳዘነ ያስጨነቀና ያስጠበበ ፈተና ገጥሟቸዋል። የመጀመሪያው ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረት ከእጃቸው ጠፋ ምክንያቱን ሊናገሩ በማይችሉት ችግር የልጅነት ወዛቸውን ያፈሰሱበት ንብረት እንደ ቀልድ ወደመ፤ ከእጃቸው እንዴት መቼ እና ምክንያቱን ሊያስረዱ በማይችሉት ሁኔታ ነው ንብረታቸው የጠፋው፤ ይህን ፈታኝ ጊዜ ወይዘሮ ሰዊተ ሲያስረዱ “ እኔ በጊዜው ልጅም ስለነበርኩ ንብረትን በአግባቡ መያዝ አልቻልኩም ነበር፤ ሌላኛው ደግሞ ዘመድ ከተናገረ ሁሉ ነገር እንዳለኝ እቆጥር ነበር ነገሩ እንዳሰብኩት አልሆነም” ይህን ፈታኝ ችግር ሳይወጡት ሌላኛው ችግር ደግሞ አይኑን አፍጦ መጣ ባለቤታቸው ቀኝ ጌታ ህሩይ በደረሰባቸው አደጋ አልጋ ላይ ለመዋል ተገደዱ ።
እግራቸው ላይ በደረሰ አደጋ ቤት የዋሉት ቀኝ ጌታ ኅሩይ እንደ ቀድሞ ቤተሰብን መምራት በተለይ ከባድ ጉልበት የሚፈልገውን የወፍጮ ስራ ማስተዳደር አቃታቸው፤ ይህ ብቻ አይደለም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ካጋጠማቸው ችግር ባሻገር አይናቸውን ታመው ቀዶ ህክምና ተደረገላቸው ፤ታዲያ እነዚህ ፈተናዎች ኑሮና ህይወታቸውን ፣ ትዳርና አንድነታቸውን ፈትኖታል። ሆኖም ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት የሚፈታ አንድነት በሰበብ የሚለያይ ህብረት አልነበረምና ሁለቱንም ችግሮች ችለው አሳልፈው ለሃምሳኛ ዓመት የትዳር ዘመን ክብር በቅተዋል። የትዳሩ የመጀመሪያ አደጋ ከተከሰተ በኋላ የነበሯቸው ልጆችና የልጅ ልጆች እጥፍ ሆነዋል ።
የትዳር ጣዕምና ደስታ
ከማንኛውም ነገር ሁሉ በላቀ ሁኔታ ደስታን የሚለግስ አንድ ነገር አለ ፤ ምን ይሆን?… በጣም ቀላልና በእጅ የሚገኝ ነው። ይህን ምስጢር ለጨረታ ላቀርበው ብችል ምን ያህል ሰው በጎረፈ! ዋጋውም ምንኛ በናረ! ብልሆች ብቻ ናቸው ምንነቱን የሚገምቱት። አንዳንዶቹ ጤንነት ፣ ወይም ገንዘብ ፣ ወይም ብዙ ወዳጅ ፣ ወይም ይህን ወይ ያን ሃብት ይሉ ይሆናል። ግን፣ እነዚህ ሁሉ ተሟልተው ደስታ ሙሉ ላይገኝ ይችላል። ዝናና ሥልጣንም ደስታን አያስገኙም። ጤንነት ፣ ገንዘብ ፣ ባልንጀራ ፣ የሞቀ ቤት … ሁሉም አስፈላጊ ቢሆኑም ደስታ አያጎናጽፉምና ከእነዚህ ሁሉ የሚልቅ አንድ ነገር አለ። እርሱም እውነተኛ ባልንጀራ ነው፤ ሰው የጠፋ ዕለት ሰው የሚሆኑ ሰው ለደስታህ ብቻ የሚሆን ሳይሆን ችግርህ የሚገባው ለባልንጀራው የሚኖር ሰው የደስታ ምንጭ ነው።
ስለዚህም እውነተኛ አጋር ካለ ምንም እንኳን ህይወት በፈተና የተሞላች ብትሆንም እውነተኛ አጋር ካለ ደስታ የጸና ይሆናል።
የቀኝ ጌታ ኅሩይ እና የወይዘሮ ሰዊተ ሕይወት ፈተና፣ኑሮ ችግር እንዳመጣው ለመግለጽ እንጂ የትዳር ጣዕምና ደስታ ከፈተናው ይበልጣል። ትዳር”መልካም” ነው የተባለውና ብቸኝነት በእምነትም ከማህበራዊ ሊቃውንትም አንጻር ተቀባይነት የለውም። ቀኝ ጌታ ኅሩይ እና ወይዘሮ ሰዊተ በትዳር ህይወታቸው ከአዘኑበት ይልቅ የተደሰቱበት አያሌ ቀን ነው። ዛሬም ቢሆን ባላቸው ኑሮ በጣም ደስ እያላቸው ነው ህይወታቸውን የሚመሩት። “ከልጅ አልፎ የልጅ ልጅ የሚሰጠው ደግሞ ፍቅር ነው። በቅዱስ ቃሉ ስለተረዳን ይበልጥ ደስ ይለናል” ያሉን ቀኝ ጌታ ኅሩይ ናቸው።
የዳቦ ስም
ለሴት ሙሽራ ዳቦ ተቆርሶ ወግ ደርሶ የወንዱ ቤተሰብ የሚጠራበት ስም ይወጣል። ስያሜውም በወርቅ የተደገፈ ነው…አመለወርቅ፣ዙሪያሽ ወርቅ…የሚልና ጠባየ ሸጋ፣ ተግባቢ…እንትሆን የሚመኝ ነው። የወይዘሮ ሰዊተ የዳቦ ስም ማን እደሆነ የነገረኝ የለም። አንድም ከዳቦ ጋር ተረስቷል። የትዳር አጋራቸው ያወጡላቸውን ስም ግን ራሳቸው የቀኝጌታ ኅሩይ ልጆች ነግረውኛል። ወንድ ልጃቸው እምአዕላፍ “እናቴነሽ ፣መከታዬ” ሲባባሉ እንደሰማ ይነገራል። ቀኝ ጌታ ኅሩይም ማን ብለው ባለቤታቸውን እንደሚጠሩ በጠየኳቸው ጊዜ ከፈገግታ ጋር “እኔ እናቴነሽ፣ መድሐኒቴ፣ ጓደኛዬ…ነው የምላት”ብቻ ምን አለፋቹ በአንዴ ሺውን ነው የዘረገፉት …እንዴት ይህ ሁሉ ጠየኳቸው ያሳየችኝ ብዙ ፍቅር እና መራራት ነዋ! አጥፊቼም የምታልፈኝ በምክር ነው።
ልጆች ምን ቀሰሙ
ቀኝ ጌታ ኅሩይ ተፈራና ወይዘሮ ሰዊተ ደምሴ በ50 ዓመት የትዳር ዘመናቸው ስድስት ልጆች አፍርተዋል፤ የተወሰኑት አግብተው አምስት የልጅ ልጆችን አሳይተዋቸዋል። የቀሩትም የታላላቆቻቸውን አርአያ ለመከተል በዝግጅት ላይ ናቸው።
ወላጅ በልጆቹ አንደበት
የ50 ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል የምስጋና ፕሮግራም መሪ እምሕላፍ ኅሩይ ከእናቱ እና ከአባቱ ቤተሰባዊ፣ ማህበረሰባዊ ክብርና ፍቅርን ቀስሟል። የሴት ልጅንም ክብር አውቋል፤ በተለይ ይላል እናቴ አባቴ በደከመበት ጉዳት ባጋጠው ወቅት ለወንድ እንኳ አስቸጋሪ የሆነውን የወፍጮቤት ስራ ቀጥ አድርጋ በመምራት የሴት ልጅን ጥንካሬ አሳይታኛለች። የሚገርመኝ ነገር ይላል እምዕላፍ የወፍጮ ችንጋ ሳይቀር የምትቀይረው እናቴ ናት ፤በተለይ አሁን አባቴ አይኑን ስለታመመ ሁሉም ኃላፊነት የወደቀው እናቴ ትከሻ ላይ ነው፡፡ ከእርሷ አሁን ያሉት ሴት ወጣት ያገቡም ለማግባትም በዝግጅት ላይ የሚገኙ እውነተኛ እረዳትነት ምን ዓይነት እንደሆነ የሚማሩባት ጀግና ሴት ናት ብሏል። በዚህም ምክንያት ለሴት ልጅ ክብር ያሰጣል።
የእናቱን እና የአባቱን ሽምግልናና የሽምግልና ምልክት የሆነውን ሽበት በልዩ ክብርም እንደሚያየው ይናገራል። “ሽበት የማህበረሰብ ጠበቃና ጠባቂ አሳዳጊ እና አስታራቂ ነው። በእናት እና በአባት ህብረት ፍቅር እና እንክብካቤ ያደጉ የልጅ ልጆች የተረጋጉ ምድርንም የሚያረጋጉ ይሆናሉ። አባቴ እና እናቴ ይህንን አስተምረውኛል”ብሏል።
ሌላኛዋ የወይዘሮ ሰዊተ እና የቀኝጌታ ኅሩይ ልጅ ሜላት ኅሩይ የተናገሩት “በየትኛውም የዕድሜ ክልል ይገኝ ልጅ ለወላጆቹ ልጅ ነው፤ ይህ ደግሞ ወላጆቼ በራሴ ህይወት እንዳየው አድርገውኛል። “እግዚያበሔር እንዲህ ያሉ አባት እና እናት ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ፡፡ ህይታቸውን ለእኛ ሲሰጡ፣ ሲያስተምሩ፣ ሲያለብሱ፣ ሲመግቡን ኖረዋል ያለአንዳች ስስት ለዚያውም የተለያየ የህይወት ፈተናን እተጋፈጡ..፤ታዲያ ይህ ፍቅር ዛሬም ያው ነው ከእኛ አልፈው ለልጅ ልጆቻቸን ያስባሉ” ብለዋል።
