“የምንፈልገውን ለማሳካት እንደ አሁኑ ጊዜ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ወቅት አላየሁም ” – አምባሳደር ጥሩነህ

– አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ

የዛሬው ቀን ታላቅ ነው። ግንባታው ተጠናቆ ም ረቃው ሊካሄድ እየተጠበቀ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 14ኛ ዓመት እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ/ዶ/ር/ የሚመራው የለውጥ መንግሥት ስልጣን የያዘበት ሰባተኛ ዓመት የሚከበርበት ቀን ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወጪ በመገንባት ዳር አድርሰውታል። ግድባቸው ኃይል ማመንጨትም ጀምሯል፤ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ተሻግረው፣ ከአፋቸው ከፍለው የገነቡት ይህ ግድብ የዚህ ትውልድ ዓድዋ ለመባል በቅቷል።

ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ሀገራቸውን ከቅኝ ገዥዎች ጠብቀዋል፤ ይህ በብዙ መስዋእትነት ያስመዘገቡት ድል ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸው ሀገራቸውን ከወራሪዎች ለመጠበቅ ትልቅ አቅም አርገው ሲጠቀሙበት ኖረዋል።

አንድ ይጠበቅባቸው የነበረው ይህን ሉአላዊነትን ከውጭ ኃይሎች የማስጠበቅ ድል ሀገሪቱን በኢኮኖሚውም የበላይነቷን እንዲጠበቅ በማድረግ መደገም እንዳለበት ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል። ከዓድዋ በኋላ የመጡት ትውልዶች የዓድዋን ድል በኢኮኖሚው መስክ ለመድገም ይህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመገንባት አሀዱ ብለው ጀምረዋል። ይህ እንደ ፖለቲካው ዘርፍ ሁሉ በኢኮኖሚውም ዘርፍ ነጻነትን ለመጎናጸፍ የሚደረግ ርብርብ በምን መልኩ መከናወን ይኖርበታል?

ባለፉት 40 ዓመታት ለአገራቸው በዲፕሎማሲው፣ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው መስክ መስራታቸውን የገለፁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፣ የአሁኑ ትውልድ በተልካሻ ፕሮፖጋንዳ ባለመሸነፍ፣ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለበት ለይቶ በማወቅ አገርን፣ ሕዝብን አስቀድሞ መጓዝ ይኖርበታል ሲሉ ያስገንዝባሉ።

አምባሳደሩ እንደሚያብራሩት፤ የአገር ነፃነት የፖለቲካ ነፃነት ከሌለ የኢኮኖሚ ነፃነት ሊኖር አይችልም። የኢኮኖሚ ነፃነት ከሌለ ደግሞ የፖለቲካ ነፃነት ሙሉ ሊሆን አይችልም። ሁለቱ የተቆራኙ ናቸው። አንድ ሕዝብ ሙሉ ነፃነቱን ለማግኘት በመጀመሪያ የፖለቲካ ነፃነት ሊኖረው ከዚያም የኢኮኖሚ ነፃነት ሊኖረው ይገባል። ይሀ ካልሆን ነፃነቱ ሙሉ አይሆንም።

የአባቶች የፖለቲካ ነፃነት ባይኖር ኖሮ አሁን ያለው ስነልቦና በኢትዮጵያውያኖች ዘንድ ይኖራል ብሎ መገመት አዳጋች ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ ያን ጊዜ በአሸናፊነት ስለተወጣች፤ አሸናፊ ሆና ስለተገኘች በሌሎችም ዘንድ በአፍሪካ ያልተደረገውን አውሮፓውያንን የማሸነፍ እድል ኢትዮጵያ ፈፅማለች የሚለው እየተንከባለለ በልጆቹ፤ በአሁኑ ትውልድ ደርሷል ሲሉ ያብራራሉ።

