
ዜና ሐተታ
በአራቱም አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም የሚወስዱት መንገዶች በዓሉን ለማክበር በሚተሙ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ተሞልተዋል። ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ስንጠጋ እያንዳንዱ መንገድ መግቢያ በአንድ ወገን ሴቶች በሌላ በኩል ወንዶች ተሰልፈው ፍተሻ ያካሂዳሉ። ከውስጥ የሚሠማው የጸሎት ድምፅ የበዓሉን ድባብ ድምቀት ይናገራል።
በስታዲየም አንድ ጎን የጸሎት ሥነሥርዓት ከሚካሄድበት ፊት ለፊት የበዓሉ የክብር ታዳሚዎች በሥርዓት በተሠደሩ ውብ ምንጣፎች ለይ ተቀምጠዋል። ቀሪው ስታዲየም ሙሉውን የየራሳቸውን መስገጃ ይዘው ጸሎት በሚያደርሱ ምዕመናን ጥቅጥቅ ብሎ የተሞላ ሲሆን ቦታው ባይመቻቸውም በርካቶች በሕዝብ መቀመጫዎች ላይ ተቀምጠው ይታያሉ። በየጥቂት ሜትሮች ርቀት ተመሳሳይ ልብስ የለበሱ የሥርዓት አስከባሪዎች ቦታ ከማስተካከል ጀምሮ የበዓሉን ታዳሚ በቅልጥፍና ሲያስተናግዱ ይታያሉ።
ለዓይን ማረፊያ ከሌለው የሕዝብ ጫካ ውስጥ በመግባት አንድን ወጣት እስኪ ምን ተሰማህ ብዬ ስለበዓሉ ላቀረብኩለት ጥያቄ ሲመልስ፤ ኢትዮጵያዊ ብሆንም የምኖረው በሀገረ አሜሪካ ነው። ስሜ ኢማድ አብዱላሂ ይባላል። በአዲስ አበባ የሚከበረው የዒድ አል ፈጥር በዓል ለእኔ ጥሩ ትዝታ ያለው ነው። በአሜሪካን ሀገር በዚህ ደረጃ የማይከበር በመሆኑ የተለየ ጉዳይ ካልገጠመኝ ሁሌም በዓል የማከብረው ሀገር ቤት እየመጣሁ ነው።
የዘንድሮውንም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በደመቀና በሰላማዊ መንገድ እየተከበረ በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል። እዚህ የምመጣው ቤተሰቦቼን ለማግኘት ብቻ አይደለም። እንደዚህ ድምቅ ብሎ በሚከበረው የዒድ አልፈጥር በዓል መታደም ዓመቱን ሙሉ ደስ የሚል ስሜት ስለሚፈጥርብኝም ነው። በፆም ወቅት በመረዳዳትና በመደጋገፍ ረገድ የሚሠሩት ሥራዎችም የየራሳቸው ትዝታ ያላቸው ናቸው። ይህ በዓል ሀገርህን ሕዝብህን ሃይማኖትህን እንድታስብ እንድታስታውስ ትልቅ ዕድል የሚፈጥርልህ ነው።
ሱዳናዊው እድሪስ አደም በበኩሉ፤ ኢትዮጵያንም አዲስ አበባንም በታሪክ እንደምናውቃቸው ሆነው አግኝተናቸዋል ይላል። በዚህ በዓል ላይ ከሙስሊም ወንድሞቼ ጋር እንዲህ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በመቻሌ በጣም ዕድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል። አዲስ አበባ የዒድ አል ፈጥር በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል ሆና አግኝቻታለሁ። የእስልምና ሥርዓትን በአግባቡ የሚከተልና ለሃይማኖቱ የሚታዘዝ ሕዝበ ሙስሊም እንዳለም ለመረዳት ችያለሁ።
ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ ገና አንድ ዓመቴ ነው። የመጣሁትም ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር ነው። በአሁኑ ወቅት በርካታ ሱዳናውያን አዲስ አበባ ውስጥ አለን። እየኖረን ያለነው ሀገራችን ያለን ያህል ሠላም እየተሰማን ነው የሚለው እድሪስ፤ ከዚህ በዓል በፊት በፆም ወቅት በተለያዩ መስጊዶች ተገኝቼ ጸሎት ለማድረስ ችያለሁ። ሁሉም ቦታ ያስተዋልኩት በጣም ደስ የሚልና ሰላማዊ ሁኔታን ነው። ወደ ሀገሬ ስመለስ ስለኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነትና ስለ እስልምና እምነትም ብዙ የምለው ይኖረኛል። ቀሪ ጊዜዬንም እንደ እስካሁን ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ እንደማሳለፍ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል የበዓሉ ድባብ የፈጠረበትን የደስታ ስሜት አጋርቶናል።
በዚህ ቦታ ሳከብር የመጀመሪያዬ ነው ያለን ደግሞ ወጣት ካሊድ አባ ዱራ ነው። ወጣት ካሊድ የበዓሉን አከባበር የፈጠረበትን ስሜት ሲናገር ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄደውን አከባበር በቴሌቪዥን እከታተል ስለነበር ደማቅ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ። እውነትም አሁን በአካል ሳየው በሚጠበቀው ደረጃ ደምቆ በጣም ብዙ ሰው የታደመበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
በመንገድ ላይ ሲደረግ የነበረው ቁጥጥርና የማስተናበር ሥራ ገና ከጅምሩ በዓሉ በሰላም እንደሚጠናቀቅ የሚያረጋግጡ ናቸው። እንደዚህ ዓይነቱ የሰላም በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የተሳተፉ በማስተናበር ሥራ የተሳተፉ ወጣቶች በምድርም ክብርን በሰማይም ዋጋ የሚያገኙ ናቸው። ለመጪው ዓመት በሰላም ካደረሰኝ እኔም ከእነሱ መካከል አንዱ እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ ብሏል።
ለድንገተኛ አደጋ የመጀመሪያ ርዳታ ስትሠጥ ያገኘናት ፋርማሲስት ሀያት ፈድሉ ትባላለች። የኢትዮጵያ ሙስሊም ጤና ባለሙያዎች ማኅበር አባል ናት። እንደዚህ ዓይነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታዳሚዎች በሚገኙባቸው ሁነቶች ለድንገተኛ አደጋ የመጀመሪያ ርዳታ ለመስጠት እንገኛለን። ዘንድሮም በቂ ባለሙያና ቁሳቁስ ይዘን ተገኝናል።
እስካሁን በመገፋፋት ከደረሰ ቀላል ጉዳት በቀር የገጠመን የከፋ ችግር የለም። ይህ በአንድ ወገን ሕዝበ ሙስሊሙ በሚጠበቀው ደረጃ ሥርዓት ይዞ እንዳከበረው የሚያሳየን ሲሆን የሕግ አስከባሪ አካላትና አስተናባሪዎች የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ መሥራታቸውን የሚመሰክር ነው።
በኅብረት የምናከበርው የዒድ አል ፈጥር በዓል ተጠናቀቀ ማለት በዓሉ አለቀ ማለት አይደለም። በየቤቱ በየዘመድ ቤት በየጎረቤቱ የሚካሄዱ ሥርዓቶች ይኖራሉ። በመሆኑም ኅብረተሰቡ በበዓል ወቅት ሊደርሱ ከሚችሉ ድንገተኛ አደጋዎች ራሱን በተለይም፤ ሕጻናት ልጆችንና አረጋውያንን ሊጠብቅ ይገባል ስትል ሙያዊ መልዕክቷንም አስተላልፋለች።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም