
አዲስ አበባ፡- ዒድ የምስጋና፣ የበጎ አድራጎት፣ ወንድማማችነት/እኅትማማችነት ዕሴቶችን የያዘ በዓል መሆኑን እያሰብን፣ እያዳበርንና ለሀገር ግንባታ እየተጠቀምን እንድናከብረው ጥሪ አቀርባለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ዒድ አል ፈጥር” በዓልን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ “ዒድ አል ፈጥር” የረመዳን ፆምን የማጠናቀቂያ በዓል ነው፡፡ ዒድ አል ፈጥር “የምስጋና፣ የበጎ አድራጎት እና የወንድማማችነት/ እኅትማማችነት” በዓል ነው፡፡ እነዚህ “የዒድ በዓል ዕሴቶችን እያሰብን፤ እያዳበርንና ለሀገር ግንባታ እየተጠቀምን እንድናከበረው ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
ዒድ አል ፈጥር ከአንድ ወር የፆም ጊዜ በኋላ የሚመጣ በዓል ነው፡፡ ፆሙ የሰውን ድካም፣ ዐቅም ማነስ እና ልክ የሚያሳይ ነው፡፡ ፈጣሪ ካልደገፈው በቀር የሰው ልጅ ዐቅም ውሱን መሆኑን ያሳያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትዕቢት፣ ጥጋብ እና ክፋት በዚህ ደካማ ሰው ላይ መብቀላቸውን ለተመለከተ፣ የሰው ጠላቱ የገዛ ፀባዩ መሆኑን ይማራል፡፡ ሰው በዘመናት ውስጥ ሌሎችን ለመግዛት የታገለውን ያህል ራሱን ለመግዛት እንዳልታገለ ገልጸዋል፡፡
ዛሬም በሀገራችን የምናየው ፈተና በዋናነት ራስን ካለመግዛት የሚመጣ ፈተና ነው፡፡ ራሱን የማይገዛ ሰው ዐቅሙን አያውቀውም፡፡ ወደ ውስጡ አያይም፡፡ ጠላቱን ከገዛ ፀባዩ ውስጥ ከመፈለግ ይልቅ፣ ጠላቱን ከጎረቤቱ እንደሚፈልገው ገልጸው፤ በዚህ የተነሣ ከገዛ ወገኑ ጋር ሲቃረን ይኖራል፡፡ እንደ ረመዳን ዓይነት ወቅቶች ውስጥን ለመመልከት የሚጠቅሙ እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ውስጣቸውን የተመለከቱ ሰዎች ምስጋና ገንዘባቸው ነው፡፡ ሰው የራሱን ልክ ካላወቀ ሌላውን አያደንቅም፤ ሌላውን አያመሰግንም። የሌለውን ካልተረዳ ያለውን አያውቅም፤ አያደንቅም። የራሱ ጠላት የገዛ ጠባዩ መሆኑ ካልገባው፣ ሌላውን ወገኑን አያፈቅርም። ለዚህ ነው የፆሙ መጨረሻ፣ ዒድ አል ፈጥር የምስጋና በዓል የሆነው።
ፆሙ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ ራስን ገዝቶ ለመሰባሰብ ይጠቅማል። መሰባሰቡም ከስሜት የወጣ፣ ስክነትና ራስን መግዛት ያለበት እንደሆነ አመልክተው፤ ሀገራዊ ምክክራችን ይሄን ዕሴት ቢላበስ እንጠቀማለን። መነጋገሩ ብቻ አይጠቅምም። ከስሜት ወርዶ፤ በስክነት ተሞርዶ፤ ነገን ተመልክቶ-መመካከር። ያ ከሆነ እንደ ዒድ ሁሉ፣ የምክክራችን ፍጻሜው ምስጋና እንደሚሆን ተናግረዋል።
የዒድ ሌላው ዕሴት በጎ አድራጎት ነው። ዐቅም ለሌላቸው፤ ሁኔታው ላልተሟላላቸው ወገኖች መልካምን ነገር ማድረግ። ዝምድናን፣ ዘርን ወይም እምነትን ሳይመለከቱ ሰውን በሰውነቱ ብቻ መርዳት። የፆም ምንዳ ሙሉ የሚሆነው በጎ አድራጎት ከተጨመረበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በጎ አድራጎት ማለት ከራስ አጉድሎ ሌላውን መሙላት ነው። እንደ ሀገር ለመቀጠልና እንደ ሕዝብ ለመተሳሰር በጎ አድራጎት እጅግ አስፈላጊ ዕሴት ነው። ራስን በሌላው ጫማ ላይ አስገብቶ ማየት። የሌላው ጉድለት ለመሙላት ሲባል የራስን ማጣት። ለምን ወገኔ ያዝናል? ለምን ወገኔ ይከፋል? ብሎ መንገብገብ ነው ብለዋል።
ሁላችንም የየራሳችንን ወገን ጥቅምና መብት በማስከበር ብቻ ሀገር ልንገነባ አንችልም። ትስስራችን ወገን ዘለል ሆኖ፣ የሌላውን ወገን ጉዳትና ፈተና መጋራት ይገባናል እንጂ። የእኔ ቤት ሲሟላ አይደለም የእርሱ ቤት የሚሟላው። የእርሱ ቤት ሲሟላ ነው የእኔ ቤት የሚሟላው ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ የፖለቲካ ምኅዳራችን በዚህ ነባር ዕሴታችን ላይ ካልተመሠረተ ፍትሐዊነትን እና እኩልነትን ለማስፈን እንቸገራለን ነው ያሉት።
እነዚህን ሁለቱን ዕሴቶች የሚያስተሳስረው የዒድ ዕሴት “ወንድማማችነት/እኅትማማችነት” መሆኑን አመልክተው፤ ወንድማማችነት/እኅትማማችነት ማለት በጋራ ዕሴቶች፣ በመተባበር እና በጋራ ግብ ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት ነው። ይሄ ወዳጅነት በሥነ ምግባር የተገራ፣ ፍቅርንና አንዱ ለሌላው መቆምን መሠረት ያደርጋል። የጋራ ኃላፊነትን ይወስዳል ብለዋል።
“በሀገራችን የፖለቲካ ሕይወት እጅግ አስፈላጊው/ግን እጅግ የተረሳው ዕሴት ነው። መብትንም ሆነ ግዴታን በወንድማማችነት /እኅትማማችነት መነጽር መመልከት ነገሩን ለሰውነት ቅርብ ያደርገዋል። ለእኔ ከሚለው አውጥቶ ለእኛ፤ ለእኛ ከሚለውም ጭምር አውጥቶ “ለእነርሱ እና ለእኛ”፤ ለእነርሱ እና ለእኛ ከሚለውም አውጦቶ “ለእኛ ይቅርብን፤ ለእነርሱ ይደረግ “ወደሚለው የላቀ ስብዕና ያደርሰዋል” ሲሉም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በእምነቶች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በማኅበረሰቦች እና በልሂቃን መካከል የተሻለውን አብሮነት የሚፈጠረው ወንድማማችነት/እኅትማማችነት ነው።
የተሻለ መረዳዳት፣ የተሻለ መተዋወቅ እና የተሻለ መግባባት ይፈጥራል። ለሌላው ሲል መተውን፤ ለሌላው ሲል መቀበልን እና ለሌላው ሲል ለበደሎች ዕውቅና መስጠትን የሚያስገኘው ዕሴት – ወንድማማችነት/እኅትማማችነት ነው።
እነዚህን የበዓሉ ዕሴቶች እያሰብን፣ እያዳበርንና ለሀገር ግንባታ እየተጠቀም እንድናከብረው ጥሪ አቀርባለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ቤተሰቦች፣ ጎረቤታሞች፣ ማኅበረሰቦች እና የእምነት አባቶች ሲሰባሰቡ እነዚህ ሦስት የዒድ ዕሴቶች ጎልተው እንዲወጡና ማኅበረሰባችን እንዲገነባባቸው እንዲያደርጉ አደራ እላለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም