
አዲስ አበባ፡- የ1446ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አል ፈጥር በዓል ኢትዮጵያንና ሕዝበ ሙስሊሙን በሚመጥን መልኩ መከበሩን የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ፈትሁዲን ሀጂ ዘይኑ አስታወቁ።
ሼህ ፈትሁዲን ሐጂ የበዓሉን በሰላም መጠናቀቅ አስመልክቶ ባስተላለፉት የደስታ መልዕክት እንዳስታወቁት፤ የረመዳን ፆም ገና ከጅምሩ አብሮነትና አንድነት የታየበት፤ በፍቅር የተሞላ ነበር፤ በተመሳሳይ የዒድ አል ፈጥር በዓልም በፍጹም ሰላም በሚያስደስት ሁኔታ በድምቀት ተከብሯል።
ለዚህ ከፈጣሪ በታች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለተወጡ አካላት ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ ያሉት ሼህ ፈትሁዲን፤ በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ እንዲሁም ሰላም በማስከበር ሥራ የተሳተፉ ወጣቶች ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ሁሉም ነገር የሚያምረው ሰላም ሲኖር በመሐሉ መላው ማኅበረሰብ ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል እንደሚገባ አመልክተው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ምንም የሚጎድልብን ነገር የለም። ሰላማችንን ማስጠበቅ ኅብረታችንን ማጠናከር ከቻልን የምናስባቸውን መልካም ነገሮች ልናሳካ እንደምንችል አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በሰላም ግንባታ ሆነ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት በስፋት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፤ ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደ ከተማ ከአዲስ አበባ ነዋሪ፤ እንደ ሀገር ከመላው ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ይሆናል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገራት መካከል ለማሰለፍ በመንግሥት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፤ እነዚህ ጅምሮች ተጠናቀው የጋራ ሀገራችን እንድትበለፅግ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፤ ይህንን ደግሞ በየእለት ከእለት ሥራችን ልንተገብር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በረመዳን ፆም ወቅት በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ ከፍተኛ መደጋገፍና መተባበር ሲደረግ ታይቷል፤ በበርካታ ቦታዎችም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የማዕድ ማካፈልና የተለያዩ ድጋፎችን ተደርገዋል፤ ይህን በጎ ተግባር በቀጣይ ጊዜያትም ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የእስልምና መሠረት የሆነ የመደጋገፍና የመተባበር ተግባር ከበዓሉም በኋላ በሚቀጥሉት አስራ አንድ ወራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ይህ ሃይማኖታዊ አስተምሕሮ በመሆኑ ሁሌም ትኩረት ተሰጥቶት ሊተገበር የሚገባው እንደሆነም አስታውቀዋል።
ለመደጋገፍ ደግሞ የግድ ሀብታምና ምቹ ሁኔታ ላይ መገኘት አስፈላጊ አይደለም፤ ሁላችንም ባለን አቅም ባለንበት ቦታ ልንሠራው የምንችለው ደግ ነገር ይኖራል፤ ይህንን እያሰብን ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም