
ለሳምንታት በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሲሠሩ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ንግግር አለመደሰታቸውን እና እጅግ መበሳጨታቸውን ተናገሩ:: ኤንቢሲ ከተባለው ጣቢያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካው መሪ ፑቲን የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ተአማኒነት ላይ ትችት በመሰንዘራቸው መናደዳቸውን ተናግረዋል::
ትራምፕ በበኩላቸው፤ ፑቲን የተኩስ አቁም ስምምነት ካልፈረሙ ከሩሲያ ነዳጅ የሚገዙ ሀገራት ላይ የሃምሳ በመቶ ታሪፍ ለመጣል መሰናዳታቸውን ገልጸዋል:: ‹‹በዩክሬን ያለውን ደም መፋሰስ ለማስቆም እኔ እና ሩሲያ ከስምምነት የማንደርስ ከሆነ እና የሩሲያ ጥፋት ነው ብዬ ካሰብኩ ከሩሲያ የሚወጣ ነዳጅ ላይ ታሪፍ እጥላለሁ›› ማለታቸው ተሰምቷል::
ትራምፕ የሰጡት አስተያየት በሩሲያ ጉዳይ ያላቸው አቋም መለወጡን የሚያሳይ ነው የተባለ ሲሆን ዋይት ሃውስ ፕሬዚዳንቱ ባሰሙት ንግግር ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል:: የአውሮፓ መሪዎች ትራምፕ በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ጉዳይ ላይ የፕሬዚዳንት ፑቲንን አቋም እያንጸባረቁ ነው ሲሉ መተቸታቸው ይታወሳል::
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ትራምፕ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪን ወደ ኦቫል ኦፊስ በመጥራት በቀጥታ በተላለፈ ስርጭት እሰጣ አገባ ውስጥ ገብተው እንደነበር ሲታወስ በሌላ በኩል ትራምፕ የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ስም ሲያወድሱ እንደነበር ይታወቃል:: አሜሪካ በዩክሬን ተኩስ አቁም ጉዳይ ላይ ሩሲያን ስትወቅስ እና ዛቻ ስታሰማ ይህ የመጀመሪያዋ ሲሆን ከሩሲያ የሚመጣው ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል እየተጠበቀ ይገኛል::
ምንም እንኳን ትራምፕ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ አምባገነን መሪ ናቸው፣ ምርጫ ሊካሄድ ይገባል ብለው ወቅሰው ቢያውቁም ከኤንቢሲ ጋር በነበራቸው የስልክ ቃለ ምልልስ ፑቲን የዘለንስኪን ተአማኒነት በመውቀሳቸው መናደዳቸውን አልሸሸጉም:: ትራምፕ ስለፑቲን ሲያወሩ መበሳጨታቸውን ክሬምሊን እንደሚያውቅ ጠቁመው ነገር ግን ከሩሲያው መሪ ጋር በጣም መልካም ግንኙነት እንዳላቸው በመናገር እሱ ትክክለኛውን ነገር ካደረገ ብስጭቱም ብን ብሎ ይጠፋል ሲሉ ተደምጠዋል::
ፑቲን በዚህ የማይስማሙ ከሆነ ግን ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ትራምፕ ዝተዋል:: ከሩሲያ ነዳጅ በሚገዙ ሀገራት ላይ ሃምሳ በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉም ገልጸዋል:: ከሩሲያ ብዛት ያለው ነዳጅ የሚገዙ ሀገራት ቻይና እና ህንድ ናቸው:: ዘለንስኪ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ‹‹ሩሲያ ምክንያት እየፈለገች ይህ ጦርነት እንዲራዘም ነው የምትፈልገው›› ብለዋል:: ትራምፕ በበኩላቸው በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ከፑቲን ጋር እንደሚመክሩ ገልጸዋል::
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቆይታ ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ ባይፈቅድላቸውም ለሶስተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት የመወዳደር ሃሳብ እንዳላቸው ገልጸዋል:: ‹‹በጣም ብዙ ሰዎች ያን እንዳደርግ ይፈልጋሉ:: ያው እንግዲህ ለዚያ ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅብናል›› ብለዋል::
በሌላ በኩል ኢራን የኒውክሌር ስምምነት ካልተፈራረመች ቦምብ እንደሚጥሉባት የተናገሩ ሲሆን ለኢራን አገዛዝ በጻፉት ደብዳቤ ድርድር ያስፈልጋል ሲሉ መጠየቃቸው አይዘነጋም:: ነገሮች መልካቸውን ከመቀየራቸው በፊት ወደስምምነት መግባት አዋጭ መሆኑን ጠቁመዋል:: የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን እሁድ እለት በሰጡት አስተያየት ከዋሽንግተን ጋር ቀጥተኛ ድርድር ውስጥ ባይገቡም በሶስተኛ ወገን ውይይት ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል::
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በአሸማጋይነት የገቡት ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም አወርዳለሁ ማለታቸው ይታወሳል:: ገና ከበአለ ሲመታቸው ጀምሮ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን በመወሰን መነጋገሪያ የሆኑት ትራምፕ በዩክሬን ጉዳይ በፑቲን ማዘናቸውን ገልጸዋል:: መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል::
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም