በቅናት ልጅን እስከ ማጥፋት

እናትነት መልካም ገጽታዎችን ደራርቦ የያዘ የሴት ልጅ ትልቅ መገለጫ ነው። እናትነት ከፍ ያለ ሥልጣን ነው። እናትነት ጥልቅና ሰናይ ባሕሪያት የሚፈልቁበት ምንጭ ነው። እናትነት የደግነት፣ የጥራት፣ የልህቀትና ተፈላጊነት ማሳያ ተምሳሌት ነው። እናትነት ሞት የማያደበዝዘው ኃያል መንፈስ ነው። እናትነት ከባድ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ነው። … እናትነት የሰላም፣ የመልካም ግንኙነትና እንክብካቤ መፍለቂያ አድባር ናት። እናትነት ሰፊና ጥልቅ የሕይወት ትምህርት ቤት ነው። እናትነት ሌሎች ከስቃይ ነፃ እንዲሆኑ፣ ምቾት እንዲሰማቸው በሚደረግ ትግል ውስጥ ዋጋ እየከፈሉ መኖር ነው።

እናቶች ሰው የመሆኛ ቅመሞች የሚጨለፍባቸው ባሕር ናቸው። … ሕይወታዊ ስሪታችን ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን የወሰደው ከእናት ነው። ከእናት የምናገኘው ‘ማይቶኮንድሪያ’ (ማይቶኮንድሪያ የኃይል ማመንጫ ክፍል ሲሆን የምንመገበው ምግብ እየተቃጠለና ወደ አስፈላጊው ኃይል እየተቀየረ ሕይወትን ያንቀሳቅሳል) የምግብ ማቃጠያ ምድጃ ወይም ኃይል ማመንጫ ቤት ሆኖ ያገለግላል። … ብዙ መልካም ስብዕና መገለጫዎች ምንጫቸው የእናት ፍቅር፣ የመልካም ስብዕና እና የርህራሄ ምንጭ ነው፤- እናትነት።

እናትነት በልጅ ይፈትናል። እናት የመሆን ብርታትም ድክመትም ከልጅ ጋር የተያያዘ ነው። በልጅ ከመፈተን የበለጠ እናትነትን የሚጎዳ አንዳች ኃይል አይገኝም። ስለ እናትነት ይህን ያህል እንድናነሳ ያስገደደን የእናት ደካማ ጎን የሆነውን ልጅ ተጣላሁኝ በሚል ምክንያት የቀጠፈውን አጋጣሚ ልናካፍላችሁ ስለወደደን ነው። መልካም ንባብ።

ተስፈኛዋ ልጃገረድ

ደስተኛና ፍልቅልቅ ልጅ ነበረች። ደስ የሚል የልጅነት ጊዜን ነበር ከቤተሰቦቿ ጋር ያሳለፈችው። እሷ በልጅነቷ ያሳለፈችውን ዓይነት ሕይወት ለመምራት ሌት ከቀን ታሰብ ነበር። በህልሟም በውኗም እንደ አባቷ ያለ ትሁትና ጨዋ ሰው እንዲገጥማት ታስባለች።

የሕይወት አጋሯ ወደ እሷ እስኪ መጣ በሥራ ሕይወቷን ለማሸነፍ ትታትር ጀመር። ያገኘችውን የምትሠራ ሠርታ ያገኘችውን የምትቆጥበው ተስፈኛ ልጃገረድ ከእለታት በአንዱ ቀን ከአሁኑ ባሏ ጋር ተያዩ። ልክ እንደተያዩ ነበር ልባቸው ለሁለት ክፍል ያለው። የትናንት ተስፋዋን ሰንቃ ለነገ የምታስበው ይች ጠንቀቃ ወጣት ውሃ አጣጬን አገኘሁ በሚል ልቧ እርፍ አለ።

ለአንድ ብላ የምትሮጠው ሩጫ ለሁለት መሆኑ ልቧን አስደስቷታል። መኖር የምትፈልገውን ኑሮ ለመኖር ጥረቷን አጠናክራ ቀጠለች። ምንም እንኳን በሕይወቷ አዲስ ሰው ቢመጣም ልቧን ያላሰረፍው ነገር መኖሩን አስተውላለች። በውሃ ቀጠነ የሚያኮርፈው ጓደኛዋ ችግሩ ምን እንደሆነ መረዳት አቅቷታል። ወይ እንደ ሰው ተናገሮ አይወጣለት.. ወይም ደግሞ አይተዋት ነገር ሆኖባት ዘወትር ይከነክናት ጀመር።

ብቸኝነት እያነጫነጨው ይሆናል ብላ ያሰበችው ይህች ወጣት በትዳር ተጠቃለው ሕይወታቸውን እንዲመሩ ጥያቄ አቀረበችለት። እሱም በደስታ ጥያቄዋን ተቀብሎ ለሶሰት ጉልቻ በቁ።

ቅናተኛው አባወራ

ቅናት በደም ስሩ የገባ ይመስል በወጣ በገባ ቁጥር ይነዘንዘታል። መለስ ሲል ምንድነው ውስጤን በሚበላ በጣም ደስ በማይል አሰቃቂ ስሜት ውስጥ የገባሁት ብሎ ራሱን ይጠይቃል። ይህ አሰቃቂ ሰሜትም ከውስጡ ማውጣት አልቻለም። ወዳው ፈቅዳ ጓደኛው የሆነችውን ሴት ንፁህ ህልሞች እያጨለመ መኖሩን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። እሷ የፍቅር ሕይወታቸው ውስጥ ሁሉ ንጹሕ እና ብርሃን ይዞ እንዲቆይ ትፈልጋለች። እሱ ግን በዚህ ቅናት በሚሉት ሰዎችን ቅር የሚያሰኝና መራር ሕመም ትቶ የሚያለፍ ጉዳይ ተጠምዶ ማጣፊያው እንዳጠረው ነው የሚኖረው።

ቅናት ለአንዳንዶች በተለይ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች መካከል ለፍቅር ወሳኝ እይታ ነው ብለው ያምናሉ። ቅናት የፍቅር ማጣፈጫ እንደሆነ የሚያምነው ይህ ሰው ቅናቱ ሌላው ሰው ላይ የሚፈጥረውን ተፅእኖ ለመመለከት ዓይኑ ተጋርዶ ነበር። እዚህኛው ቤት በቅናት የተነሳ ቤት ንብረታቸውን ያጡ፤ ከንብረትም በላይ የቤተሰብ ፍቅር የተነጠቁት ይኖራሉ ከሚባል በላይ አሰቃቂ ድርጊትን ለመፈፀም ቅናት ሰበብ ሆኗል።

በጓደኝነት ጊዜ ይፋ ባያወጣውም ውስጥ ውስጡን ሲበላው የኖረው ቅናት፤ ትዳር ላይ ከገቡ በኋላ ተባብሶ ቀጠለ። ምንም እንኳን ትዳራቸው በልጅ ቢባረክም ሰበብ አስባብ ፈልጎ ሚስቱን ለመጠርጠር ምክንያት የማያጣው አባወራ የቤቱን ሰላም ማደፍረስ ሥራዬ ብሎ ይዞታል።

ከዕለታት በአንዱ ቀን የሁለት ዓመት ልጁን አዝላ ገበያ ደርሳ ስትመለስ አንደ ሰው ሸክሟ አሳዘኖት የያዘችውን እቃ ይቀበላታል። የተሸከማለት ሰው እና እማወራዋም እየተጫወቱ መንገዳቸውን ቀጠሉ።

የጠቡ መነሻ

መንገደኛው ሰው እማወራዋ በምትሄድበት አቅጣጫ የሚጓዝ በመሆኑ የያዘችውን እቃ ተሸክሞ ቤቷ አደረሰላት። ተመሰጋግነው እሱም መንገዱን ቀጠለ። ይህ ሁሉ ሲሆን አድፍጦ ይከተል የነበረው አቶ ባል የቅናት ዛሩ ተነስቶ ይጨፍርበት ገባ። ንዴት አቅሉን እንደሳተው ወደቤት ተንደርድሮ የገባው አባወራ ባለ በሌለ ኃይሉ ሚስቱን በጥፊ ሲያላጋት ከግድግዳ ጋር ተጋጭታ ባፍጢሟ ተተከለች።

በወደቀችበት ሯሷን የሳተችውን ሴትን ትቶ የገዛ ልጁን ከወላጅ እናቷ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት ሊያጠፋው ፈለገ። እናት ከወደቀችበት አልተነሳችም ልጁን ሲመለከት በሰላም ተኝቷል። ከተኛበት አንስቶ አየወ። የአባትነት ርህራሄውን የቅናት ስሜት አጥፍቶበታል። ልጁ በሰላም እንቅልፉን እየለጠጠ ነው። የለመደው የአባቱ ጠረን ስለሆነ ይሁን ሌላ ምንም ነገር ከእንቅልፉ የሚያባንነው አይመስለም ነበር። ጭራሽ ተመቻችቶ ወደ አባቱ ደረት ጠጋ ብሎ እንቅልፉን ቀጠለ።

አሰቃቂው ድርጊት

መነሻው ከሕፃኑ ወላጅ እናቷ ጋር በመጋጨቱ ነው። በእነሱ ግጭት መካከል ሕፃኑ ምንም ድርሻ አልነበረውም። ግን አባትነቱን ያስረሳው ቅናት ከንዴት አልፎ ወደ ጭካኔ ተቀየረ። ሕፃን ልጁን ጉሮሮዋን አንቆ በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለ በኋላ አስከሬኑን መጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ጨመረው።

በዚህ መካከል ነበር እናት ከወደቀችበት የተነሳችው። ተነስታ ልጇ ወደተኛበት አቅጣጫ ተመለከተች። ልጇ የለም። ሰውነቷን ማንቀሳቀስ ተሰናት። ምንም እንኳን ብርክ የሚያስይዝ ከባድ ድንጋጤ ውስጧ ቢገባም አባት ልጁ ላይ ክፉ ነገር ያደርሳል ብላ አልጠበቀችም።

‹‹በቃ በእኔ ሲናደድ ልጁን ወስዶ ብቻውን ሊያሳድግ ነው። ወይም ለቤተሰቦቹ ሊሰጥ ነው የሚሉ እና ሌሎች ምክንያቶችን ጭንቅላቷ ውስጥ ደርደራ ወደ ውጭ ብቅ አለች። ተናዳጁ አባወራ የሠራውን ሠርቶ ወደ ልቡ ሲመለስ በር ላይ ተገጣጠሙ። የሆነውን ሁሉ በአፉ ተናገረ።

የሕጻኗ እናት ከሆነችው ባለቤቱ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት የሥጋ ልጁን አንገቷን አንቆ ሕይወቷን ካሳለፈ በኋላ 10 ሜትር ጥልቀት ባለው የመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ማስገባቱ በአፉ ተናገረ።

እናት የሰማችውን ነገር መቀበል ተሰናት ራሷን ሳተች። የሚስትን መውደቅ የተመለከቱ ጎረቤቶች ወደቤት ብቅ ሲሉ የሆነውን በሙሉ ሰሙ። ምንም እንኳን ለጆሮ የሚከብድ ነገር ቢሰሙም ሕግ ማወቅ ነበረበትና ፖሊስ ጠርተው እናትን ወደ ሆስፒታል ወሰዷት።

የፖሊስ ምርመራ

ጥቆማ የደረሰው የደሎቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አዋለው። ተጠርጣሪ አደረኩት ያለውን ድርጊት እውነት አለመሆኑን ለልባቸው የነገሩት የሕግ አካላት አስከሬኑ ተጣለበት የተባለውን አካባቢ መበርበር ጀመሩ። ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋለውን ተጠርጣሪ ደጋግሞ ሲጠይቅ ቃሉ አንድ በመሆኑ ድርጊቱ ስለመፈፀሙ ወደርግጠኝነት አመጣው። ሕፃንዋን እንዳለው አድርጓል። በአፉ ያደረገውን ደጋግሞ መናገሩ ሁሉም ሰው ቢገርመውም ከሁሉ የከፋው ደግሞ የሕፃኗን አስከሬን ከመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ መጣሉ ነበር። ከሁለት ቀን ፍለጋ በኋላ የተገኘውን የሕፃኗን በድን አካል በማውጣት አስከሬኑን ለምርመራ ወደ ወራቤ ኮምፕሬሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተላከ።

ፖሊስ ይህን አሰቃቂ ድርጊት ከሰማና ከአየ በኋላ ምርመራውን አጠናክሮ ጨረሰ። የምርመራ ውጤቱን በመያዝ ለተፈጸመው ድርጊት አስፈላጊ የሆኑ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች አሰባስቦ፣ አጠናቀቀ። ምርመራውን በማጣራት መዝገብ አደራጅቶ ለስልጤ ዞን ዓቃቤ ሕግ አቀረበ።

የአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

ዓቃቢ ሕግ ከፖሊስ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ ሲመለከት ተከሳሹ የሕፃኗ እናት ከሆነችው ባለቤቱ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት የሥጋ ልጁን አንገቷን አንቆ ሕይወቷን ካሳለፈ በኋላ 10 ሜትር ጥልቀት ባለው የመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ማስገባቱ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ መረጋገጡን ይመለከታል።

ፖሊስ በምርመራ ያደራጀውን ውጤቱን በመያዝ ለተፈጸመው ድርጊት አስፈላጊ የሆኑ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች አሰባስቦ፣ ምርመራውን በማጣራት የተደራጀ መዝገብ ለስልጤ ዞን ዓቃቤ ሕግ አቀረበ። ስልጤ ዞን ዓቃቤ ሕግ ከፖሊስ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ አይቶና ፈትሾ ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539(1)(ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ በፈጸመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ክስ መስርቶ ለስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረቡንም አቀረበ።

የስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ከዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን የነፍስ ግድያ ወንጀል ክስ የቀረበለትን ክርክር ሲያደርግ የቆየው ተከሳሽ በክርክሩ ሂደትም የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል አልቻለም።

ተከሳሽም ክሱን ማስተባበል ባለመቻሉ ምክንያት ከዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን የነፍስ ግድያ ወንጀል ክስ የቀረበለትን ተገቢ የሆነ ማስረጃ መሠረት በማድረግ የስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽን ያርማል፤ ሌሎችን መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን ያስተምራል በማለት፤ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ተከሳሽ ደጀኔ መኮንን ተክለፃዲቅ በዕድሜ ልክ በፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን  መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You