ቀኝ ጌታ ኅሩይ እና ወይዘሮ ሰዊተ እነርሱ ሲገናኙም ሆነ ሲጋቡ በቤተሰብ ፍቃድ ይሁን እንጂ ልጆቻቻው በራሳቸው ፈቃድ ያመጣቸውን “እኛም ወደናል ይሁን (ትሁን)” ብለው ነው የሚድሩት። እኛ አናጭም በእኛ ዘመን እንደነበረው ይሁን አንልም። ሁለቱ ተጋቢዎች ተሳስበው ለጋብቻ ወስነው ሲመጡ እኛም እንቀበላለን”ነው ያሉኝ።
ረጅሙን የትዳር እና የህይወት ጉዞ በግጥም እያዋዛ ያቀረበው በቤተሰቡ እንደ በኩር ልጅ የሚታይ እና በስጋ ግን የወይዘሮ ሰዊተ የእህት ልጅ የሆነው አቶ ተሾመ በትሩ እነዚህ ጥንዶች በሀይማኖትም በመጠበቅም ሆነ በማህበራዊ ህይወት ምሳሌ እንደሆኑ ጠቅሶ የረጅም ጋብቻ ሚስጥር ሁለቱም ባለትዳሮች እርስ በራሳቸው የሚያሳዩት ደግነት እና ውስጥን መረዳት መሆኑን ይናገራል። ታዲያ እነዚህ የህይወት አጋሮች ይመካከራሉ፡፡ይወቃቀሳሉ ያለአንዳች ሶስተኛ ወገን ማለቴ ነው፡፡
በተጨማሪም በባለ ትዳሮች መሃከል ያለ የምስጋና ስሜት እጅግ አስገራሚ ነው። ባል እና ሚስት በዚህ ልክ ሲመሰጋገን ስታይ ትገረማለህ ፤ በትዳር አጋራቸው የሚመሰገኑ እና የሚሞገሱ ሰዎች ለትዳራቸው ይበልጥ ታማኞች እና ለህይወት መልካም አስተሳሰብ ስላላቸው መሆኑን ይመሰክራል። በመጨረሻም አቶ ተሾመ “በረጅሙ የ50 ዓመት ትዳራቸው ለትውልዱ ምሳሌ የሚሆን ነው፤ ለእኛም ለልጅ ልጆቻችንም አርአያ ሆነዋል። ረጅም ጤና ይስጥልኝ !”ብለዋል።
ምክር ከጥንዶቹ
ለ50 ዓመት በትዳር የቆዩት ጥንዶቹ በርካታ ውጣ ውረዶችን ቢያሳልፉም ሰፊውን ዘመናቸውን በመተሳሰብ በመቻቻል እንዲሁም በንፁህ ፍቅር ነው ያሳለፉት። ታዲያ እነሱ ያሳኩትን በትዝታ በደስታ የተሞላ ህይወት በዚህ ዘመን ላይ የሚኖሩ ጥንዶችም ሊደግሙት እንደሚችሉ ሙሉ እምነት አላቸው። ይህን ሲሉ ግን እነርሱ ካሳለፉት ህይወት ያገኙትን ልምድ በማካፈል ነው።
ጥንዶቹ ትዳር በጥንቃቄ እና በብልሃት ሊይዙት የሚገባ ፀጋ ነው በማለት በዚህ ህይወት ውስጥ የሚገኙ ሁሉ ሆደ ሰፊ እና ትግዕስተኛ መሆን እንደሚገባቸው ይናገራሉ። አለመስማማት በሚፈጠርበት ወቅት አንደኛው ወገን ችግሩን ላለማባባስ ዝምታን አሊያም ደግሞ ይቅር ማለትን መልመድ እንደሚኖርባቸው ይናገራሉ። ከዚህ ባለፈ ትዳርን አክብሮ በጋራ ህግ አብሮ መኖር ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ መሆኑን ይገልፃሉ። እነዚህን ተግባራት የዚህ ዘመን ባለትዳሮች መተግበር ከቻሉ በደስታ የተሞላ የረጅም ዘመናት የደስታ ህይወትን እንደሚጋሩ ያስረዳሉ።
በእሁድ የህይወት እንዲህ ናት ገፃችን ይዘንላችሁ ከቀርብንላችሁ ባለትዳሮች በርካታ የህይወት ቁምነገሮችን እንዳገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን። አዲስ ቤት ቀልሳችሁ የህይወት ሀሁን ማጣጣም የጀመራችሁ ባለትዳሮች ከእነ ቀኝ ጌታ ህሩይ እና ከወይዘሮ ሰዊተ የ50 ዓመታት የትዳር ቆይታ ትምህርት ወስዳችሁ ያማረ ህይወት እንድትኖሩ ተመኘን፤ ሰላም !
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2011
አብርሃም ተወልደ