
-አቶ ዛዲግ አብርሃ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ፡- ቴክኖሎጂ ሁሉም ያለውን አዋጥቶ ሀገሩን የሚያሳድግበት እንጂ እርስ በርስ የሚያበላላ እና ሀገር የሚያፈርስ ሥራ የምንሠራበት እንዳልሆነ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ አስታወቁ፡፡ ኅብረተሰቡ መረጃ ሲደርሰው እውነት ነው ብሎ ከመቀበሉ በፊት ማመዛዘን እና ከዋናዎቹ ሚዲያዎች ማረጋገጥ እንደሚኖርበት አመለከቱ።
አቶ ዛዲግ አብርሃ ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ከሰሞኑ ያስተላለፈውን ሐሰተኛ መረጃ በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳመለከቱት፤ ኅብረተሰቡ መረጃዎች ሲደርሱት ዝም ብሎ ከመቀበል ይልቅ መጠየቅና የመረጃውን ትክክለኝነት ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
የውሸት መረጃ ከእውነት መረጃ ጋር ሲነጻጸር ስድስት እጥፍ ወደ ሰዎች የመዛመት እና የመስፋፋት ባሕሪ እንዳለው ጥናቶችን ጠቅሰው የገለጹት አቶ ዛዲግ፤ ኅብረተሰቡ የሚደርሱትን መረጃዎች ዝም ብሎ ከመቀበል ይልቅ መጠየቅና የመረጃውን ትክክለኝነት ከዋናዎቹ ሚዲያዎች ማረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዘመናት የሰው ልጅ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በሀገር ጉዳይ የሚያደርጋቸው ማኅበራዊ መስተጋብሮች በእርስ በርስ መተማመን ላይ የተመሠረቱ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ማኅበራዊ ችግሮችን የሚፈታ ከመሆን ይልቅ የሚያባብስ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰው ልጅ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር አቅሙ እያደገ መምጣቱን ተናግረው፤ ይህም በኦን ላይን ማስታወቂያና በተለያዩ አማራጮች ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳደረገ ጠቅሰው፤ ይሁንና ሶሻል ሚዲያ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዳለው ሁሉ አሉታዊ ተፅዕኖም የሚፈጥር ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ቴክኖሎጂው እውነት ላይ ያልተመሠረቱና እውነት የሌለው ማኅበረሰብ እንዲፈጠር እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
እውነተኛ መረጃ የሕዝብን እና የሀገርን ዕጣ ፈንታ የሚወስን እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዚያው ልክ እውነተኛ ያልሆነ መረጃም አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ከማኅበራዊ ሚዲያ የሚገኝ መረጃ ችግርን የሚቀርፍ እንጂ ለማኅበረሰብና ለሀገር አደጋ የሚፈጥር እንዳይሆን ኅብረተሰቡ መጠንቀቅ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ሀገራችን ገና ታዳጊና ብዝኃነትን የያዘች፤ የሕዝባችን የትምህርት ደረጃም ገና ያላደገ ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፤ የሚነዙት የሐሰት መረጃዎች ‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› እንዲሉ የሀገራችንን ችግር የሚያወሳስቡ ናቸው ብለዋል፡፡ አባቶቻችን መስዋዕት ከፍለው ያስረከቡንን ነፃ ሀገር ታሪካዊ ጠላቶቻችን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችንን ለሌላ ነገር እንዳያውሉት መጠንቀቅ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ሲተኮስ በማናየው የኢንፎርሜሽን ጦርነት ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ ዛዲግ፤ ሰዎች ለተለያየ ዓላማ ሐሰተኛ መረጃን እንደ አንድ የጦር መሣሪያ እየተጠቀሙት በዜጎች ላይ ትልቅ ጉዳትና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ለማምጣት እንደሚሞከሩ እንዲሁም በሥልጣኔ እና በሰው ልጅ ላይ አደጋ እየፈጠሩ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሶሻል ሚዲያ ጉዳቱ እየጨመረ እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡
የቡርቱካን ጉዳይ በሚዲያ ከተላለፈ በኋላ ያስተላለፈው ሚዲያ ስህተት መሥራቱን አምኖ ይቅርታ ጠይቋል፤ ልጅቱም መሳሳቷን አምናለች፤ ጉዳዩ የልጅቷ መደፈር ከሆነ፤ ጉዳዩ እዚያው ጋር ማብቃት ነበረበት ያሉት አቶ ዛዲግ፤ ማኅበራዊ ሚዲያው ጉዳዩን አሁንም የሚያራግብ መሆኑ ሲታይ ሐሰተኛ መረጃውን ለሌላ ዓላማ መጠቀም እንደተፈለገ ያመላክታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ጽንፍ የያዙ አስተሳሰቦች እንዳሉ ጠቅሰው፤ እነዚህ ሁኔታዎች ባሉበት ማኅበራዊ ሚዲያው ከሜን ስትሪም ሚዲያ ያገኘውን የተሳሳተ መረጃ ማራገቡ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ጋዜጠኞች እንዲህ አይነት ፕሮግራሞች ከማስተ ላለፋቸው በፊት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በራሳቸው የአሠራር ሥርዓት መሠረት ከስህተት የፀዳ ሥራ መሥራት፣ እርስ በርስ መተራረም፤ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር ተቀራርቦ መሥራት እና የተቀመጡ መመሪያና ደንቦችን ማክበር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡
አሁን የዓለም ሀገራት እየተወዳደሩ ያሉት እርስ በርሳቸው ሳይሆን ከቴክኖሎጂ ጋር ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፤ ቴክኖሎጂው በዚህ ፉክክር ሁሉም ያለውን አዋጥቶ ሀገሩን የሚያሳድግበት እንጂ እርስ በርስ የሚያበላላ እና ሀገር የሚያፈርስ ሥራ የምንሠራበት አይደለም ብለዋል፡፡
‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንደሚባለው፤ ሁሉም አካላት ማለትም መንግሥት፣ ሚዲያዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች ማኅበራት፣ ምሑራን ትምህርት ቤቶች ከዚህ ስህተት ልምድ ወስደው ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም