“ድራማው የሚፈልጉትን የፖለቲካ ዓላማ በእርስ በርስ ግጭት ለማሳካት ያለመ ነው” – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- ‹‹ድራማው ኢትዮጵያ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ፣ የግጭትና የትርምስ ማዕከል እንድትሆን፣ በዚህ ሂደትም የሚፈልጉትን የፖለቲካ ዓላማ በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት ለማሳካት ያለመ ነው፡፡›› ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ስለተላለፈውና መነጋገሪያ በሆነው ፕሮግራም ዙሪያ ትናንትና በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በወጣት ብርቱካን ተመስገን ላይ የተሠራው ድራማ ሕዝብን ለማጋጨት ታስቦ ጠላቶች የፈጠሩት የውሸት ትርክት ነው:: በሀገር ውስጥ ያሉ ጽንፈኞችና የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው፤ ድራማውን የሠሩበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ፣ የግጭትና የትርምስ ማዕከል እንድትሆን፣ በዚህ ሂደትም የሚፈልጉትን የፖለቲካ ዓላማ በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት ለማሳካት ያለመ ነው።

ጉዳዩ እንደ አንድ ነጠላ ክስተት የሚታይ አለመሆኑንና ይልቁንም ባለፉት ሰባት የለውጡ ዓመታት ውስጥ ብዙ ጊዜ መልካቸውን እየቀያየሩ የተከሰቱ ችግሮች አካል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ከባለፉት 50 ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መገለጫዎች መጠፋፋት፣ ጠላትና ወዳጅነት የሚል ቅኝት ያለው እንደሆነ ያስታወሱት ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር)፤ በዚህም ምክንያት ፖለቲካችን የመጠፋፋት ሆኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሴራ ትንተና፣ ሸፍጥ፣ ውሸትና ውዥንብር በመንዛት፤ የፖለቲካ ዓላማን የማሳካት ልምምድ ውስጥ እንደቆየችም ጠቅሰው፤ “እኛ ከያዝነው ሀሳብ ውጭ ያለው አስተሳሰብ በኃይል መጥፋት አለበት የሚል የፖለቲካ ባህልና ልምምድ ውስጥ ቆይተናልም” ብለዋል።

በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ባህላችን ወደ ኋላ የቀረና ዲሞክራሲን የማያውቅ፤ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ልምምድ የሌለው እንደሆነ አመላክተዋል።

እነዚህ ልምምዶች ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ግጭትና በትርምስ ውስጥ እንድትቆይ አድርገዋታልም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የረዥም ዘመን ታሪክና ሥልጣኔ ያላት፤ በሌላ በኩል ከድህነትና ኋላቀርነት ያልተላቀቀች እንደሆነች ጠቅሰዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የተለማመድነው የፖለቲካው ባህላችን እንደሆነ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስለቆየች የብልፅግና መንግሥት ይህን ሁኔታ ከስር መሠረቱ በመቀየር፤ አዎንታዊ ሰላም ለማምጣትና የተረጋጋ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ነበር ብለዋል ።

ከእነዚህም ትናንት ያለንን የተናጠል ቅሬታ አስወግደን የጋራ መግባባት ላይ እንድንደርስ የሚያስችለው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋምን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። የሀገራዊ ምክክር ዓላማ ከበታኝ እና ነጠላ ትርክቶች ይልቅ ወደ አሰባሳቢና የወል ትርክቶች ለመምጣት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ዜጎች ሀሳባቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲያቀርቡ ዕድል ተሰጥቷቸው እያለ ጽንፈኞችና የጽንፍ ፖለቲካን የሚያራምዱ መንግሥት የሚያቀርብላቸውን የሰላም አማራጭና ሕዝብ የሚፈልገውን ነገር ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ፤ አመጽ፣ ሁከት፣ ብጥብጥ፣ የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር እየሠሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል። ከሰሞኑ ከወጣት ብርቱካን ጋር ተያይዞ የተሠራው ድራማም የዚህ ትርክት አካል እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህ ድራማ ሀብት፣ ጊዜ፣ ጉልበት ወጥቶበት በሀገር ውስጥ ያሉ ጽንፈኞችና የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የሠሩት እንደሆነ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ፤ የግጭትና የትርምስ ማዕከል እንደትሆን፤

እነዚህ አካላት አንዳንዴ ብሔርን፣ አንዳንዴ ሃይማኖትን፤ አንዳንዴም ሰብዓዊ መብትን ከሴትነት ጋር በማያያዝና ዲሞክራሲያዊ መብትን ሽፋን በማድረግ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ የሠሩት ድራማ እንደሆነ ገልጸዋል።

በብርቱካን ላይ የተሠራው ድራማም ሴት ልጅ ላይ እንዴት እንዲህ ዓይነት ጥቃት ይፈጸማል በሚል ከዳር እስከዳር ቁጣ እንዲፈጠር አልመው ያደረጉት ነው ብለዋል።

ዋና ዓላማውም ኢትዮጵያን የትርምስ ማዕከል በማድረግ በኃይል ሥልጣን ለመያዝ እንደሆነ ተናግረዋል::

በመጨረሻም ሚዲያዎች አንድን መረጃ ሲያስተላልፉ ሀገርን እና ሕዝብን የማይጎዳ መሆኑን ተጠንቅቀው መሥራት እንደሚገባቸው ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)አሳስበዋል።

አዲስ ዘመን  መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You