
አዲስ አበባ:- 1446ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አል ፈጥር በዓል አብሮነትና አንድነት የሚታይበትና የምናጠናክርበት ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ፈትሁዲን ሐጂ ዘይኑ አሳሰቡ።
ፕሬዚዳንቱ በዓሉን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደገለጹት፤ የዒድ አል ፈጥር የሰላም፣ የአንድነት፣ የደስታና የአብሮነት በዓል ነው። የዘንድሮውን በዓል ስናከብር ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅርና ስለወንድማማችነት እያሰብንና ለማጠናከር እየሠራን ሊሆን ይገባል።
ባለፉት የረመዳን እያንዳንዷ ቀናት እስላማዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት ረገድ አብሮነትን፣ መተጋገዝንና ማካፈልን ስንተገብር ቆይተናል። አሁንም በዓሉ የደመቀና የሰላም እንዲሆን በአንድነት ልንተባበር ይገባል ያሉት ሼህ ፈትሁዲን፤ ወቅቱ እኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓል የምናከብርበት ብቻ ሳይሆን ወንድሞቻችን የክርስትና እምነት ተከታዮች የፆም ወቅት ነው ።
በመሆኑም በኅብረት ለሀገራችን ልማትና ብልፅግና እንዲሁም ለሕዝባችን ሰላም ጸሎት የምናደርግበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
እስካሁን የተካሄዱት የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር፤ የቁርዓን ውድድር በሰላም መጠናቀቃቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አመልክተው፤ እነዚህንና የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲከበር አብረውን ለሚሠሩት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ እንዲሁም ሰላም በማስከበር ሥራ እየተሳተፉ ላሉ የተለያዩ አደረጃጀቶች ምክር ቤቱ ምስጋናውን ያቀርባል ብለዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም