
አዲስ አበባ፡– በታላቁ ረመዳን ወር የነበረንን የመረዳዳት እና መተሳሰብ መልካም ተግባራት ሁልጊዜም ባህል አድርጎ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ገለጹ፡፡ ከፆሙ የምናገኘው ዋጋ ሙሉ እንዲሆን እዝነትን እና መልካምነትን የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርገው እንደሚገባ አመለከቱ ።
ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በረመዳን ወር የሚደረገው መረዳዳትና መተሳሰብ የሚያስደስት ነው፡፡ ፈጣሪ መልካም እንድናደርግ የሚፈልገው በየእለቱ ስለሆነ በታላቁ የረመዳን ወር ስናከናውናቸው የነበሩ መልካም ተግባራትን ባህል አድርገን ልናስቀጥላቸው ይገባል፡፡
ግለሰቦች እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጋ ለመድረስ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ጠቅሰው፤ አንዳንድ ድርጅቶችም የመረዳዳትን መልካም ዕሴት ሲያከናውኑ ተመልክተናል።
ፈጣሪ በረሃባችን የሚያገኘው ነገር የለም፤ የፆም ትልቁ ዓላማ ፈጣሪያችንን እንድንታዘዝና ትዕዛዛትን እንድንፈጽም ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
ይህን መልካምነት ግን በሆነ ጊዜ ብቻ የምከናውነው ሳይሆን የሕይወታችን መርሕ አድርገን ልንተገብረው ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር አሕመድ፤ በዚህ ረመዳን ወርም ሰዎች ለሌሎች ሲያዝኑና ሲደግፉ በስፋት ተስተውሏል፤ የረመዳን ወር የተሰጠን መልካምነትንና ለሌሎች ማሰብን ልምምድ የምናደርግበት ነው፤ በፆም ወቅት መጥፎ ላለማድረግና መልካም ተግባራትን ለማከናወን የነበረንን ተነሳሽነት ማስቀጠል እንደሚጠበቅብንም አመልክተዋል፡፡
የዒድ አልፈጥር በዓልን ስናከብር በፆም ወቅት የነበረንን መረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን ማሰብ አጠናክረን መቀጠል እንደሚያስፈልግ አስታውሰው፤ ከፆሙ የምናገኘው ዋጋ ሙሉ እንዲሆን እዝነትን መልካምነትን የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርገው እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡
አንድ ሺህ446ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል ጨረቃ ስለታየች ትናንት መጋቢት 21 ቀን 2017 በድምቀት መከበሩ ይታወሳል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም