የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ለአምራች ኢንዱስትሪው ብሥራት ነው

አዲስ አበባ፡- የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መጎልበት ወሳኝ ሚና የሚኖረው ስለሆነ ብሥራት ነው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ አስታወቁ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ የመላው ኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የነበረውና ሁሉም በኅብረት የገነባው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቅርቡ የሚጠናቀቅ መሆኑ በተለይ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትልቅ ብሥራት ነው፡፡ ይህም የአምራች ኢንዱስትሪው ቁልፍ ችግር የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የሚፈታ በመሆኑ የዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ያስችላል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው ለሀገር ኢኮኖሚ እድገትም ሆነ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ ሚና ያለው እንደሆነ ገልጸው፤ እስከአሁን አምራች ኢንዱስትሪው ተገማች  የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኝ በመሆኑ ከተማ ውስጥ ያለውን ኃይል ከሌላው ኅብረተሰብ ጋር ለመካፈል ተገዶ መቆየቱን ተናግረዋል። ይህም በመሆኑ በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ችግር ያጋጥም እንደነበር አስታውሰው፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በቅንጅት ሲሠራ መቆየቱን አመልክተዋል።

ይሁንና ኢንዱስትሪው እያደገ ከመምጣትና የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎቱም እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አቅርቦቱ ላይ ውስንነት መኖሩን አስገንዝበዋል።

የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ለኢንዱስትሪዎቻችን ትልቅ ብሥራት እንደሚሆን ተናግረዋል።

‹‹በተለይ አንዳንድ ጊዜ የሚታየውና ለኢንዱስትሪዎቻችን ፈተና ሆኖ የቆየው የኃይል መቆራረጥና የአቅርቦት ችግር በዘላቂነት የሚፈታው ነው የሚሆነው›› ብለዋል፡፡

ሕዳሴ ግድብ ደግሞ የሚያመነጨው ኃይል ከፍተኛ በመሆኑ ለዘርፉ አንቀሳቃሾች ትልቅ ተስፋ እንደሚሆን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ‹‹በተጨማሪም ወደፊት በአነስተኛ ዋጋ ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርብ በመሆኑ፤ የማምረቻ ወጪያቸውን እንዲቀንሱና የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያጐለብቱ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል›› በማለት አስገንዝበዋል።

ከዚህም ባሻገር የግድቡ መጠናቀቅ አሁን ላይ ሥራ ላይ ላሉት ኢንዱስትሪዎች ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ኢንቨስትመንትንም ይዞ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ታረቀኝ አመልክተዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንደሀገር በቀጣይነት የሚሠሩ ሥራዎችንን ይህንን የኃይል አቅርቦት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You