‹‹ የግድቡ ተደራ ዳሪዎች የሀገራቸውን ጥቅም ለማስከበር የሄዱበት መንገድ ማስተማሪያ ሊሆን ይገባል›› – አቶ ፈቅአሕመድ ነጋሽ

– አቶ ፈቅአሕመድ ነጋሽ የዓባይ ግድብ ተደራዳሪና የዓባይ ውሃ ጂኦ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ

አዲስ አበባ፡- በዓባይ ግድብ ዙሪያ ሲደራደሩ የቆዩ አካላት የሀገራቸውን ጥቅም ለማስከበር የሄዱበት መንገድ ተቀምሮ በቀጣይ ማስተማሪያ ሊሆን ይገባል ሲሉ የዓባይ ውሃ ጂኦ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ እና የግድቡ ተደራዳሪ አቶ ፈቅአሕመድ ነጋሽ ተናገሩ።

የግድቡ ተደራዳሪ አቶ ፈቅአሕመድ ነጋሽ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በተለይ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቴክኒክ ሥራው ከፖለቲካ ሥራ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሄድ የሠሩበት ሁኔታ በመልካም ጎን መታየት ያለበት እና ድርድሩ የኢትዮጵያን ጥቅም ባስከበረ መልኩ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።

ግድቡ ከላይ በመንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ክትትል ተደርጓል። የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድም በቅርበት ሲከታተል ቆይቷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግድቡ ጎን መቆሙ በዓባይ ውሃ ላይ ለሚደራደሩት አካላት ትልቅ ግብዓት እንደሆነ ገልጸው፤ ከተቋማቱ በተጨማሪ ሕዝቡ በራሱ ትልቅ አቅም ስለሆነ፤ ግድቡ ለዚህ መብቃት ችሏል ሲሉ ለድርድሩም ሆነ ለግድቡ መጠናቀቅ የብዙዎች ሚና መኖሩንም አሳውቀዋል።

በዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ዙሪያ በማተኮር የድርድሩ አካሄድ እና ፈታኝ ሁኔታዎችን በመሻገር የሚደራደሩት አካላት የሀገራቸውን ጥቅም ለማስከበር የሔዱበት መንገድ ተቀምሮ በቀጣይ ማስተማሪያ ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡

‹‹ስህተቶች አልነበሩም፤ ችግር አልተፈጠረም ማለት አይደለም፡፡›› ያሉት የዓባይ ግድቡ ተደራዳሪ አቶ ፈቅአሕመድ ነጋሽ፤ ስህተቶች ሲያጋጥሙ ወዲያው የመፍትሔ ርምጃዎች መወሰዳቸው መልካም ውጤት ማምጣቱን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል በቀጣይ የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት አጠቃቀም ጉዳይ ያነሱት አቶ ፈቅአሕመድ ፤ በኢትዮጵያ ያለው የውሃ መጠን በቂ አለመሆኑን አብራርተዋል። በተወሰኑ ተፋሰሶች ከባሮ አኮቦ፣ ከዓባይ እና ከኦሞ እንዲሁም ከጊቤ አካባቢ ውጪ ሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የውሃ እጥረት እንዳለባቸው ልብ ማለት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ይህንን በመረዳት የኢትዮጵያ የውሃ አጠቃቀም በጥንቃቄ እና በቁጠባ መሆን አለበት። ሥራዎች በሙሉ የአካባቢ ጥበቃን መሠረት ያደረጉ፤ የውሃ ምንጮችን መንከባከብ ላይ የተመሠረቱ እና የተቀናጀ አሠራርን የተከተሉ ሊሆኑ እንደሚገባም ገልፀዋል።

አቶ ፈቅአሕመድ ጨምረውም፤ ግድቦች ወደ ፊት የሚገነቡበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ቶሎ ወደ ውሳኔ መግባት እንደሚገባም አመልክተው፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውሃ ተጠቃሚ ካልሆነ፤ በቀጣይም ሕዝባዊ ንቅናቄ ማምጣት ላይ ችግር ስለሚፈጥር ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል።

በፌዴራል ደረጃ በክልል እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የውሃ ዋስትና የሚረጋገጥበት ሁኔታ ከተፈጠረ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You