
እውነተኛ ታሪክ ነው። በመዲናችን አዲስ አበባ የተከሰተ። አንድ ቤተሰብ ውስጥ ባልና ሚስት አብረው ይኖራሉ፣ በትዳር ቆይታቸውም አራት ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ያፈራሉ። እናት የቤት እመቤት አባት ደግሞ በአነስተኛ የመንግሥት ሥራ የሚተዳደሩ ናቸው። ልጆቻቸውን የሚያሳድጉትም ሆነ ኑሯቸውን የሚገፉት አባት ከውጪ በሚያመጣው ገቢ እናት ደግሞ በግቢያቸው ከምታረባቸው የሀበሻ ከብቶች ወተት ሽያጭ ነው።
ዓመት በዓል ሲደርስ የዳቦ መድፊያ የኩበት ማገዶ ለመግዛት ቤታቸውን የማያንኳኳ የለም፤ ሁሉም የመንደሩ ሰው ከእነሱ ውጪ ገዝቶ አይጠቀምም። የዚህ ምክንያቱ ሁለት ነው፤ አንዱ ቅርብ ቦታ ላይ ስለሆነ በቀላሉ ልጆችንም ላክ አድርጎ መግዛት ስለሚቻል፤ ሌላው እና ዋናው ምክንያት ግን በጉስቁልና፣ በችግር ውስጥ ያለችና በየጊዜው የባለቤቷ ጡጫና ግልምጫ የሚያርፍባትን የልጆች እናት በኢኮኖሚ ማገዝ ነው።
የቤቱ አባወራ ሁሌም አመሻሽ ላይ መለኪያቸውን ጨብጠው ሞቅ ብሏቸው በገቡ ቁጥር በቤቱ የሚሰማው ድምጽ ለቅሶና የድረሱልኝ የሚስት ወይም የልጆች ጩኸት ነው። «ልማደኞቹ» እስከመባል የደረሰ ስም ወጥቶላቸዋል። ይሄ ልማደኝነት ግን አንድ ቀን ማብቃቱ አልቀረም። ወይዘሮ መሰረት (ስሟ የተለወጠ) በተለመደው የመጠጥ ኃይል ጉልበት ጭኖ የመጣው ባለቤቷን ንግግርና ዱላ መታገስ አልቻለችም። በወገቧ ያረፈባትን ዱላ ነጥቃ ብድሯን መለሰች፤ ከዚህ በኋላ ግን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን መዘዝ አርቃ በማሰብ፤ እየተቋሰሉ አብሮ መቀጠሉን አልመረጠችም፤ የከፋም ነገር ሊያመጣም ይችላልና እስከ እዚያ ሰዓት ድረስ «ለልጆቼ ስል» እያለች የተሸከመችውን እዳ አራግፋ ልጆቿን ቤት ንብረቷን ትታ ልትወጣ ወሰነች። በእልህ፣ በንዴት፣ የተከመረን የበደል ተራራ ናደች:: እናም የታቀፈችውን የሁለት ዓመት ልጇን አንጠልጥላ በጨለማ ቤቷን ጥላ ወጣች::
ወይዘሮ መሰረት በእርግጥ ነገሮች እስኪያልፉ ፈትነዋታል። የሰው ቤት የሰው ነውና ቆርሰው የሚሰጡ እጆች ተቆርሶ ሲሰጣቸው መሸማቀቋ አልቀረም፤ ሆኖም ቀን ያልፋል እስኪያልፍ ያለፋል ብላ የነገዋን እያሰበች የአቅሟንም እየሰራች ጥቂት ወራትን አስቆጠረች። አንዱ ቀን ግን እንደ ሌላው ጊዜ እዚህ ቦታ ሥራ አለ የሚል የጎረቤት መልዕክት አልነበረም የደረሳት። ይልቁንም ባለባት መከራ ላይ ሌላ ያላሰበችውና ያልጠበቀችውን ድንጋጤ ሰማች፤ ያደመጠችውን በሴት ልጇ ላይ ደረሰ የተባለውን ችግር አምና መቀበል ከበዳት፤ እንባ ተናነቃት። ፈጣሪዋን ደግማ ደጋግማ በመጥራት አማረረች። የሰማችውን በአይኗ ማየት፣ በጆሮዋ መስማት እና ማረጋገጥ አለባትና በጨለማ ከወጣችበት ቤት በጸሀይ ተመለሰች።
ጾታዊ ጥቃት የደረሰው በ13 ዓመት ልጇ ላይ ነው:: በቦሀ ላይ ቆሮቆር እንዲሉ እሷ የገባችበትን ችግር ሳትወጣ ሌላ መከራ ተደቀነባት:: ልጇንም አግኝታ ሁሉንም ነገር ተረዳች፤ ተጎጂዋን ወደ ሕክምና ወስዳ ሌላውን ፍርድ ግን ለፈጣሪ ሰጠች:: ጊዜው ቢረዝምም ሁሉም ነገር ግን ተደብቆ አልቀረም። ቀስ እያለ ሚስጢሩ ተገለጠ። ጥቃቱ የደረሰባት በገዛ አባቷ መሆኑ ተሰማ እናት ግን ይሄ ገመናዬ ነው ብላ ጉዳዩንም ለፍትህ አካላት ሳታቀርብ ደፋፍና አስቀረች፤ የልጇም ስነልቡና ሳይታከም ቁስሉም ሳይሽር ተዳፈነ። የግንዛቤ እጥረት የፈጠረው መከራ።
የእነ መሰረት ቤተሰብን አይነትና ከዚህም የከፋ የጾታዊ ጥቃት ታሪክ ብዙ ነው። ያልተነገረላቸው በቤተሰብ፣ በቅርብ ዘመድና አዝማድ፤ በአደራ ጠባቂ ጎረቤት የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች በርካታ ናቸው። ለጋ የሆኑ ከእቅፍ ያልወጡ ሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት በየጊዜው የምንሰማው የወሬ ማድመቂያ ሆኗል። በአጥፊዎች ላይ የሚሰጠው ፍርድ ደግሞ አንድም የሚዘገይ፤ ሌላው ደግሞ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ቅሬታን የሚያጭር ጉዳይ ሆኗል።
ጭካኔ በተሞላበት፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሰ ጥቃት የሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ ከ5 እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ነው። ይሁን እንጂ ከፍትህ አካላት በኩል የግንዛቤ እጥረትም ይሁን ጉዳዩን አቅልሎ ከማየት በአጥፊዎች ላይ የሚሰጠው ውሳኔ አመርቂ ሆኖ አይታይም። ዛሬ ዛሬ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ እጅግ ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበትን ወሬ መስማት እየተለመደ መጥቷል። ቀደም ባሉት ዘመናት ብዙም ባልተለመደ መልኩ ጾታዊ ጥቃት ተባብሷል። ይሄ ለምን ሆነ? የወንጀል ድርጊቱ ከባድነት እንዳለ ሆኖ የቅጣቱ ማነስ ምክንያቱስ ምን ይሆን? በፍትህ አካላቱ በኩል ያለው ግንዛቤስ ? የሕጉ ክፍተትስ ተዳሷል?
«ወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎችን በተፋጠነ እና ተጎጅ-ተኮር በሆነ መንገድ መዳኘት» በሚል ርዕስ በጀስቲስ ፎር ኦል-ፕሪዝን ፌሎሽፕ ኢትዮጵያ እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትብብር የተዘጋጀ ማንዋል ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኞች ስልጠና ሰጥቶ ነበር። ስልጠናው በዋነኛነት የፍትህ አሰጣጡ ስርዓት፣ ከላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች እና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። በዚህ ዙሪያ ዳኛ መላኩ ካሳዬ ማብራሪያ ሰጥተውናል።
ዳኛ መላኩ ሲገልጹ፤ ወሲባዊ ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት የሚፈጸም ድርጊት ነው:: በመጠኑ እና ዓይነቱ ከሚለያይ በስተቀር ጥቃቱ ባደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚፈጸም ነው። ወሲባዊ ጥቃት በሠላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ ይፈጸማል። ይሁን እንጂ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረው ግንዛቤ በጣም የተሳሳተ ሆኖ ቆይቷል:: ለምሳሌ፡- አስገድዶ መድፈር በጥንት ዘመን ይታይ የነበረው በንብረት ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል ተደርጎ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በባል ወይም በቤተሰብ ክብር ላይ እንደተፈጸመ፣ በሂደትም በሴቷ ክብር እንዲሁም በሞራል ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል ተደርጎ ሲቆጠር ቆይቷል።
በሴቷ ሰብአዊ መብቶች ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል (በሴቷ ስብዕና፣ ክብር፣ የወሲብ ነጻነት፣ የአካል ደኅንነት፣ የመራባት፣.. ወዘተ መብቶች) ላይ የሚፈጸም ከባድ ወንጀል መሆኑ ግንዛቤ እያገኘ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሆኑን ያስረዳሉ::
ዳኛ መላኩ እንደሚሉት፤ አሁንም ቢሆን ወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎችን እንደ ሁለተኛ ደረጃ፣ በማኅበራዊ ሕይወት እንደሚገጥም ቀላል ወንጀል፣ የቤተሰብን ክብር እንደሚያጎድፍ እና የኅብረተሰብን ሞራል እንዲሁም ኃይማኖት እንደሚያበላሽ ወንጀል የማየትና ዋና ተጎጅዋን የመርሳት ወይም ከግምት ውስጥ ያለማስገባት እንዲሁም አጠቃላይ ድርጊቱን እንደ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ድርጊት እንጂ እንደ ኃይል ጥቃት አድርጎ ያለማየት ችግር በስፋት አለ። ከነበረው የተሳሳተ አረዳድ እና ግንዛቤ የተነሳ (ፆታ እና ሥርዓተ ፆታ) በተለይ ሴቶች እና ልጃገረዶች ከሚደርስባቸው ጥቃት ተገቢው የሕግ ከለላ እና መፍትሔ ሳይሰጣቸው በደልን ተሸክመው በሰቆቃ እንዲኖሩ ተገድደዋል።
የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ጉልህ እጥረቶች
ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በሚመለከት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ- አዋጅ ቁ 414/1996 ተበታትነው የተቀመጡ ሲሆን ጉዳዩን በሚመለከት የተለየ ክፍል አለመደንገጉ፣ በተመሳሳይ የ1954 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዐት ሕጉ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ካለመሆኑም በላይ ያለው ሕግ የማሻሻል ሂደት ዓመታትን አስቆጥሯል። በአጠቃላይ የሕግ ሥርዓቱም ሆነ የፍትሕ አካላቱ ተቋማዊ አሠራር ለወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎች፣ ለተጎጂዎችና ለምስክሮች ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የተለየ ቦታ ወይም ትኩረት የማይሰጥ መሆኑ ተመላክቷል።
የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እና የወንጀል ሕጉ (ኮዱ) የመግቢያ ክፍል እንዲሁም በ2003 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ ስለ አንዳንድ ሥርዓተ-ጾታን መሠረት ያደረጉ ድርጊቶች ከፍ ያለ ትኩረት የሰጡ ቢሆንም ወደተግባር ለመለወጥ የሚያስችሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ገና አለመፈጠሩን ያብራራሉ።
ከአመለካከት፣ ከመሠረታዊ የወንጀል ሕግ ማዕቀፍ እና ከተቋማዊ አሠራር ጀምሮ ስለወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎች ያለው ሁኔታ ገና ብዙ የሚቀረውና መሻሻል ያለበት መሆኑን ነው ዳኛ መላኩ አጽንኦት ሰጥተው የሚናገሩት።
በተለይም በፖሊስ፣ በዓቃቢያነ ሕግ፣ በጠበቆች እና በፍርድ ቤቶች በኩል ስለወሲባዊ ጥቃት እና ከዚህ ጋር ስለተያያዙ የወንጀል ፍትሕ ጉዳዮች ገና መለወጥ፣ እንደገና መቃኘት ያለባቸው ጉዳዮች በርካታ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።
የወሲባዊ ጥቃት ድርጊቶችን ምንነትና ክብደት በትክክል ከመገንዘብ ጀምሮ እንዲህ ላሉ ጥቃቶች እና ተጎጂዎች ተገቢውን ትኩረትና ክብደት ሰጥቶ ገና መሠራት ያለበት ጉዳይ መሆኑንም ያብራራሉ።
አጠቃላይ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ጉልህ እጥረቶች ፍርድ ቤቶችም የሚጋሯቸው፣ ከዚያም አልፎ በአንዳንድ ሁኔታዎች የበለጠ የሚመለከታቸው ናቸው። የዳኝነት አካሉ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች አተገባበር ላይ ካለው የጎላ ሚና እና ኃላፊነት አንጻር ከሌሎቹ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት የበለጠ እንደሚጠበቅበት ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የዳኝነት አካሉ አሁን ላይ የወሲባዊ ጥቃት ጉዳይን በተመለከተ ያለው አተያይና አሠራር ቀደም ሲል ከነበረው የተለየ ወይም የተለወጠ ስለመሆኑ የሚጠቁም ነገር ገና መሆኑን ይናገራሉ።
የወሲባዊ ጥቃት ጉዳይን በትክክል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አካል እንደሆነ አድርጎ የማየትና ለወንጀሉ እና ለተጎጂዎች ሊሰጥ የሚገባውን ትኩረትና ክብደት ሰጥቶ የመሥራት ጉዳይ ገና በተግባር መታየት ያለበት መሆኑንም የሚናገሩት አጽንኦት ሰጥተው ነው።
ዳኛ መላኩ እንደሚሉት፤ አሁን ባለው ሁኔታ ምናልባት ወጣት አጥፊዎች በወንጀል ተጠርጣሪነት ወይም ተከሳሽነት ሲቀርቡ በተወሰኑ አካባቢዎች ከሚታይ መልካም ጅምር በስተቀር ስለ ወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎች እና ስለተጎጂዎች እንዲሁም ምስክሮች በፍርድ ቤቶች የተለየ ክብደትና ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ አይታይም። የሥርዓተ ጾታ ጥቃት አንድ አካል የሆነው ወሲባዊ ጥቃት ሁለቱንም ጾታዎች (እንዲሁም ሌላ መገለጫ ያላቸውን) የሚመለከት ጥቃት ነው:: ብዙውን ጊዜ ግን የጥቃቱ ሰለባዎች ሴቶች እና ልጃገረዶች ናቸው::
በኅብረተሰቡ ውስጥ ባለው የተዛባ አመለካከት፣ ልማድና አሠራር የተነሳ ሴቶች እና ልጃገረዶች በጾታቸው እና የሥርዓተ- ጾታ ሥርዓት ምክንያት የሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት ብዙ ዓይነት እና አስከፊ መሆኑን ያብራራሉ:: ጥቃቶቹ በተጎጂዎች የአካል፣ የአእምሮ እና የስሜት ደኅንነት፣ ሰብአዊ ክብር እንዲሁም ጤንነት እና የወሲብ ነጻነት ላይ የሚፈጸሙ ስለመሆናቸው ይናገራሉ:: እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አካል መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እንደየሀገሩ ሁኔታ ያለው የአቀራረብ ልዩነት፣ ጥልቀትና ስፋት እንደተጠበቀ ሆኖ ወሲባዊ ጥቃቶች በወንጀል ሕግ የሚያስቀጡ ድርጊቶች መሆናቸውን ያብራራሉ:: በጾታቸው እና የሥርዓተ- ጾታ ሥርዓት ምክንያት ከሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት በተጨማሪ ሴቶች እና ልጃገረዶች በሌሎች ማንነታቸው የተነሳም (በፖለቲካዊ፣ ነገዳዊ/ ዘውጋዊ፣ ኃይማኖታዊ እና የዘር ማንነታቸው) ተደራራቢ የሆነ የወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ነው ዳኛ መላኩ የተናገሩት::
በአሁኑ ወቅት በግጭት ወይም ጦርነት ዐውድ በተዋጊዎች የሚፈፀሙ አስገድዶ መድፈርም ሆነ ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች እንደ ዓለምአቀፍ የጦር ወንጀል (war crime) እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ እንደ ዘር ማጥፋት ወይም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚታዩ ናቸው።
ከሀገራችን አኳያ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ የእሳቤ መዛነፎች፣ የአቀራረብ እጥረቶችና ጉድለቶች ቢኖሩበትም የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ በሴቶች እና በወንዶች ላይ የሚፈጸሙ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች በወንጀል የሚያስቀጡ ድርጊቶች እንደሆኑ ይደነግጋል። በተበታተነ ሁኔታም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ ወሲባዊ ድርጊት ፈጻሚዎችን ሊያስጠይቁ እና ሊያሰሩ የሚችሉ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች እንዳሉ አያከራክርም:: እነዚህን ድንጋጌዎች መሠረት አድርጎ ከመከላከል ጀምሮ ብዙ ሥራዎችን መሥራት የሚቻል መሆኑን ይጠቅሳሉ:: ያሉትን ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግም የወንጀል ምርመራ በፍርድ ቤት ፊት ክስ አቅርቦ ድርጊት ፈጻሚዎችን ለማስቀጣት እንደሚቻል ነው ያብራሩት::
ከወሲባዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ መሰረታዊ የወንጀል ሕጉ ክፍተት ያለበት ነው የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ለማሻሻል ምን ይሰራ ለሚለውም የመፍትሄ ሀሳብ ተመላክቷል ሲሉ ገልጸዋል። በዚሁ መሰረት የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ማሕቀፍን በተመለከተ እንዲሁም የወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎች የክርክር ሂደት ላይ ለሚሳተፉ ስልጠና መስጠት የሚሉትን በዋናነት ጠቅሰዋል።
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም