
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረችው መርሃ-ግብር ለዘላቂ እድገት ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለማስፋት የአረንጓዴ ቦንድ እና የካርቦን ክሬዲት መገንባት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ በኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ እና በሌሎች አጋር አካላት ጥምረት በትናንትናው እለት ተካሂዷል፡፡
በወቅቱ የኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሂክመት አብደላ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 163 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ጂዲፒ እና ከ120 ሚሊዮን በላይ የሀገሪቱ ሕዝብ በዋናነት ከግብርና ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ለአየር ንብረት ተጽዕኖ የተጋለጠ ነው፡፡ በዚህም ከሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ላይ በዓመት ከአንድ እስከ አንድ ነጥብ አምስት በመቶ ኪሳራ ይደርሳል። ይህም እ.አ.አ በ2040 ወደ አምስት በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን እያንዳንዱ ተግዳሮት የራሱ የሆነ እድል አለው የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ኢትዮጵያ አየር ንብረትን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረችው መርሐ-ግብር እና አረንጓዴ ዐሻራ ለዛቂ እድገት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሂክመት እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር በ2030 የጋዝ ልቀትን በ68 ነጥብ ስምንት በመቶ ለመቀነስ የታቀደውን እቅድ ለማሳካት 316 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም ለዚህ ተግባር የአረንጓዴ ልማት የገንዘብ አማራጮች ማለትም “ግሪን ቦንድ” እና “ካርቦን ክሬዲት” እንደ አማራጭ የሚወሰዱ ሳይሆን፤ የግድ አስፈላጊ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ከአጋር አካላት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን አረንጓዴ ካፒታል ገበያ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ማዕቀፎችን ለማሳደግ ሚናቸው የጎላ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከፍተኛ አማካሪ አቶ አሰፋ ሱሙሮ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመፍጠር፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር፤ ውጤታማ እንዲሆን በፕላን ሚኒስቴር እና በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡
ነገር ግን እነዚህ ሥራዎች የካፒታል ገበያን መሠረት ያደረጉ ሳይሆን፤ አየር ንብረት ለውጥ ችግር መቋቋም እና መቅረፍ ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ባለሥልጣኑ በዋናነት ትኩረት ያደረገው ለአረንጓዴ ልማት በተለያዩ ተቋማት የሚሠሩ ሥራዎችን በማየት ያለው የመመሪያ እና የሕግ ክፍተት ምንድን ነው? የሚለውን ከመለየት በተጓዳኝ፤ የሌሎች ሀገራትን ልምድ በማየት በኢትዮጵያ ምን አይነት ካፒታል ገበያ መፍጠር እንደሚቻል አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚደረጉ ምርምሮች እና ውይይቶች መነሻ ሃሳብ እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም