
የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ከአምስት እስከ 10 ዓመታት ውስጥ አሜሪካ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ውስጥ ያላትን ሚና በአውሮፓ ኃይሎች ለመተካት የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀታቸው ተገልጿል። እቅዱ ለአውሮፓ ደኅንነትና መከላከያ አሕጉሩ ራሱ የበለጠውን ኃላፊነት እንዲወስድ የሚያደርግ ነው ተብሏል። ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና የኖርዲክ ሀገራት የጦር ኅብረቱን ቅርጽ የሚለውጠውን እቅድ ካዘጋጁት ሀገራት መካከል እንደሚጠቀሱ ‹‹ፋይናንሻል ታይምስ›› (The Financial Times) ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል። አውሮፓውያኑም ይህን እቅድ በመጪው ሰኔ ከሚካሄደው የድርጅቱ ዓመታዊ ስብሰባ ቀደም ብለው ለአሜሪካ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኔቶ አውሮፓና ካናዳ የወታደራዊ ኅብረቱን የጦር መሣሪያና የቁሳቁስ ክምችት በ30 በመቶ እንዲያሳድጉ ጥያቄ ለማቅረብ ማሰቡን ‹‹ብሉምበርግ›› (Bloomberg News) ዘግቧል። የአውሮፓ መሪዎች በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡበትና ይህን እቅድ እንዲያዘጋጁ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከሆኑ ወዲህ እየወሰዷቸው ያሉት ርምጃዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የአውሮፓ ፖለቲከኞች የሩሲያ ቀጣይ የወረራ ዒላማ አውሮፓ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ለዚህም አውሮፓ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት ያሳስባሉ። አውሮፓ በአስተማማኝነት ራሱን መከላከልና ማስከበር የሚችለው በራሱ የመከላከያ ኃይል እንደሆነ የሚያምኑት እነዚህ የአውሮፓ ፖለቲከኞች፣ ከአሜሪካ ጥላ ነፃ የወጣ አውሮፓዊ የመከላከያ ኃይል እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ።
የዩክሬን ጦርነት አውሮፓን በብዙ መንገዶች አስጨንቋል። የሩሲያን ነዳጅና ሌሎች ምርቶችን በብዛት የሚገዙት የአውሮፓ ሀገራት ከደረሰባቸው የምጣኔ ሀብት ተፅዕኖ ባሻገር፣ ሀገራቱ የሩሲያ ወታደራዊ የጥቃት ሰለባ የመሆን ስጋትም አለባቸው። በርካታ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ለዩክሬን በሚያደርጉት የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ በእጅጉ የተበሳጨችው ሩሲያ፣ ለምትወስዳቸው የአፀፋ እርምጃዎች ኃላፊነቱን ሀገራቱ እንደሚወስዱ ትዝታለች። አውሮፓውያኑ የሩሲያ ርምጃዎች ወታደራዊ ጥቃቶችን ሊጨምር እንደሚችል ይገምታሉ።
የሩሲያን ዛቻ ለአውሮፓውያኑ የበለጠ አስፈሪ ያደረገው ደግሞ የዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ወደ ‹‹ዋይት ሐውስ›› መመለሳቸውና የሚወስዷቸው ርምጃዎች ናቸው። ‹‹ምርጫውን ካሸነፍኩ በአንድ ቀን አስቆመዋለሁ›› ያሉትን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም የወሰዷቸው ርምጃዎች በአውሮፓ ፖለቲከኞች ዘንድ በበጎ አልታዩላቸውም። ፕሬዚዳንት ትራምፕ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪን ‹‹ጦርነቱን የጀመረ፣ አምባገነን፣ ለሰላም ፍላጎት የሌለው…›› በሚሉ ቃላት መሸንቆጣቸው፣ አሜሪካ ለዩክሬን ስትሰጠው የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ እና የስለላና ደኅንነት መረጃዎችን ለዩክሬን ማጋራቷን ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ማቋረጣቸው፣ ስለዩክሬን የኔቶ አባልነትና በሩሲያ ስለተያዙት ግዛቶቿ ጉዳይ የተናገሯቸው ንግግሮች እንዲሁም በመጀመሪያዎቹ የሩሲያ-አሜሪካ-ዩክሬን የድርድር መድረኮች ላይ የአውሮፓ ሀገራትን ለማሳተፍ አለመፈለጋቸው አውሮፓውያኑ ስለቀጣዩ የአሕጉራቸው ዕጣ ፈንታ እንዲያስቡ ምክንያት ሳይሆናቸው አልቀረም።
