በረመዳን የታየው መደጋገፍ ከዒድ በኋላም ሊቀጥል እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡በረመዳን ወቅትና በዒድ አልአፈጥር በዓል የሚደረገው መደጋገፍ ከበዓሉም በኋላ ተጠና ክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የትምህርትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አልዩ ሰዒድ አሳሰቡ።

ዳይሬክተር አልዩ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በረመዳን ፆም ወቅት በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ ከፍተኛ መደጋገፍና መተባበር ሲደረግ ቆይቷል። በበርካታ ቦታዎችም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የማዕድ ማካፈልና የተለያዩ ድጋፎችን የማድረግ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅትም ለበዓል መዋያ የሚሆኑ ድጋፎች ለአቅመ ደካሞችና ወላጅ አልባ ሕጻናትና አሳዳጊዎቻቸው እየተደረገ ይገኛል።

ይህ የእስልምና መሠረት የሆነ የመደጋገፍና የመተባበር ተግባር ከበዓሉም በኋላ በሚቀጥሉት አስራ አንድ ወራት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያመለከቱት ዳይሬክተር አልዩ፤ ይህ ሃይማኖታዊ አስተምሕሮ በመሆኑ ሁሌም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው። የሰው ልጅ ማኅበራዊ አኗኗርን የሚከተል ፍጡር እንደመሆኑ በደስታም በኃዘንም አብሮነቱን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።

መደጋገፍና መተባበር ያለብን የእለት ምግብ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን በልማቱ በሰላም ግንባታ ባጠቃላይ ከድህነት ለመውጣት በሚደረጉ ጥረቶችም እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ የራሳችን አቅም ያለን በመሆኑ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማትም ጠንክረው መሥራት ይኖርባቸዋል፤ በተለይም ወጣቶች ስደትን በመጸየፍ በሀገራቸው ሠርተው መለወጥን እንዲለምዱ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። በዚህ ረገድ ከወጣቶች ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ሰውን ለመርዳት የግድ ሀብታም መሆን አይጠበቅም የሚሉት ዳይሬክተር አልዩ፤ ከአስተሳሰብና ከምክር ጀምሮ እያንዳንዳችን ልናደርጋቸው የምንችል ድጋፎች አሉ። በዚህ ረገድ አላስፈላጊ አባባሎችን ልንሻገር ይገባል። «ከራስ በላይ ንፋስ» ከሚል የተሳሰተ ብሂልና አስተሳሰብ በመላቀቅ ከእኔ በላይ ሀገርና ሕዝብ አለ የሚል ትውልድ እንዲፈጠር ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተስፋፉ በመጡ ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት የሕዝቡ ማኅበራዊ ስሪት እየፈረሰ ሃይማኖታዊ እሴቱ እየተሸረሸረ ይገኛል። ይህንን የማስቆምና ወደነበረበት የተከበረ ኢትዮጵያዊ ማንነት መመለስ ከሁሉም የሚጠበቅ እንደሆነም አመልክተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You