ትውልዱ በዚህም የተነሳ ራሱን የሚመለከትበት ሁኔታ እንዳለው ጠቅሰው፣ ለማድረግም ለማሸነፍም እችላለሁ የሚል ስነልቦናም አለው ይላሉ። በዚያን ዘመን በሚገባ የታጠቀ አፍሪካን በሙሉ ለመቀራመት የተነሳ የነጭ ኃይል ማሸነፍ ከተቻለ አሁን ደግሞ ያጋጠመውን የኢኮኖሚ ችግር ሊወጣ እና ልታገል፤ ላስወግድ እችላለሁ የሚለውን ሕሊና ይዞ ነው የሚነሳው ብለዋል።

የዓባይ ግድብ በብዙ ውጣውረድ፣ በምዕራባውያንና በሌሎች የተለያዩ ኃይሎች ከየአቅጣጫው የተደረገበትን ከፍተኛ ጫና አሸንፎ እውን የሆነ ነው። ግድቡ የኢኮኖሚና የፖለቲካ እርዳታ ከማንም ወገን ሳይገኝ ኢትዮጵያውያን ሲመኙት የነበረውን አንዳንዶች ደግሞ ማድረግ አይቻልም ብለው የገመቱትን መፈፀም የተቻለበት ነው።

አምባሳደሩ እንዳሉት፤ የዓባይ ግድብ ታላቅ ድል ነው። የዓድዋ ድል በጥቂት ወራት ውስጥ የተፈፀመ ሲሆን፣ የዓባይ ግድብ ግን በረዥም ጊዜ ከፍተኛ ትግልን የጠየቀ በመሆኑ ከዓድዋ ጋር ቢነፃፃር የሚጎለው አይደለም።

በኢትዮጵያውያን መካከል ጎልቶ የሚታይ አንድ ትልቅ ነገር አለ። ኢትዮጵያውያን እርስበርስ የሚጋጩበት፣ የማይግባቡበት አጋጣሚ አለ። የውጭ ኃይል በሚመጣበት እንዲሁም ግፊቱ ከውጪ በሚሆንበት ጊዜ ግን በአንድ ላይ ይሰባሰባሉ። አንድ ላይ ተሰባስበው ስለአገራቸው ነፃነት፤ ስለፖለቲካው ሁኔታ እልሀ አስጨራሽ ትግል ያደርጋሉ። በዓድዋም ይህን አድርገዋል።

ከሀገሪቱ ሁሉም አቅጣጫ ተውጣጥተው፣ በሺህ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር በእግራቸው ተጉዘው፣ የመሳሪያ ኃይል በሌለበት፣ ያለበቂ ስንቅ ተጉዘው በጣም የተደራጀውን በቂ ስንቅ ይዞ የመጣውን ጣልያንን ሰራዊት አሸንፈው ወደመጣበት በመመለስ ነፃነታቸውንም አረጋግጠዋል። በዚህም ሀገራቸውን የመጀመሪያዋና በቅኝ ግዛት ተገዝታ የማታውቅ አገር እንድትባል ማድረግ ችለዋል።

ይህ የቀድምቶቹ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ነው። የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በብዙ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ፣ ምዕራባውያንና ግድቡ እውን እንዳይሆን ጥረት ሲያደርጉ የኖሩ ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል የማይፈልጉ ኃይላት ተጣምረው የሸረቡትን ሴራ ሁሉ በጣጥሶ ጥሎ ግድቡን እውን አርገዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዓባይ ግድብ ካጠናቀቀች በዓድዋ በቀደምት አባቶች ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም የነፃነት ተምሳሌት እንደሆነች ሁሉ በኢኮኖሚ ነፃነቱም ምሳሌ ትሆናለች።

የእኛን የበላይነትን በማውረድ ረገድ የተለመደውን ሚናዋን ትጫወታለች በሚል ግድቡን እንዳትፈፅመው የተረባረቡባት ብዙ ኃይላት ናቸው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የውጭ ኃይል አንድ ላይ ሆኖ ኢትዮጵያን ለመጉዳት በሚመጣበት ጊዜ እንደሚያደርጉት ሁኑ በአንድነት ተነስተው አንድነታቸውን አሳይተው ይሄንን ነገር ለመፈፀም ችለዋል። ከውጭ ርዳታ ሳይኖር፣ ያለውን ሀብት በማዋጣት፣ በመስጠት መንግሥትን በማበረታታት፣ መንግሥት ጎን በመቆም የዓባይ ግድብ ግንባታን እውን አድርገዋል።

በዓድዋ ድል ጊዜ ኢትዮጵያውያንን ለድል ያበቃቸው የነበራቸው አንድነት እንደሆነ ሁሉ፤ በዓባይ ግድብ ጊዜም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን ያሳዩት አንድነት አሁን ለተደረሰው የዓባይ ግድብ የመጨረሻው ፍፃሜ ደረጃ አብቅቷቸዋል።

የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ለሌላ አልበገርም ባይነት ነው። ከዚህ አኳያ ሲታይ ሁለቱም ክስተቶች የኢትዮጵያውያንን ስነልቦና ሁኔታ የሚያሳዩ እና በውጭ ጠላት በሚመጣበት ጊዜ በአንድነት እንደሚቆሙ የሚያረጋግጥ በመሆኑ በዚህ ረገድ የዓድዋ ድል በጣም ከፍተኛ ተጋድሎ የተደረሰበት ነው። የዓባይ ግደብም ከዚህ ያነሰ አይደለም። ትግሉ ትልቅ ነው ግን በዚህ መሃል ትልቅ ሚና የተጫወተው የኢትዮጵያውያን አንድነት ነው።

ትውልዱ አሁን የተጀመረውን የኢኮኖሚ ነፃነት እንቅስቃሴ በምን መልኩ ማስቀጠል አለበት?

አንድና አንድ ትልቁ ነገር ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ማጠናከር እንዲሁም በአንድነት መቆም አለባቸው፤ የሚጠበቅባቸው ለአንድ ዓላማ በአንድነት መቆም ነው። ትውልዱ ያንን አሳይቷል።

ለወደፊትም የሚጠብቀን ብዙ ይሆናል። ኢትዮጵያ የተጠራቀሙ በብዙ ኃይላት ግፊት የተከማቹባት ችግሮች አሉባት። የባሕር በር የማጣት ዓይነት ሁኔታዎች እና የመሳሰሉት አይነት ችግሮች።

130 ሚሊየን ሕዝብ ይዛ አሁን ባለችበት ደረጃ ላይ መገኘት እንደሌለባት ወጣቱ ትውልድ በውል መገንዘብ እንደሚኖርባትም አመልክተዋል።

የባሕር በር የማጣት፣ የኢኮኖሚው ድክመትና የመሳሰሉት ጉዳዮች አሁን በወጣቱ ፊት ተደቅነው እንደሚታዩ ተናግረው፣ ወጣቱ ይሄን ይዞ መቆየት እንደማይችልና ማስወገድ እንደሚኖርበርት አስገንዝበዋል።

‹‹ኢትዮጵያውያን ለመድረስ የምንመኘው ከፍታ አለ፤ እዚህ ከፍታ ላይ መድረስ አለብን›› ያሉት አምባሳደሩ፣ በዓድዋ አሸንፈናል፤ አሁንም በዓባይ ግድብ እያሸነፍን ነው ለወደፊትም በዚሁ መቀጠል አለብን ብለዋል። ስነልቦና ይዘን ወደ ምኞታችን ከፍታ ለመድረስ አሁንም ትግል አለ። የባሕር በር መልሶ የማግኘት ትግል አለ። በአካባቢያዊ አውራ ሆኖ የመገኘት ትግል አለ ሲሉ አስገንዝበዋል።

እነዚህን ይዞ ለመውጣት አሁን ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቁመው፣ ወጣቱ በብዛት የተነሳሳበት ሁኔታ እንዲሁም ወጣት መሪዎች በሥልጣን ላይ እንደሚገኙም አመላክተዋል። መሪዎች በድፍረትና በስልት ወደፊት ሕዝቡን እየመሩ ያለበት ሁኔታ ይታያል ሲሉም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳስገነዘቡት፤ ትውልዱ የዓድዋን እና የዓባይን ግደብ ድል በመጠቀም፤ አሁን ያለውን ምቹ ሁኔታ ስንቅ በማድረግ የሚቀጥለውንም ድል ለመጎናፀፍ መጓዝ አለበት። ሀገሪቱን ወዳለመችው ከፍታ ለመድረስ ወጣቱ ይሄን ይጠበቅበታል፤ ይሄንን ማድረግም ይቻላል። የአሁኑ ወጣት ትውልድ አባቶቹ ያደረጉትን ለመድገም እንደሚያቅተውም አመልክተዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አምባሳደር ጥሩነህ ዜና መንግሥት እና ትውልዱ አሁን የተያዘውን ዓይነት የኢኮኖሚ ነፃነትን እውን የማድረግ ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል። አሁን የተያዘው መንገድ ይበል እንደሚያሰኝ ተናግረው፣ ለእዚህ ደግሞ ወጣቱ የበለጠ መተባበር፣ አንድነቱን ማጠናከር እንዲሁም ከውዥንብር ራሱን ማላቀቅ አለበት ብለዋል።

በዚህ ወቅት ወጣቱ ብዙ እውቀት የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉበት፤ ብዙ ውዥንብር ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ ማህበራዊ ሚዲያው፣ ፕሮፖጋንዳው፣ በትምህርት ዘርፉ የታየው ድክመት ሁሉ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳርፉበት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ወጣቱ ስለ ሀገር፣ ስለሕዝብ ኢትዮጵያ ስለነበረችበት ሁኔታ፣ ወዴት መድረስ እንዳለባት በትምህርቱ መስክም በጣም ጠበቅ ያለ እውቀት ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ከአሁኑ የተሻለ ሊሰራ ይችል እንደነበር አስባለሁ ሲሉም አመልክተዋል።

ያንን ድክመት አስወግዶ የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ትውልዱ መወጣት እንዳለበት አስታውቀው፣ ይህ ኃላፊነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሕዝብም ጭምር እንደሆነም አመላክተዋል። ‹‹ይህ ጉዳይ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ይመለከተናል። ምሳሌ ነበርንና አሁንም ምሳሌ ሆነን መቀጠል አለብን›› ሲሉም ገልጸው፣ ሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ኢትዮጵያ ምን እየሰራች ነው? በማለት እንደሚመለከቱም ተናግረዋል።

ያ የመሪነት እና የምሳሌነት ቦታ እንዳይታጣ ማድረግ በተለይ የወጣቱ ኃላፊነት መሆኑንም ጠቅሰው፣ ወጣቱ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለበት ለይቶ በማወቅ፤ በተልካሻ ፕሮፖጋንዳ ባለመሸነፍ፣ ሀገርን፣ ሕዝብን አስቀድሞ መጓዝ ይኖርበታል ብለዋል።

በመንግሥት በኩልም ወጣቱ ይህን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ያስቻለ ስልት እንዳለ ጠቅሰው፣ ለእዚህ ታላቅ ዓላማ ማስተባበሩና ማሰባሰቡ አሁንም ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ሁልጊዜ አደጋ ውስጥ የምትገባው፣ ጠላቶችም የሚነሱባት ስትከፋፈል፣ ስትዳከም ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ ይሄንን ማስወገድ ከተቻለ፤ አንድነቱ ከተጠናከረ የምናስበው ከፍታ ላይ መድረስ እንደሚቻል ገልጸዋል። አሁን ኢኮኖሚው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ለኢትዮጵያ ጥሩ የማይመኙ ወገኖች ኢትዮጵያ ወደምትመኘው ከፍታ እንድትወጣ ሁኔታዎችን ከማጨለም ወጥተው ወደ ማመቻቸት የሚሻገሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ሲሉም ጠቁመዋል።

መንግሥት በዚህ ረገድ በመጀመሪያ በሀገር ውስጥ የሚታየውን አንድነት የበለጠ ማጠናከር አለበት ሲሉም አመልክተው፣ በአሁኑ ጊዜ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ለማምጣት ብዙ መስራት እንደሚገባም አስታውቀዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በተለያዩ አካላት ዘንድ ኃያል የመሆን ምኞት እንዳለም ጠቅሰው፣ እኔ የአካባቢው መሬት አውራ መሆን አለብኝ የሚሉ ሀሳቦች እንዳሉ አመልክተዋል። በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ በታሪክ እዚህ አካባቢ ነበርኩ፤ ተመልሼ መውጣት አለብኝ የሚሉ ፍላጎቶች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል። ከዚህ ውስብስብ ሁኔታ አኳያ መዘጋጀት አንደሚያስፈልግም አመላከተዋል።

ኢትዮጵያ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ እና በቀይ ባሕር አካባቢ የቆየ ታሪካዊ ሚና እንደነበራትም አስታውሰው፣ ይህ ሚና አሁንም የግድ ሊኖራት እንደሚገባ አመልክተዋል። ለዚህም መንግሥት በኢኮኖሚና በወታደራዊ አቅም ተጠናክራ መውጣት እንዳለበት ገልጸዋል። ሕዝቡን በማስተባበር ያልተገደበ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ሌላው የመንግሥት ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አምባሳደሩ “ኢትዮጵያ ከታሪክም እንደተረዳሁትም ሆነ በቅርቡ እንዳነበብኩት፣ በመንግሥት ኃላፊነትም ወደ 40 ዓመታት ያህል በቅርበት ሳገለግል እንዳየሁት፤ በሀገሪቱ አሁን ምቹ ሁኔታ ይታያል›› ብለዋል። ፊት የነበሩት፣ ለሌላው ምንም እድል የማይሰጡት ሁኔታዎች በአሁኑ ጊዜ እንደሌሉም አመልክተው፣ ኃያላን አገራትም ቢሆኑ እርስበርስ የነበራቸው በጣም ዝግና ለሌሎች ምንም እድል የማይሰጡ ሁኔታዎች አሁን እንደሌሉም ተናግረዋል። በመካከላቸው የተፈጠረው የኢኮኖሚ ክፍተትም እንዲሁ ያንን የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ማዳከሙንም ገልጸዋል። ይህ አጠቃላይ ሁኔታም እኛ ድክመታችንን አስወግደን፣ ወደ ምንመኘው ከፍታ ለመውጣት ጠንክረን ከሰራን ያሰብነው ከፍታ እንደምንደርስ ያመላከታል ብለዋል።

አምባሳደር ጥሩነህ እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ አሁን 130 ሚሊየን ያህል ሕዝብ አለ። ምንም ሳይኖረን ነፃነታችንን በመጠበቅ፣ ኢኮኖሚያችንን በማጠናከር፣ ለሌላው ጫና ባለመበገር የመጣነው መንገድ ያስተማረን፣ በጥሩ ስነልቦና ላይ ያስቀመጠን ሁኔታ አለ ሲሉ አስታውቀው፣ ‹‹ይህን ሁሉ ይዘን ወደ ፊት ለመሄድ እንደ አሁኑ ጊዜ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ወቅት አላየሁም” ሲሉ አስገንዝበዋል። በመሆኑም ጠንክሮ መስራት የመንግሥትም የትውልዱም ኃላፊነት ነው ሲሉ አመላከተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You