አሜሪካ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ውስጥ ግዙፍ ውሮፓ እስከ 100ሺ የሚደርስ ጦርም አሰማርታለች። ይህ የሚያሳየው አሜሪካ በአውሮፓ ፀጥታና ደኅንነት ውስጥ ከፍተኛ ድሚና አላት። ከድርጅቱ ዓመታዊ ወጭ ውስጥ ከ16 በመቶ የሚበልጠውን የምትሸፍነው አሜሪካ ናት። በመላው አርሻ እንዳላት ነው።
ለባለብዙ ወገን ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ትብብሮች ብዙም ግድ የሌላቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ በሰሜን አትላንቲኩ ወታደራዊ ትብብር ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን ያቀርባሉ። ፕሬዚዳንቱ የድርጅቱ አብዛኛው ሥራና ኃላፊነት በአሜሪካ ትከሻ ላይ የወደቀ ነው ብለው ያምናሉ። አባል ሀገራቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እያደረጉ እንዳልሆነና ለድርጅቱ የሚያደርጉትን መዋጮ እንዲያሳድጉም ደጋግመው ይናገራሉ። ‹‹አሜሪካ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣች አውሮፓን የምትጠብቀው በምን ዕዳዋ ነው?›› እያሉ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በዚህም የተነሳ ፕሬዚዳንቱ አሜሪካ አውሮፓን ላለፉት 75 ዓመታት ሲጠብቅ ከኖረው የትራንስ አትላንቲክ የጦር ኅብረት ልትወጣ እንደምትችል ሲዝቱም ነበር። ታዲያ ይህን የአሜሪካ ዛቻ ችላ ማለት ያልፈለጉት የአውሮፓ ሀገራት የመከላከያ በጀታቸውን እንደሚያሳድጉ ገልፀዋል። ለአብነት ያህል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ለመከላከያ ኃይላቸው የሚመድቡትን በጀት እንደሚጨምሩ አሳውቀዋል።
ባለፈው ወር በጀርመን በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኙት የወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራቲከ ኅብረት ፓርቲ (CDU) ሊቀ-መንበርና ቀጣዩ የጀርመን መራኄ መንግሥት እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ፍሬድሪክ ሜትስ አውሮፓ ከአሜሪካ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለበት በፅኑ የሚያምኑ ፖለቲከኛ ናቸው። ከአሜሪካ ጫና የተላቀቀ አውሮፓን መገንባት ከዋና ዋና እቅዶቻቸው መካከል አንዱ እንደሆነና ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሚወስዷቸው እርምጃዎች በእጅጉ መበሳጨታቸውን የሚናገሩት ሜትስ፣ የአሜሪካ መንግሥት የአውሮፓ መፃኢ ዕድል ግድ እንደማይሰጠው በግልጽ ማሳየቱንና አውሮፓ በፍጥነት የራሱ የሆነ መከላከያ ሳያስፈልገው እንደማይቀር ተናግረዋል። ‹‹ከአሜሪካ በኩል ምን ዓይነት ውሳኔና እርምጃ እንደሚመጣ ብዥታ የለብኝም። ከአሜሪካም ከሩሲያም ከፍተኛ ጫና እየደረሰብን ነው›› በማለት አውሮፓ ለምጣኔ ሀብቱም ሆነ ለፀጥታው ተባብሮ ከመቆም ውጭ ሁነኛ አጋር አለኝ ብሎ መዘናጋት እንደማያስፈልገው አበክረው ሲናገሩ ይደመጣሉ።
አሜሪካ በአውሮፓ ፀጥታና ደኅንነት ውስጥ ያላት የገዘፈ ሚና ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ርምጃዎችና ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ጋር ተዳምሮ አውሮፓ ከአሜሪካ ጫና የተላቀቀና በራሱ የሚመራ አስተማማኝ የሆነ የደኅንነት ዋስትና እንዲኖረው የአሕጉሩ ፖለቲከኞች ላይ ታች እያሉ ነው። ከአምስት እስከ 10 ዓመታት ውስጥ አሜሪካ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ውስጥ ያላትን ሚና በአውሮፓ ኃይሎች ለመተካት ያስችላል የተባለው እቅድ ስኬታማ ከሆነ በትራንስ አትላንቲክ ትብብር ዕጣ ፈንታ ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያስከትል ይሆናል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም