ማዕከሉ በእንስሳት ልማት ዘርፍ የሚፈልገውን ባለሙያ ማፍራት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፦ የወተት ልማት ማሠልጠኛ ማዕከሉ እንደ ሀገር የእንስሳት ልማት ዘርፉ የሚፈልገውን ባለሙያ ማፍራት የሚያስችል መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስትሩ ብሔራዊ ሁለገብ የወተት ልማት ማሠልጠኛ ማዕከል ለመገንባት በሆለታ ከተማ የመሠረተ ድንጋይ ትናንት አኖሩ።

በወቅቱ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ 20ሺሀ እንስሳት አዳቃይ ባለሙያ የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ያሉት ከአምስት ሺህ አይበልጡም። በኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ መንገድ የእንስሳት ማዳቀል ሥራ ሲጀመር በዓመት 500 ሺህ እንስሳት ብቻ ነበር የሚዳቀሉት። ይህም በጣም ዝቅተኛ የሚባል ነው። ይህም የማዕከሉን አስፈላጊነት አጎልቶ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የሰው ሠራሽ ማዳቀል ሥራ ለመሥራት ፈሳሽ ናይትሮጂን እና ዝርያዎችን ለማዘጋጀት ያሉት ማዕከላት አናሳ መሆናቸው ለሥራው መዳከም የመጀመሪያው ምክንያት ነው ሲሉ ገልጸዋል ።

ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ በያዝነው ዓመት 10 የፈሳሽ ናይትሮጂን ማዕከላት እንዲገዙ ሥራዎች ተሠርተው ግማሹ ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀሪዎቹ በቀጣይ ወራት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

እነዚህን ነገሮች ከማዘጋጀት በተጓዳኝ፤ ሥራውን ለማሳለጥ በዘርፋ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ማዕከሉ የእንስሳት ዘርፉ የሚፈልገውን የቴክኒክ እና ሌሎች ሙያዊ ግብዓት የሚሆኑ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እንደ ልኅቀት ማዕከል የሚያገለግል እንደሚሆን ገልጸዋል።

ወደፊት ግንባር ቀደም አርብቶ አደሮች ገብተው የሚሠለጥኑበት እንደሚሆን አመልክተው፤ የሰው ሠራሽ ማዳቀል ሥራ ለመሥራት ፈሳሽ ናይትሮጂን እና ዝርያዎችን ለማዘጋጀት ያሉት ማዕከላት አናሳ መሆናቸውን ለሥራው መዳከም የመጀመሪያው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

የፈሳሽ ናይትሮጂን፤ የዝርያ እና የባለሙያ ችግር ስለተፈታ ከዚህ በኋላ ያለው የእንስሳት ተዋፅዖ ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎች በራስ አቅም እንደሚፈቱም ጠቁመዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን እንስሳት ለማዳቀል መታቀዱን አመልክተው፤ በስምንት ወራት ሦስት ሚሊዮን ለማዳቀል ተችሏል። ይህን ለማሳካት የተቻለው በዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ለመፍታት በመቻሉ እንደሆነም አመላክተዋል።

የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አሥራት ጤራ(ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለፁት፤ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የያዘውን የሰው ሠራሽ የእንስሳት ማዳቀል ሥራ ለማሳካት፤ የሌማት ትሩፋት መንደሮች ለማሠልጠን በዘርፉ የሠለጠኑ ቴክኒሻኖች ተደራሽነት ወሳኝ ሚና አለው።

በዘርፉ የሚገኘውን ውጤት ለማሻሻል ባለፉት ጊዜያት በርካታ ሥራዎች ተሠርተው በዓመት 500 ባለሙያዎች የማሠልጠን አቅም መፈጠሩን ገልጸው፤ በሀገሪቱ የሚፈለገውን ባለሙያ ለማሟላት በጥናቱ መሠረት ከ16 ሺህ በላይ አዳቃይ ቴክኒሻኖች ማሠልጠን ይጠበቃል ብለዋል።

የወተት እሴት ሠንሠለት በእውቀት መመራት ስላለበት የሚገነባው ማዕከል በአንድ ዙር 250 ባለሙያዎችን ማሠልጠን የሚያስችል መኝታን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮች የተሟሉለት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ማዕከሉ መሠረታዊ የሆነ የማዳቀል ሥልጠና ከመስጠት በተጓዳኝ በወተት እሴት ሠንሠለት ላይ ሥልጠና እንደሚሰጥ አመላክተዋል።

ፕሮጀክቱ በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚገነባ ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የግንባታ ሥራው ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You