
ከአዲስ አበባ – አሶሳ – ጉባ 900 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ በእያንዳንዱ ሰው ልብ እና አእምሮ ውስጥ ታትሞ የሚገኝ የሜጋ ፕሮጀክታችን አንዱ የሆነው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገኛ ነው።
ሁሉም ዜጋ ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከተማረው እስካልተማረው፣ ከሀብታም እስከ ደሀ አይኑንና ቀልቡን የሚጥልበት ልዩ ሥፍራ ነው።
የሕዳሴ ግድብ ቀን ከሌሊት የደከምንበት፤ ከጉሮሯችን ነጥቀን የገነባነው፤ የልፋታችን፣ የአንድነታችንና የጀግንነታችን መገለጫ ነው፤ ለዚህ ትውልድ ደግሞ በብዙ ምጥ የተገኘ የበኩር ልጅ ነው።
ይህ ንብረትነቱ የኢትዮጵያውያን የሆነው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የግንባታው የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነው፣ የዛሬ 14 ዓመት የምስራቹ ሲበሰር እያንዳንዱ ዜጋ እንገነባዋለን፣ እንሰራዋለን ብሎ የግንባታውን ኃላፊነት ወደ ትከሻው ያወጣው በታላቅ ደስታን ጀግንነት በተሞላው ስሜት ነበር።
የሕዳሴ ግድቡ ዛሬ ላይ የደረሰበት ደረጃ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ዛሬ 98 በመቶ ሥራው ተጠናቆ ለፍጻሜ የደረሰው በመንግሥት በኩል በነበረው ከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት ነው።
የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ማነቆው እጅግ ብዙ እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል፤ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ የተገኘ ድል የተመዘገበም ውጤት አይደለም።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን እንዳታጠናቅቅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ብዙዎች ደክመዋል። በሚችሉትም ሆነ በማይችሉት መንገድ እንቅፋት ለመሆን ጥረት አድርገዋል፤ ተሟሙተዋል። ሆኖም ድካም እንጂ አንዱንም ያሰቡትን አላሳኩም፤ ለፉ እንጂ አንድም ከዓላማችን ዘነፍ አላደረጉንም።
«ሚስማር አናት አናቱን ሲመታ ይጠብቃል» እንዲሉት ብሂል በተለያየ አቅጣጫ የተለያየ አጀንዳ እየፈጠሩ ግንባታውን ለማደናቀፍ ጥረት ቢያደርጉም የግንባታ ዘመኑ ጊዜ ሲረዝም ወጪው እየጨመረ ሲሄድ ተሰላችተው፣ አቅም አጥተው በሌላ ሌላ ምክንያትም ይስተጓጎላል ብለው ቢያስቡም አልተሳካላቸውም።
እስከ ተባበሩት መንግሥታት ምክር ቤት የሚደርስ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አድርገው የሴራ ጥንስስ ቢጠነሰስም አልተሳካላቸውም። የአሸናፊነትን ጉሽ መጎንጨት አልቻሉም። ሀገራችን የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ይዛ የራሷን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ረጅም ርቀት ተጉዛለች፤ በጉዙዋም ስኬታማ መሆን ችላለች።
ለፍትሀዊ ተጠቀዋሚነት መርሕ በአብዛኛው በግብፅና በሱዳን ብርቱ ፈተናዎች አጋጥሟታል። ለጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጋራ ትብብርና ድጋፍ ማድረግ እንጂ እንቅፋት መሆን አያስፈልግም ነበር፤ ትብብሩ ሳይሆን ወደፊት የቀደመው ለማጨናገፍ መውተርተር ነበር።
ከመነሻው ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት የልማት ሀሳብ እንዳይኖራት ለዘመናት ስትባዝን የኖረች ግብፅ፣ የሕዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ በኢትዮጵያ ላይ የማስፈራሪያና የማስጠንቀቂያ ብዛት ስታዘንብ ከርማለች።
ከማስፈራራትና ከድንፋታ በኋላ ወደኋዋላ የሚል መንግሥትም ሆነ ሕዝብ እንደሌለ ስትረዳ አቅጣጫዋን ያደረገችው ከጎኔ ይቆማሉ ብላ ያሰባቻቸውን ሀገራት ማስተባበር ነበር። አድማ እንዲመቱ የክፋት ሀሳቧን ወደፊት በማራመድ ጫና እንዲያሳድሩና የባለቤትነት መብት እንዲያረጋግጡላት በብዙ ሰርታለች።
86 በመቶ የውሀው ሀብቱ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ መብቷን ጥላ የገዛ ሀብቷን ለመጠቀም ግብጽን ይሁንታ ፍለጋ እንድትዳክር ቅዠት ጭምር ያለበትን ሀሳብ ከዚህና ከዚያ አራምዳለች። ኢትዮጵያ ግን በየትኛውም አቅጣጫ የሚነሳውን ዛቻ እንዲሁም የትኛውም ሀሳብና ጫና ከአቋሟ ዝንፍ ሳትል ግንባታዋን ሌት ተቀን ስታስኬደው ከርማለች።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ያጋጠማት ፈተና በርከት ያለ ከመሆኑም በላይ በየምክንያቱ ብዙ ነገሮችን እንድታጣ ተደርጋለች። በአንድም ሆነ በሌላ ኢኮኖሚዋ እንዲዋዥቅ በብዙ ተጥሯል። በሕዝቦች መካከከል ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ሰፋፊ ጥረቶችም የዚሁ እውነታ አካል ነበሩ፤ ዛሬም ናቸው።
ግብፅ የሕዳሴ ግድቡን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ለ13 ጊዜ በማመላለስ ኢትዮጵያ በብዙ ጫና ውስጥ እንድታልፍ ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች። ስለ ዓባይ ግድብ ምንም የማያገባው የዓረብ ሊግም በጉዳዩ ላይ መግለጫ እስከማውጣት ደርሶ ነበር። የቅኝ ግዛት ስምምነት ላይ ተጣብቃ አልላቀቅም ያለችው የግብፅ ጩኸትም ሆነ የተለያዩ የተቃውሞ ስልቶች አላተረፋትም።
የአቋም መዋዠቅ ውስጥ ሆና ወዲህ ወዲያ የምትለው የሱዳን ሁኔታም ኢትዮጵያን ከሥራዋ ለአፍታም ቢሆን አላስቆማትም። ይልቁኑ ከጥቂት ወራት በኋላ ኢትዮጵያውያኑ እንደ አካላቸው ክፋይ የሚያዩት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፍጻሜውን ያገኛል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ብዙና ልዩ ነው። ለኢትዮጵያውያን እራትም መብራትም ሆኖ ይጠቅማል። ለጎረቤት ሀገሮች ኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥም ኢኮኖሚያችንን የምናሳድግበት አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶዋችን ነው።
በማሕበራዊ አገልግሎቱ በሥራ እድል በመፍጠር፣ በአሳ እርባታ በመስኖና በሌሎችም የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው። እንዲሁም ፖለቲካል አንደምታ የእንችላለን ትርጉሙ ከምንም በላይ የድል ባለቤት የሚያደርገን ነው። ትልቅ የአሸናፊነት የድል አድራጊነት ምልክት ነው።
ዛሬ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርከት ያሉ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ለፍጻሜው መድረሱ ከምንም በላይ ትልቅ ስኬት ነው። የሁሉም ዜጋ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሚኮሩበት የአሻራቸው ውጤት ከዓድዋ ቀጥሎ የምንኮራበት ታሪካችን ነው።
በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻልና ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር አስተዋፅዖው ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያውያኑ ጥንካሬ የተገነባው እና ሊጠናቀቅ ጫፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ሀገሪቷ ልታድግ የምትችልበትን፣ ምርታማነት የሚጨምርበትን፣ በከፍተኛ ደረጃ የሥራ ዕድል የሚከፈትበትንም ዕድል የሚፈጠር ነው።
የሕዝቡ ኑሮ ማሻሻል የሚቻለው አንድም የሥራ እድልን በመፍጠር ነው። ሕዝብ የሥራ እድል ተፈጥሮለት የሚሠራ ከሆነ የገቢ ምንጭ ይገኛል። ገቢን ከፍ ለማድረግ ዋነኛው መሠረት የሆነው ምርታማነትን መጨመር እና ማበራከት ነው። በሁሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች በአገልግሎት መስጫ፣ በኢንዱስትሪ እና በግብርናው ዘርፍ ላይ ሁሉ የኤሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው።
ሁሉም ዘርፎች ኤሌክትሪክ አግኝተው ውጤታማ እንዲሆኑ ቀጣይነት እንዲኖራቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ከፍ ያለ ፋይዳ አለው። ከዚህ ጎን ለጎን ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት መቻል ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸውን የምርት አይነቶች በተገቢው መንገድ ማምረት እንዲችሉ ያደርጋል ።
በየኢንዱስትሪው እና በየፋብሪካው ያሉ ማሽኖች የሚጠቀሙት ኤሌክትሪክ ኃይል ነው። ስለዚህ ፋብሪካዎች አዳዲስ የሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች በቂና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ይኖራቸዋል፤ በእዛው ልክ ምርታማነት ያድጋል፤ የውስጥም የውጪም ኢንቨስትመንት ይስፋፋል ለዜጋውም የሥራ ዕድል የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጠራል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ኤክስፖርት ምርቶች ያድጋል። ሀገሪቱም የውጭ ምንዛሪ ገቢ ታገኛለች።
እንዲሁም በሚፈጠሩ የሥራ እድሎች ሥራ አጥነት ቀንሶ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያድጋል፤ ይመነደጋል። ይህም ተምረው ሥራ አጥተው የተቀመጡ ዜጎችን ወደ ሥራው መስክ እንዲሳቡ የሚያደርግ ይሆናል፣ በርካቶች በሥራ ላይ ሲሰማሩ በሀገር ውስጥ የሚሰበሰብ ገቢ ያድጋል።
የግለሰብ ገቢ ሲያድግ የራሱን ገቢ ከማሻሻል አልፎ በሀገር ደረጃ የመንግሥት ገቢ ከፍ ለማድረግ የራሱ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ወደ ውጪ ሀገር የሚሰደዱ የተማሩ ሆኑ ያልተማሩት በሀገር ውስጥ ሥራ ላይ በመሰማራት የገቢ አቅሙም እያደገ ይሄዳል። ሀገሪቱ ታክስ ሰብሳቢ ትሆናለች።
ይሄ ደግሞ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት የዜጎችን ጤና በመጠበቅ፣ ትምህርትን በጥራት በማስፋፋት፣ ቱሪዝምን ግብርናን እንዲሁም በሌሎች ጭምር ሕብረተሰቡ የተጠቃሚነት መጠን እያደገና ጥራቱንም እያረጋገጠ የሚሄድ ይሆናል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በዓመት በአማካይ 15 ሺ 759 ጊጋ ዋት በሰዓት ኢነርጂ በማመንጨት ለሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ትስስር ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያልሆኑ 70 በመቶ የገጠር መንደሮችና ከተሞችንም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይታሰባል።
በአሁኑ ወቅት የግንባታው ፕሮጀክት 98 በመቶ አካባቢ የደረሰ ሲሆን በመጪዎቹ ስድስት ወራት ተመርቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
እስካሁን በነበረው ሁኔታ ሀገራችንን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ሊያላቅቀን ያልቻለው አንዱ ምክንያት በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማጣታችን ነው።
ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል የምንጠቀምባቸው የምርት መገልገያ መሣሪያዎችን ማንቀሳቀስ አንችልም። ፈጥነን በማምረት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ አዳጋች ይሆናል። በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን አሳይተን እና ገበያዎችን ሰብረን ገብተን የምናመርታቸውን እቃዎቻችንን በተሻለ ሁኔታ መሸጥ እና መገበያየት አንችልም። ስለዚህ የግድቡ መጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ነው የምንለው በምክንያት ነው።
የሕዳሴ ግድቡ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ሲታይ የባሕር ትራንስፖርትና የዓሣ ሀብት ልማት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ይታሰባል። እንዲሁም 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሰው ሠራሽ ሀይቅ ስለሚፈጠር በአካባቢው በታንኳ እና በጀልባ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ እንዲሁም በዓለማችንም ተጠቃሽ የቱሪስት መዳረሻም እንደሚሆንም ይታሰባል። በተለይም በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሀይቅ እየሰፋ ሲሄድና ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅም ከ78 በላይ ደሴቶች የሚፈጠሩ በመሆናቸው ይህም ሌላው የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን ይችላል።
ሪዞርቶች የመገንባት፣ ለዓሣ ልማት እና ለመሳሰሉት ኢኮኖሚያዊ አማራጮች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በዓመት እስከ 50 ሺህ ቶን ዓሣ ሊመረትበት እንደሚችል ይታሰባል። ይህም የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ አንዱ ሲሆን ከሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ በተጨማሪም ወደ ጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት እስከማድረግ የደረሰ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
የሕዳሴ ግድቡ እውን እንዳይሆን የሚደረገው ጥረት ሁሉ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እንዳያድግ በማሰብ ነው። ምክንያቱም የግድቡ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍ ያለ ነው። በተለይም እንደ ሀገር የማይቆራረጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ተገኘ ማለት ተከታታይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታን ይፈጠራል።
ኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በዚህ በመጨረሻው ትንቅንቅ ላይ ተሳታፊ ከሆነ ከፍጻሜው የሚገኘውን ትሩፋት ተቋዳሽ ይሆናል ማለት ነው። በአሁኑ ወቅት ትሩፋቱን ልንቋደስ ከጫፍ እንደመድረሳችን ለፍጻሜው የሚሊየኖች አይኖች ሁሉ ወደ ሕዳሴያችን ያማትራሉ።
የመቶ ሚሊየኖች አሻራ ያረፈበት ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ሲመረቅ ለወዳጅ ደስታ ለጠላት ሀዘን ነው። ከደስታው ለመደሰት ከጥቅሙ ለማጋራት የቀረን በጣት የሚቆጠሩ ወራት ናቸው።
ለምርቃቱ ያብቃን ትጋታችን ነው ።
ሰላም
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም