
– አንድ እንቁላል በ20 ብር መሸጡ ተገቢ አይደለም
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተከናወነ ባለው የከተማ ግብርና ሥራ በቀን ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን እንቁላል እየተመረተ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ የአንድ እንቁላል ዋጋ እስከ 20 ብር መሸጡ ሕገወጥ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ፤ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ባለው የከተማ ግብርና ሥራ በተለይም በዶሮ ርባታ በቀን እየተገኘ ያለው የእንቁላል ምርት ከፍተኛ መሆኑንና ሥራውም አበረታች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
እንቁላል በስፋት እንዲመረት በማህበር ተደራጅተው ለሚሠሩ እስከ 100፣ በቤተሰብ እስከ 50፣ ለእናቶች አምስት ቄብ ዶሮዎች የሚይዝ የዶሮ ቤት(ኬጂ)፣ በመስጠት በንቅናቄ እየተሠራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቅሰው፤ በተጨማሪም ለከተማ ግብርና በተዘጋጁ ሼዶች ከ500 እስከ አንድ ሺህ ቄብ ዶሮዎች ይዘው የሚሠሩ መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
አቃቂ ክፍለ ከተማ በልማት ምክንያት ከአካባቢው የተነሱ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸውን በማህበር በማደራጀትና የመሥሪያ ቦታም በማዘጋጀት በተከናወነው ሥራም በመጀመሪያው ዙር ላይ በቀን ወደ 35 ሺህ እንቁላል በማእከል ደረጃ መመረቱን አመልክተዋል፡፡
እንዲሁም በክፍለ ከተማው የሚገኙ አርሶ አደሮች ደግሞ በሚሰጣቸው ጊዜያዊ የግብርና ፈቃድ በመጠቀም በይዞታቸው ላይ በቀን ከ15ሺህ እስከ 25ሺህ የእንቁላል ዶሮዎች በማምረት እያሰራጩና የስጋ ዶሮም እያዘጋጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብር ገበያውን ከማረጋጋት አንፃር አስተዋጽኦ ማድረጉን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ከተመረተበት ሥፍራ አንድ እንቁላል በስምንት ብር ዋጋ ሲቀርብ እንደነበርና አሁን ላይ ከዶሮ መኖ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ አንድ እንቁላል ከ11 ብር ከ50 ሣንቲም እስከ 13 ብር እየቀረበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንቁላል አሁን እየቀረበ ባለው ዋጋ መቅረብ አለበት ብሎ ኮሚሽኑ እንደማያምን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ከዋጋ ጋር የተያያዘውን ጉዳይ በምክትል ከንቲባ የሚመራ በየሳምንቱና በየአስራ አምስት ቀን የሚገመግም ኮሚሽኑን ጨምሮ ግበረኃይል ተቋቁሞ እየሠራ እንደሆነና ኮሚሽኑም በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ውስጥ በቀን ምን ያህል እንቁላል እየተመረተ እንደሚቀርብ ሪፖርት እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡
አንድ እንቁላል ዋጋው እስከ 20 ብር መድረሱ የመሸጫ ዋጋው እንዳልሆነ፣ ከምርት ጋርም እንደማይያያዝና ችግሩ ሰው ሠራሽ መሆኑን ገልፀዋል። በ13 ብር ሂሣብ የሚረከብ ነጋዴ ከአንድ ብር በላይ አትርፎ መሸጥ እንደሌለበት ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡
እንቁላል አሁን ካለው የመሸጫ ዋጋም ዝቅ ባለ ዋጋ መቅረብ እንዳለበት ጠቅሰው፤ ከመኖ ግብዓት ጋር የሚያያዝ መሆኑንና በዚህ ላይ መሥራት እንደሚገባና መኖ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በኮሚሽኑ በኩል እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ወደ 210 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መኖራቸውንና ከዚህ ውስጥ ለግብርና ወደ 87 ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ አገልግሎት ለሚሰጡበት ቦታ እንደማይከፍሉና ወጪያቸው ትራንስፖርት ብቻ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚህ አኳያ አምራቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ይገባቸዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በየሱቁ ከዋጋ በላይ እየቀረበ ያለውን ሕገወጥ ነው ብለዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም