ኢትዮጵያውያን ዳግም ገዝፈው የታዩበት የዓባይ ግድብ

አዲስ አበባ ፦ የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም፤ ጉልበትና ገንዘብ የተገነባ በመሆኑ አይቻልምን የሰበረ ነው ሲሉ የውሃ መሐንዲሱ ኢንጅነር አበራ ተስፋዬ ገለጹ።

ኢንጂነር አበራ የዓባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 14ኛ ዓመት አስመልክተው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ ዓባይን የመሰለ ግዙፍ ፕሮጀክት በራስ አቅም ፤ በራስ ባለሙያ፤ በራስ ወጪ ተሠርቶ አያውቅም። ይህም አይቻልምን የሰበረና መንፈሱም ከዓድዋ ድል የተቀዳ ነው። ኢትዮጵያውያንም የላቁበት፣ ውጤታማ ሥራ ሠርተው ለዓለም ያሳዩበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያ ብዙ የላቁ ተግባራትን ማከናወን እንደምትችል ያረጋገጠ ነው ያሉት ኢንጅነሩ፤ ያላትን ሀብት የመጠቀም ልምዷን ከፍ እያደረገች እንደሆነም የሚያሳይ ነው። በተለይም በቴክኒካል ሥራዎች ልቃ የታየችበት ነው። በኢኮኖሚያችን ከፍ የምንልበትን ነፃነትንም ያወጀችበት ዳግማዊ ዓድዋ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ግድቡ አይችሉምን ወደ ይችላሉ ቀይራለች። እንደ ግብፅ አይነት ሀገራትንም ሃሳብ ማስቀየር የቻለችበት እንደሆነ አመልክተው፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሃሳብ እንዲያሸንፍ ያደረገችበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ለዚህ መሠረቱ ደግሞ ማንነታችን በነፃነት የተገነባ እንደሆነ አስረድተዋል።

በነፃነት የተሠራ ሰው መቼም ቢሆን አይወድቅም፤ አይሸማቀቅም። የጀመረውን ሳይጨርስም ወደ ኋላ አያፈገፍግም። ሁልጊዜ ለስኬቱ ይዋደቃል። የወደፊቱንና እድገቱን ይመለከታልም። ሁሌ ብልፅግናውን ያስባል የሚሉት ኢንጅነር አበራ፤ በዓባይ መነሻነት ቀጣይ ሥራዎቻችን ያብባሉ። ፍሬያቸውን ለመቅመስም አንቸገርም ሲሉም ገልጸዋል።

ዓባይ ግድብ የኢትዮጵያ አበርክቶ ዓለም ላይ ጭምር እንዲታይ የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም አረንጓዴ ታዳሽ ኃይል በመሆኑ የአካባቢ ደኅንነትን ይጠብቃል። የአየር ንብረት ለውጥን ይቀንሳል።

በዚህም ኢትዮጵያ የዓባይን ግድብን ስትገነባ ከራሷ ተጠቃሚነት አንጻር ብቻ እንዳልሆነ ሁሉም መገንዘብ ይገባዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዓባይ ግድቡ ለሌሎች ሀገራትም ጠቃሚ በሚሆን መልኩ ሠርታዋለች ሲባል አንዱ ማሳያ ከአስዋን ግድብ ከ10 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የሚሆነውን በትነትና በስርገት የሚባክን ውሃን እንዳይባክንና የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ግድቦቻቸው በደለል እንዳይሞሉ ማድረግ መቻሏን ኢንጅነር አበራ ጠቁመዋል፡፡

የመስኖ ልማታቸውን እንዲያሰፉና እንዲያከናውኑም ዕድል ይፈጥርላቸዋል የሚሉት የውሃ መሐንዲሱ፤ ሌሎችን ስታስብ የራሷንም ጥቅም የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በማከናወን ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷ በተለይም ከወንዝ የሚመጣው ውሃ ነዳጅን ሊተካ የሚችል አቅም ያለው እንደሆነ ጠቁመው፤ የውሃ ማማ እየተባለች የምትጠራበትን የወንዝ ሀብቷን በአግባቡ አልምታ መጠቀም ይኖርባታል ሲሉ አስገንዝበዋል።

“እኛ ተፈጥሮ ያደለችን ሕዝቦች ነን ስንል ዝም ብለን አይደለም። ውሃ፤ መሬት፤ በቂ የሰው ኃይልና ጉልበት አለን። ነገር ግን ከአለን አንጻር ምንም አልሠራንም፤ አልተጠቀምንም።

ያለንን ሀብት አጣጥሞ የመጠቀም ችግርም ገጥሞናል፡፡” የሚሉት ኢንጅነር አበራ፤ መለወጥ ከአሰብን እነዚህ ነገሮች በአግባቡ አስማምተንና አቀናጅተን ልንጠቀምባቸው ይገባል። የሥራ ባህላችንን መቀየር ያስፈልገናልም። በተለይም በሃይድሮፓወርና የመስኖ ሥራዎች ጅምሮች እየታዩ በመሆናቸውም እነርሱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አመልክተዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You