
አዲስ አበባ፤- ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን የፆም ወቅት ያሳየውን መተሳሰብ፣ መረዳዳትና አብሮነት በዒድ አል ፈጥር በዓል ሆነ በሌሎች ወራቶች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አሳሰቡ። የአፍጥር መርሐ ግብር በማዘጋጀት አብሮነትን ላሳዩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ ለ1446ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን ትናንት ሲያስተላልፉ እንዳሉት፤ የረመዳን ፆም በሰላም በደስታና በፍቅር ተጠናቆ ለዒድ አልፈጥር በዓል ደርሰናል። ፆሙ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እስኪጠናቀቅ ድረስ ከመቼውም ጊዜ የተለየ አብሮነትና መተሳሰብ የታየበት ነው። በምናከብረው የዒድ አል አልፈጥር በዓልም በተመሳሳይ አቅም የሌላቸው ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ በፍቅርና በሰላም ልናከብረው ይገባል ብለዋል።
እያንዳንዱ ሕዝበ ሙስሊም ባለው አቅም የሌላቸውን ወንድሞቹንና እህቶቹን ሊደግፍ ይገባል። ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ፣ ወላጅ አልባ ልጆችን፣ አቅመ ደካሞችን እንዲሁም በየጎዳናው የወደቁትን ወገኖች ማሰብና መደገፍ ከእያንዳንዱ ምዕመን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በዓሉ ለሰው ልጆች ሰላም የሚሰበክበትና የይቅርታ መሆኑን አመልክተው፤ በተለያዩ ምክንያቶች አኩርፈው መሣሪያ አንስተው ጫካ የገቡ አካላትም ይቅር መባባልን ሊያስቀድሙ ይገባል ብለዋል። የዘንድሮውን የረመዳን ፆም ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ጠንካራ አብሮነት የታየበት መሆኑ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እምነታቸው ሳይገድባቸው ሁሉም የመንግሥት ተቋማትና ድርጅቶች የአፍጥር መርሐ ግብር በማዘጋጀት ለሰጡን ፍቅርና ላሳዩን አብሮነት ተግባር እናመሰግናለን ነው ያሉት።
ይህ ተግባር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኘውን ሕዝበ ሙስሊም ያስደሰተ ተግባር መሆኑን ገልጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያላቸውን ሳይሆን ምስኪኖችን በመሰብሰብ ያካሄዱት የአፍጥር መርሐ ግብር ለብዙዎቻችን ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ አንስተዋል።
“እኛም በዓሉን ስናከብርም ሆነ ከዚያ በኋላ እንደመርሕ በመከተል የሌላቸውን በማስታወስና በመደገፍ የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርገው የሚገባ ጉዳይ ነው” ብለዋል።
በመንግሥት ጥረትና በመጅሊሱ ትብብር የአፋርና የሶማሌ ክልሎች በመሐከላቸው የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የንጹሐን ደም ሳይፈስ የዘንድሮውን ረመዳን በአንድነት ማሳለፋቸው ለሁላችንም ደስታን ሰጥቶናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እንዲህ አይነቱ ተግባር እንዲቀጥልም ሁላችንም ልንሠራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ገለጻ፤ አካባቢያችንና ጎረቤታችን ሰላም ሳይሆን እኛ ሰላም ልንሆን አንችልም። በመሆኑም ከራሳችን ጀምሮ ለጎረቤት ለሀገርና ለዓለም ሰላም አበክረን ልንፀልይና ልንሠራ ይገባል።
በኢትዮጵያና በመላው ዓለም ለሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን ለ1446ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በሠላም አደረሣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ፣ በዓሉ የሠላም፣ የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም