
ያኔ ከዛሬ 27 ዓመት በፊት በየዕለቱ የእድር ጡሩንባ መስማት አዲስ አልነበረም። በየአካባቢው በርካታ የኤች አይቪ ኤድስ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች አሉና። ዛሬ ማን ይሆን ብሎ መቅበር እስኪታክት እድርተኛው ተሰላችቷል። ባስ ሲል በአንድ ቀን ከአንድ በላይ ቀብር ይስተናገዳል። ከሚሞተውም በላይ በርካቶች አልጋ ይዘው አስታማሚ አጥተዋል። በርካታ ህጻናት ወላጅ አልባ ሆነዋል። በርካታ ወላጆች ይጦሩኛል ያሏቸውን ልጆች ተነጥቀው በእድሜቸው መጨረሻ የልጅ ልጅ አሳዳጊ እንዲሆኑ ተገደዋል። ያኔ ነበር የነገሮች አካሄድ ያልጣማቸው ወጣቶች በጋራ ሰብሰብ ብለው ስለጤናቸው ለመመካከር የወሰኑት። ኤች አይቪ ኤድስን ስለመከላከል ለመምከር የተሰባሰቡት።
የወጣቶቹ ስብስብ እራሳቸውንና ሌሎች ወጣቶችን ከኤች አይቪ ኤድስና ተዛማጅ የጤና ችግሮች መከላከልን ያለመ ነው። የዛሬ 27 ዓመት ጅማሬውን ሲያደርግ ሕይወት ጸረ-ኤድስ ማኅበር በኢትዮጵያ ይሰኝ ነበር። ሟቹም ታማሚውም በዝቶ ቢያዩ የበኩላችንን እናድርግ ብለው ተደራጁ። ይሁን እንጂ ስለበሽታው በቂ መረጃ አልነበራቸውም፤ እንዴት ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን እንደሚጠብቁ አያውቁም። ያኔ ከመስራች ወጣቶች መሃል የነበሩትና አሁን የሕይወት ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ጌታዓለም ካሳ እንደሚያስረዱት፤ በወቅቱ በአካባቢያቸው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶችን በመጠጋት ምን መስራት እንዳለባቸው ልምድ ቀሰሙ። ያኔ ከማሰልጠን መሰልጠን ይቀድማልና ሕብረተሰቡን በምን መልኩ ሊያግዙ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ሥልጠናዎችን ወሰዱ።
ወጣቶቹ አስፈላጊውን ስንቅ ከሰነቁ በኋላ የኤች አይቪን ስርጭትና በኤድስ ምክንያት የሚሞት ወገናቸውን ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ተንቀሳቀሱ። በተለይ ለወጣቶች ተስማሚ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ የኪነጥበብ መንገዶችን በመጠቀም በስፋት ሰሩ። በድራማዎች፣ በመዝሙር፣ በግጥም፣ በዘፈን፣ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ወጣቱና ሌላው የማኅበረሰብ ክፍል ግንዛቤ እንዲጨብጥ አደረጉ።
ያኔ ኤች አይቪ ኤድስ እንደጭራቅ ይሳል ነበር የሚሉት አቶ ጌታዓለም፤ ሰው ኤች አይቪ አለበት ከተባለ መድሎና መገለሉ ከፍተኛ ስለነበር የመከላከል ሥራቸው ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ያነሳሉ። ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች ጋር በጋራ መድረክ በማመቻቸት መገለልና መድሎን የሚቀንሱ ትምህርቶችና ስለቫይረሱ የማስተማር ሥራ እያዝናኑና ቁምነገር እያስጨበጡ ይሰሩ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ያኔ የነበሩት ወጣቶች የአስተሳሰብ አድማስ እየሰፋ ሲሄድ የወጣቶቹን እንቅስቃሴ ያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች እነሱን ለመደገፍ መነሳሳታቸው የተሻለ ሥራ ለመስራት እንዳስቻላቸውም ይጠቅሳሉ።
ከኤች አይቪ በተጨማሪ የሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ ሥርዓተ ጾታ ላይ መስራትና በተለያዩ መድረኮች የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማስፋት መቻላቸው ከወጣቶች ማሕበርነት ከፍ ያለ ሀገራዊ ሥራ መስራት እንደሚችሉ ተረዱ። አቅማቸውንም አወቁ። በዚህም አስፈላጊውን የምዝገባ ሂደት በማሟላት እ.አ.አ በ2000 ‹‹ሕይወት ኢትዮጵያ›› በሚል ስያሜ ሀገር አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት በመሆን መስራት የሚያስችል ምዝገባና ፈቃድ አገኙ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ እንደ አንድ ድርጅት ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣት ወደ እንቅስቃሴ ገቡ።
ሕይወት ኢትዮጵያ ጤና ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ከጤናም ኤች አይቪ ኤድስ ዋና የድርጅቱ ትኩረት መሆኑን ይናገራሉ። የወጣቶች ሥነ-ተዋልዶ ጤና ሌላው የድርጅቱ ትኩረት ነው። ወጣቶች ስለ ሥነ-ተዋልዶ ጤና ግንዛቤያቸው ከፍ ሲል ሌላው የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን ዝቅ ማድረጊያ መንገድ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት ተሰርቷል ይላሉ።
እንደ አቶ ጌታዓለም ማብራሪያ፤ ኤችአይቪ ትልቅ ጫና ከሚያደርስባቸው ዘርፎች አንዱ የትምህርት ዘርፍ ነው። ለዚህም በትምህርት ቤት ያሉ አካላት ስለኤች አይቪ ኤድስ በቂ መረጃ እንዲኖራቸውና ቫይረሱን ለመከላከል ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተከታታይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ተሰርተዋል። ድርጅቱ በተመሰረተበት ወቅት በኤድስ ምክንያት ወላጆችን በማጣትና መሰል ጫናዎች ምክንያት ትምህርት በተገቢው መልኩ አለመከታተልና ማቋረጥ ያጋጥም ነበር። ድርጅቱ ተማሪዎችን መደገፍ፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ትምህርት ቤቶችን ለተማሪዎች ምቹ በማድረግ ላይ በትኩረት ሰርቷል።
የኤች አይቪ ኤድስ ጉዳይ ከሥርዓተ ጾታ ጋር ይያያዛል የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ የጾታ እኩልነት መከበርን የተቋሙ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማምጣትና ጥቃትን ለመከላከል ዋናው ጥቃት አድራሻ የሆኑት ወንዶች የመፍትሄው አካል መሆን አለባቸው ብለው ያምናሉ፤ ለዛም ይንቀሳቀሳሉ። ሌላው የድርጅቱ ትኩረት የሕጻናትና ወጣቶች መብት መጠበቅ ነው። የሕጻናትና ወጣቶች መብትን ማስከበር እንዲቻልና ሕጻናትና ወጣቶች መብቶቻቸውን እንዲያውቁ የተለያዩ ሥልጠናዎች ይሰጣቸዋል።
ድርጅቱ ከሚሰጠው ሥልጠና በተጨማሪ በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ተሳትፈው ልምዶችን እንዲቀስሙና ለአቻዎቻቸው እንዲያካፍሉ ይደረጋል። የሕጻናትና የወጣቶችን መብት ከማክበር አንጻር በሀገሪቱ ሕጎች የተቀመጡና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ማክበር ያስፈልጋል። በመሆኑም ድርጅቱ እየሰራም ይገኛል ብለዋል።
በሀገራችን ድህነት ከባድ ጫና እያሳደረ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጌታዓለም፤ በተለይ ወጣት እናቶች ችግር ላይ ናቸው ይላሉ። በዚህም ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የማይልኩ፤ መመገብ የማይችሉ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት የማይችሉ መኖራቸውን ያነሳሉ። ይሄንን ለመፍታት የኢኮኖሚ ድጋፍ ያስፈልጋል። ለዚህም ሥልጠና በማሰልጠንና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ችግር ላይ ያሉ እናቶች እየሰሩ ልጆቻቸውን መደጎም የሚችሉበት ሁኔታ ይመቻቻል። ይሄ በሌላ መንገድ ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር ይያያዛል። ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ እናቶች የጸረ-ኤች አይቪ መድሀኒት ሲወስዱ ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ ተመራጭ በመሆኑ የኢኮኖሚ ድጋፍ በድርጅቱ እንደሚደረግም አንስተዋል።
እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የተነሳውን የእርስ በእርስ ግጭት ተከትሎ ድርጅቱ በሚሰራባቸውና ጦርነቱ ባለባቸው አካባቢዎች ሰዎች እየተፈናቀሉና ለችግር እየተዳረጉ ነው። ጥቃት ስደት ሲኖር ያልተፈለገ የግብረስጋ ግንኙነት ይኖራል። በዚህ የተነሳ የኤች አይቪ ኤድስ ተጋላጭነት ይጨምራል፤ አላስፈላጊ እርግዝናም ሊፈጠር ይችላል። በመሆኑም በዚህና መሰል ችግር ላይ ያለን ማኅበረሰብ መርዳት፤ ከትምህርት የራቁ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት መመለስና ወላጆችና ልጆች ወደቀያቸው እንዲመለሱ መርዳት ድርጅቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመረው ፕሮግራም ነው።
ድርጅቱ በሚሰራበት አካባቢ የወደሙ ትምህርት ቤቶች የትኞቹ ናቸው ምን ጎደላቸው? ምን ያህል ተማሪዎች አሉ? ምን ያህሉ ተሰደዱ? ምን ድጋፍ ይሻሉ? የሚለውን በመለየት ድጋፍ ያደርጋልም። ተፈናቃይ ዜጎች ቤታቸውን ጥለው ስለወጡ አልባሳትና መጠለያ ጭምር የላቸውም። ስለዚህ የድርጅቱ ድጋፍ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑትን ጭምር እንደሚያካትት ተናግረዋል። ከግለሰቦችም በተጨማሪ ለትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጋቸውንና የጎደላቸውን ግብዓት የማሟላት ሥራ መስራታቸውን ጠቅሰው፤ በደብረብርሃን፣ በሸዋሮቢት ጎንደር በሚገኙ መጠለያዎች ቀጥታ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ነገሮችን ያካተተ ድጋፍ መደረጉንም በአብነት አንስተዋል።
እንደ ሕይወት ኢትዮጵያ ሕጻናትና ወጣቶች ናቸው የኛ ትኩረቶች የሚሉት አቶ ጌታዓለም፤ ሕጻናትና ወጣቶች ጤናማ ደስተኛ፤ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ አስፈላጊውን ሥራዎች እንሰራለን። አለፍ ሲልም የሕጻናትና ወጣቶችን መብት የሚነኩ፣ ጤንነታቸውን የሚጎዳ ማንኛውንም አካል በፕሮግራሙ እንዲሳተፍ እናደርጋለን። ለሕጻናትና ወጣቶች ተስማሚ ሁኔታን መፍጠርና ጤናማ ደስተኛና አምራች ትውልድ ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት ራዕያችን በመሆኑ ይህንን በስፋት እንሰራበታለን ሲሉ አስረድተዋል።
ከሕግ አውጪና አስፈጻሚ አካላት፣ ከቤተሰብ ከሚዲያና አጠቃላይ በሕጻናትና ወጣቶች ዙሪያ ካሉ ተቋማትና ማኅበረሰብ ጋር ሥራዎችን በትብብር እንደሚሰሩ የሚገልጹት ሥራ አስፈጻሚው፤ ሕይወት ኢትዮጵያ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። ምክንያታቸውም ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያን እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በሚገባ አለማወቃቸው ነው። እናም ‹‹ሚዲያ ስማርት ዩዝ ኔትወርክ›› የሚል ተቋም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመመስረት እየሰሩ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።
ሕጻናትና ወጣቶች ምቹ አካባቢ እንዲኖሩ፤ ጤናማ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ከችግር ነጻ የሆነ ኑሮ እንዲኖሩና ተምረው ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎች ሊሆኑ ይገባል። ስለዚህም ያለእድሜያቸው የሚዳሩ ልጆች ቢያንስ ራሳቸው መወሰን እስኪችሉ ድረስ እንዳይዳሩ እንሰራለንም ይላሉ።
እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ አብዛኛው የድርጅቱ ገቢ ከውጪ በሚገኝ ድጋፍ (ፈንድ) የተገደበ ነበር። አሁን ግን የሀገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ አስፈላጊነት ታምኖበት የተሻለ የሀገር ውስጥ ሀብት የማሰባሰብ ልምድ ካላቸው ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅቶች ልምድ መቅሰም ተጀምሯል። ድርጅቱ የሀገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ እንዲችል በቅርቡ የሀገር ውስጥ ሪሶርስ ሞብላይዜሽን ቡድን አቋቁሟል። የድርጅቱ መስራቾች የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በመሆን ቀጥለዋል። ከዛ በተጨማሪ ድርጅቱ ውስጥ በተለያየ ጊዜ አገልግለው የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በሰላም ከድርጅቱ የለቀቁ አባላት የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ አባል የሚሆኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል። እነዚህ አባላት ከጠቅላላ ጉባኤ አልፈውም እስከቦርድ የሚያገለግሉበት ሁኔታ አለ። ሰዎች የድርጅቱ ባልደረባ እንዲሆኑ ሰልጥነዋል፣ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ እውቀት ወጥቶባቸዋል። ምንም እንኳን የተሻለ ነገር ፍለጋ ቢሄዱም በልምዳቸው እንዲያገለግሉ ሁኔታዎች ተመቻችቷል።
በተለያየ ጊዜ ከሀገር ውስጥ በጎ ፈቃደኞች በተጨማሪ ዓለምአቀፍ በጎ ፈቃደኞች ከድርጅቱ ጋር እንደሚሰሩ የሚያነሱት አቶ ጌታዓለም፤ በማኅበረሰቡ ውስጥም ከድርጅቱ ጋር የሚሰሩ የሕጻናት የወጣቶች ክበባትና የማኅበራት አደረጃጀቶች መኖራቸውን በማንሳት የኛ ሥራ ማስተባበር ነው ብለዋል። አብዛኛው ሥራ በበጎ ፈቃደኞች እንደሚሰራም አንስተዋል። ለአብነትም በሰሜን ሸዋ ‹‹ኮሚኒቲ አክሽን ቲም›› ተብሎ የተሰየመ ያለእድሜ ጋብቻን የመከላከል ፕሮግራም መኖሩንና ዋናው ሥራ በእነሱ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ከሕግ አካላት፣ ከሀይማኖት አባቶች ከሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ቢሮዎች ጋር በመሆን በየቦታው እንዲህ አይነት አደረጃጀቶችን በመፍጠርም እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በእነርሱ በኩል አስፈላጊውን ግብአት በማሟላት ሥልጠና በመስጠትና ቴክኒካል ድጋፍ በማድረግ ሥራው በፈቃደኝነት በማኅበረሰቡ እንዲሰራ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
ሕይወት ኢትዮጵያ የተመሰረተው በበጎ ፈቃደኞች በመሆኑ የበጎ ፈቃድ ሥራን ያበረታታል። ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ሥራ እንዲያልፉ ይፈልጋል። ይህ መሆኑ ደግሞ በበጎ አድራጎት ድርጅቱን ከማገልገል ጀምረው ድርጅቱን የተቀላቀሉ ሠራተኞች እንዲኖሩ አስችሏል። ድርጅቱና ሌሎች በሰሩት ሥራ የኤች አይቪ ኤድስ እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ መጥቷል ብለው እንደሚያምኑ የሚያነሱት ሥራ አስፈጻሚው፤ ሆኖም ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ በመከሰቱና በሀገራችን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በኤች አይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዳይጨምር ስጋት አላቸው። የዚህ ምክንያቱም የመንግስት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የሚዲያና የሌሎች አካላት ዋና ትኩረት ወደ ሰብአዊ ድጋፍ እየዞረ መሄዱ ነው። ስለሆነም የኤች አይቪ ኤድስ ጉዳይ ወደ ኋላ እንዳይቀርና የቀደመው ታሪክ እንዳይደገም ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም