ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንድ ቀን እስኪቀረው ንቅናቄው ይቀጥላል

አዲስ አበባ፡– ታላቁ የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ የልማት ንቅናቄው እንደሚቀጥል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለፀ፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ይህ የተገኘው ትልቅ ዕድል ሁሉም ተረባርቦ ፕሮጀክቱ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ ንቅናቄው ላይ በመሳተፍ ደስታውን ለመካፈል ስጦታውን ማበርከት ይገባዋል።

ኅብረተሰቡ ያወጣው ገንዘብ ትልቅ ቁም ነገር ላይ ውሎ ውጤቱን ሲያየው እጅግ የሚኮራበት ጉዳይ ነው ያሉት ወይዘሮ ፍቅርተ፤ የልማት ንቅናቄ ልክ ዓድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን ያሳዩት አንድነት እና ኅብረት እንዲሁም ሙሉ የሀገር ፍቅር ተነሳሽነት የታየበት እንደሆነ አመል ክተዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የአሁኑ ትውልድ ትልቅ የልማት አርበኝነት እንድንጎናፀፍ ዕድል ሰጥቶናል፤ የይቻላል መንፈስ እና ጀምሮ የመጨረስ ሕልማችንን ዕውን ያደረግንበት ትልቅ ስኬት እንደሆነም፣ አስታውቀዋል ፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በቀጣይ ለብዙ ፕሮጀክቶች ልምድ እና መሠረት የሚሆን ነው፤ የፕሮጀክቱ ክንውን ከጅማሬው አንስቶ አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ እያንዳንዱ የሥራ ሂደት ለታሪክ የሚቀመጥ በርካታ ሠንሠለቶች እና ቀበቶዎች የያዘ ነው ብለዋል፡፡ መጭው አዲስ ዓመት መስከረም ላይ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ተባብረን ሪቫኑን እንቆርጣለን የሚል ተስፋ ይዘን እየሠራን ነው ያሉ ወይዘሮ ፍቅርተ፤ ፕሮጀክቱ ልክ እንደ መጀመሪያው በሞቅታ ተቀጣጥሎ እየቀጠለ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ለአብነት ዛሬ በኦሮሚያ ክልል የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ያዘጋጀው በርካታ ሕዝብ የተሳተፈበት የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች እየተካሄዱ ነው፤ በሁሉም ክልሎች እና በውጭ ሀገር ኤምባሲዎች መሰል ዝግጅቶች ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቁመዋል ፡፡

ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ተጠሪነቱ ለውሃና ኢነርጂ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፤ በየቀኑ የፕሮጀክቱ ሂደት በገንዘብ፣ በሃሳብ እና የዕቅድ ክትትል ከሚገባው በላይ እየተደረገ ነው፤ ይህም ዓባይ የውሃ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢነርጂም ጭምር ስለሆነ በቋሚ ኮሚቴው ሳይቀር የዘወትር ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገለት ነው ብለዋል፡፡

እያንዳንዷ ቀን የፕሮጀክቱ ወጪ ትጠይቃለች ያሉት ወይዘሮ ፍቅርተ፤ በመሆኑም የቦንድ እና የስጦታ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ሚዲያውም ለፕሮጀክቱ ግብዓት የሚሆን መረጃ በማዘጋጀት ኅብረተሰቡ በንቅናቄው እንዲሳተፍ የራሱን አስተዋፅዖ በማድረግ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እንደ ተጀመረው በቃላችን መሠረት ዳር ለማድረስ የግንባታ ሥራው ተጠናቆ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ እና የማስመረቅ ዝግጅት ላይ ይገኛል፤ ያልተሳተፈ የኅብረተሰብ ክፍል ካለ በመሳተፍ የደስታ ተካፋይ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You