የስንዴ ልማቱ ከፍታ

በዚህች ሀገር ስንዴ ከውጭ ሊገዛ ስለመሆኑ፣ ወይም የተገዛው ስንዴ ወደብ ስለመድረሱ፣ ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዘ ስለመሆኑ፣ ወዘተ የሚወጣ ዘገባ ከተሰማ ዓመታት አልፈዋል። ከውጭ ከሚገዛ የስንዴ ጥራት ጋር ተያይዞ ይነሳ የነበረ ጥያቄ ከተረሳ ቆይቷል።

የዱቄት ፋብሪካዎች ስንዴ፣ ዳቦ ቤቶች ዱቄት አጣን ሲሉም አይሰማም፤ ስንዴም ዱቄትም በመጥፋቱ የተነሳ ዳቦ ጠፋ ሲባልም እንዲሁ። አሁን በዚህ በኩል ጥያቄ ሊሆን የሚችለው የዳቦ ግራም መቀነስና የዋጋው እየጨመረ መምጣት ብቻ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ዓመታት መንግሥት ምን ያህል ስንዴ በዓመት እየተገኘ እንደሆነ፣ ስንዴው በምን ያህል ማሳ እየተመረተ ስለመሆኑ፣ በመኸርና በበልግ እንዲሁም በበጋ መስኖ በልማቱ ምን እየተከናወነ ስለመሆኑ ሲገልጽ ሲያብራራ ይሰማል፤ አየሩን በእጅጉ የያዘው ይሄ ነው።

ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተጓዘ እግረ መንገዱም ይሁን በመዳረሻው አካባቢ ብዙም ወደ ውስጥ ሳይገባ በተለይ በሰብል አምራች አካባቢዎች በበጋ ወቅት የተንጣለሉ አረንጓዴ የለበሱ የስንዴ ማሳዎችን ሊመለከት ይችላል፤ ይህም በጋው በከፋበት፣ አቧራው በንፋስ ኃይል እየተቀሰቀሰ ቆሞ የሚሄድ በሚመስልበት ወቅት አረንጓዴ ማሳ ተንጣሎ መመልከት በእርግጥም ግርምትን ያጭራል። በኢትዮጵያ ይህ እየሆነ ይገኛል።

የማሳዎቹ ስፋት ሲታሰብ ደግሞ አካባቢው ለብቻው ክረምት የተፈጠረለትም ሊመስል ይችላል። ይህን ሰው መገናኛ ብዙኃን ብቻ አይደሉም፤ ሰዎችም በስፋት ይሉታል። በተለያዩ የምርት ዘመኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የስንዴ ማሳዎች ሲጎበኙ መመልከት ተለምዷል፤ መሪዎቹ ስንዴ እንዲለማ ትእዛዝ ሰጥተው አቅጣጫ አስቀምጠው ብቻ አልተቀመጡም፤ ልማቱ ምን እንደደረሰ ምን እንደሚያስፈልገውም ይከታተላሉ።

አዝመራው በሜካናይዜሽን ሲሰበሰብ፣ ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ የውሃ ፓምፖች ሲሰራጩ፣ ትራክተሮችና ኮምባይነሮች በስፋት ለአርሶ አደሩ ሲቀርቡ፣ ወዘተ ማየት ተለምዷል። በማሳ ዝግጅት፣ በዘር፣ በቡቃያው እንዲሁም በአዝመራ ስብሰባው ወቅት ይህን አድርገዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት ዓመቱ መክፈቻ፣ መዝጊያና የየስድስት ወራት ሪፖርት በሚቀርብበትና ማብራሪያ በሚሰጥበት ወቅት ተጠቃሽ ሆነው ከሚቀርቡት መካከል ስንዴ ዋናው ነው። እሱም የተሰጠውን ትኩረት ያህል እየሰጠ ይገኛል።

ዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ ተቋማትም ጭምር የሀገሪቱን የስንዴ ልማት ማሳ ድረስ ተገኝተው ይጎበኛሉ። የአፍሪካ ልማት ባንክ በተለያዩ መድረኮች ላይ ይህን የስንዴ ልማት ያደንቃል። የባንኩ ፕሬዚዳንት የስንዴ ልማቱን ሁሌም ይጠቅሳሉ። የዓለማችን ሀብታሙ ቢልጌት ልማቱን ጎብኝተውታል። የአንዳንድ አፍሪካ ሀገሮች ልዑካን ቡድኖችም የመስክ ጉብኝት ስለማድረጋቸው የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች አመላክተዋል።

ሁሉም በምክንያት ነው የሆነው፤ አዎን በዚህች ሀገር በስንዴ ልማት ታሪክ እየተሠራ ይገኛል። ልማቱ በመኸርም በበጋ መስኖም በስፋት እየተካሄደ ነው። በስንዴ ልማቱ በየዓመቱ የሚሸፈነው መሬትም፣ የሚገኘው ምርትም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተመዘገበ ያለው ውጤት ሀገሪቱን የዳቦ ቅርጫት የማድረጊያው ዘመን ይህ ያለንበት ዘመን እንደሚሆን ያመላክታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በ2011 ዓ.ም በሀገሪቱ ቆላማው አካባቢ በተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተገኘው ምርት 26 ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ ነበር። ይህ አኃዝ በቀጣዩ ዓመት ወደ 54 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል። እንዲህ እንዲህ እያለ ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚገኘው ምርት ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ደርሶ ነበር።

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንዳመለከተው፤ በመኸር ብቻ የሚገኘው ዓመታዊ የስንዴ ምርት ከ48 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 152 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል። በ2011 ዓ.ም በ3ሺህ 500 ሄክታር መሬት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደግሞ፥ አሁን ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ማደጉን በማንሳት ከዚህም 172 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው። አጠቃላይ የስንዴ ምርቱም /መኸር፣ በልግና የበጋ መስኖ ብሎ/ ቢሆን ዘንድሮ 300 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁትም፤ ስንዴን ብቻ እንደ አንድ የሰብል ምርት ብንወስድ፤ በመኸር አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ለምቷል፤ በበጋ መስኖ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ታርሷል። በድምሩ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከሰባት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር ያላነሰ መሬት በስንዴ ሰብል የሸፈነች ሲሆን፣ ከዚህም ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ይጠበቃል።

‹‹ይሄ ዘርፉን ለሚያውቁ ሰዎች፣ ሀገሪቱ ስንዴ ከውጭ ማስገባት የለባትም፤ በራሷ ማምረት አለባት ብለው ለወሰኑ ሰዎች እንደ ተዓምር ሊወሰድ እንደሚችልም አመልክተው፣ ይህ ስኬት ዛሬ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ከፍተኛ ስንዴ አምራች ሀገር እንዳደረጋትም ተናግረዋል።

በእርግጥም ተዓምር ነው። የኢትዮጵያ አጠቃላይ የግብርና ምርት ቀደም ሲል 300 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህን ዓመታዊ የግብርና ምርት ነው በስንዴ ብቻ መድረስ እየተቻለ ያለው። እናም በስንዴ ልማቱ የተገኘው ስኬት በራሱ ጮክ ብሎ እየተናገረ ይገኛል፤ ይህን ማስተጋባት ግን ይገባል።

ሀገሪቱ በእዚህ ልክ ስንዴ ልማት ውስጥ ስለተገኘች ለዘመናት አብሯት የኖረው የስንዴ ግዥ ጥያቄ አብቅቶለታል። ለእዚህም ነው ፋብሪካዎች የስንዴ፣ ዳቦ ቤቶችም የዱቄት ያለህ ሲሉ የማይሰሙት። ለእዚህም ነው የስንዴ ዓለም አቀፍ ግዥ ጨረታ እንዲሁም የስንዴ ማጓጓዝ ወሬም የማይሰማው። ልማቱ እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች አውርዷቸዋል። በሀገሪቱ በዚህ ሁሉ ምትክ አየሩን የያዘው፣ እየተሰማ ያለው እንደጠቀስኩት የስንዴ ልማቱ በምን ያህል መሬት እየተካሄደ፣ ከዚህ በአጠቃላይ ምን ያህል ምርት እየተገኘ ስለመሆኑ እንዲሁም በቀጣይም መድረስ ስለሚፈልግበት ከፍታ ነው።

የሕዝብ ብዛት እየጨመረ መምጣት እንዲሁም ከአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ የስንዴ ፍላጎት በየዓመቱ በሚጨምርባት ሀገር፣ የስንዴ ዱቄት ፋብሪካዎች እንደአሸን በፈሉባት ሀገር፣ ምንም አይነት የስንዴ እጥረት አለመታየቱ የልማቱን ስኬታማነት ይመስክራል፤ ስንዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ከፍተኛ ፍላጎት እየቀረበበት ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ስንዴ ከዓለም አቀፍ ገበያ ከመሻማት ውስጥ ወጥታ መገኘቷ ያጋጣሚ አይደለም፤ ታስቦበት በቁርጠኝነት በመሠራቱ ነው።

በስንዴ አምራች ሀገሮች አካባቢ ከተከሰተው ጦርነትና ከዓለም አቀፍ ጫናዎች ጋር በተያያዘ የውጭ ምንዛሪ ይዞ ስንዴ መግዛት ምን ያህል ፈታኝ እንደነበረ ኢትዮጵያ በሚገባ ታውቃለች። በእዚህ በእጅጉ ተፈትናለችና። በተለያዩ ወገኖች ጫና መግዛት እንዳትችል ተደርጋለች። መንግሥት የሀገር ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደተቻለው ሁሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አምኖበት በስንዴ ልማቱ በቅጡ መሥራት ውስጥ የገባበት አንዱ ምክንያት ይሄው ይመስለኛል።

ይህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በቀጣይም በስፋት ይሠራበታል፤ መንግሥት በመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሠራ ነው፤ ወንዞችን በመገደብ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በመቆፈር ላይ ተጠምዷል። ወደ ልማቱ የገቡ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸውን አጣጥመዋልና ማሳ እንደሚያስፋፋ፣ ማሳ ከሌላቸውም ሊኮናተሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ወደ ልማቱ ያልገቡ አርሶ አደሮች የመስኖ ልማቱ ያስገኘውን ጥቅም በመረዳትና ተሞክሮ በመቅሰም ባሉት የውሃ አማራጮች በመጠቀም ወደ ልማቱ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ልማቱ በሁሉም መልክዓ ምድሮች ላይ እየተካሄደ ነው። በቆላ ጀምሮ ወይናደጋ፣ ደጋ እያለ ዘልቋል። ግድቦች ባሉባቸው አካባቢዎች የግድቦቹን ውሃ በመጠቀም እንዲሁም አርሶ አደሮች ወንዝ እየገደቡ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ እያወጡ ልማቱን ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህ ልማት አርሶ አደሩን በዓመት አንዴ እልፍ ቢል ሁለቴ ከሚያመርትበት ሁኔታ በማውጣት ዓመቱን በሙሉ አምራች አድርጎታል። የመኸር አዝመራ ስብስቦ እስከ ሌላው የመኸር ወቅት መጀመሪያ መጠበቅ መቅረት ጀምሯል። አዝመራ ሰብስቦ ወደ አዲሱ የግብርና ልማት መግባት በብዙዎች ዘንድ ተለ ምዷል።

ሀገሪቱ በመስኖ ሊለማ ከሚችለው መሬቷ የተጠቀመችው ገና ጥቂቱን ነው። 10ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሁን ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታሩን ነው ለስንዴ ልማት ያዋለችው። በመኸርና በበልግ የምርት ዘመን በስንዴ የሚሸፈነው መሬት ስፋትም እየጨመረ መሆኑ ይገኛል፤ በእነዚህ የምርት ወቅቶች በየዓመቱ በስንዴ ልማት እየተሸፈነ ያለው መሬት እየጨመረ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል።

በአጠቃላይ በተለይ በመኸር ወቅት እየጨመረ የመጣው የሚታረስ ማሳ ስፋት ስንዴንም ገና በስፋት ማልማት የሚያስችል አቅም እንዳለም ይጠቁማል። በእዚህ ላይ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ዕድሉ እየሰፋ ነው። ማሳዎች ለእዚህ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ኩታገጠም እርሻ እየተስፋፋ ይገኛል፤ ኩታ ገጠም እስከ አለፈው ዓመት ድረስ ከነበረበት ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር ዘንድሮ ወደ 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል።

መንግሥት ባንኮች ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ማሳሰቡን ተከትሎም ባንኮቹ ለዘርፉ ፋይናንስ በማቅረብ በኩል አጋር መሆን ጀምረዋል። ይህም የዘርፉን የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር ለመፍታት ትልቅ አቅም ጀምሯል ማለት ይቻላል። በትራክተር የማረስ ምጣኔ እየጨመረ ይገኛል። በእዚህም ከሚታረሰው ማሳ አምስት በመቶውን በትራክተር ማረስ ተችሏል፤ ይህ በመንግሥት ቁርጠኛ ውሳኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጣ ለውጥ ነው።

አርሶ አደሮች በግላቸው እየተደራጁ በኅብረት ሥራ ማኅበሮቻቸው በኩል ትራክተርና የሌሎች ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ባለቤት መሆን እየቻሉ ይገኛሉ። በእዚህ ላይ የግሉ ዘርፍ በሜካናይዜሽን አገልግሎት እየተሠማራ ይገኛል። ማሽነሪዎቹ ለሚያስፈልጋቸው ጥገናና የመሳሰሉት ሥራዎች የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን የማሠልጠን የጥገና አገልግሎት የመስጠት አቅም በመገንባት ላይ እየተሠራም ነው። በቅርቡ እንኳን ይህን ሥራ የሚሠሩ ሁለት የሚሆኑ ማዕከላት እውን ተደርገዋል።

የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት መጨመሩን ቀጥሏል፤ መንግሥት የማዳበሪያ ፍላጎትን ለዘለቄታው ለመመለስ የማዳበሪያ ፋብሪካ ወደ መገንባት እንደሚገባ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል። ይህ ሁሉ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረው ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ነው። ቀደም ሲልም አቅም /ፖቴንሻል/ ከመግለጽ የዘለለ ምን ነበረን። በመስኖ ሊለማ የሚችል 10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አላት ከማለት ውጪ ከዚህ መሬት በመስኖ የለማ ብለን ያሳየነው ምርት አልነበረም።

ያለፉት ዓመታት ለግብርና ልማት ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ምቹ ሁኔታዎቹም እመርታዊ ለውጦችን አስመዝግበዋል። በአጠቃላይ የግብርና ልማቱ በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የታየውም ይሄው ነው። አሁን የተፈጠረውን አቅምና ቀድሞም ያለው አቅም ገና ብዙ እመርታዎችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመላክታሉ።

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You