
በዓባይ ውሃ አጠቃቀም እና የሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ አስራ አራት ዓመታትን ያስቆጠሩ ንግግሮች አለፍ ሲልም ክርክሮች እና ድርድሮች ተካሂደዋል:: የኢትዮጵያ ባለውለታ ብርቅ የኢትዮጵያ ልጆች ከጦርነት ባልተናነሰ መልኩ ቀን እና ለሊት ያለእንቅልፍ ከሁለት በኩል ሲሰነዘርባቸው የነበሩ ሃሳቦችን ተፋልመው፤ ታላቅ ተጋድሎ ፈፅመው ድል አስመዝግበዋል::
በእነዚህ ዕልህ አስጨራሽ ድርድሮች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከነበሩ ምሁራን መካከል ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ መምህርና ተመራማሪ ረ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶክተር) እና የውሃ ኃብት የአስተዳደር የግል አማካሪ አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ተጠቃሾች ናቸው::
እነዚህ ምሑራን ያለመታከት እና በየድርድሩ ተከታታይ ቀናትን በሚፈጀው ሂደት በአፍሪካ ሕብረት፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬት አስተባባሪነት እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በተለያዩ ጊዜያት ዓመታትን የፈጁ ንግግሮችና ድርድሮች ሲያካሂዱ ምሁራዊ አበርክቷቸውን አድርገዋል::
የድርድር ሂደቱን አስመልክቶ ተደራዳሪው አቶ ፈቅ አህመድ እንደተናገሩት፤ ግብፆች ቀድመው የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጀመር ወደ ድርድር የገቡት ተለሳልሰው ስለነበር አጀማመሩ ከባድ አልነበረም:: ‹‹መረጃ ይሰጠን›› ብለው ሲጠይቁ እንኳ፤ በፍራቻ ኢትዮጵያ መረጃ አልሰጥም ትላለች ብለው ስጋት ውስጥ ሆነው ነበር:: ሆኖም እየቆዩ የኢትዮጵያን ሃቅ ለማዛባት ጥረት ማድረግ እና ተለዋዋጭ ሃሳብ በመያዝ በየጊዜው ችግር ውስጥም ቆዩ::
እንደ አቶ ፈቅአሕመድ ማብራሪያ፤ ግብጾች፣ የሶስቱ አገራት ባለሙያዎች አንድ ላይ ግድቡን ያጥኑ የሚል ጥያቄ አቀረቡ:: በነበረው ሂደትም ትልቅ ጭቅጭቅ የነበረበት፤ አንዳንዴም ግብፆች መድረኮችን ረግጠው ሲወጡና፤ ተለምነው እየገቡ ንግግር የሚካሔድበት ሁኔታም ነበር:: ይሄም ሳይበቃቸው እንደገና የውጪ ባለሙያዎች ይግቡበት የሚል ጥያቄ አቀረቡ::
‹‹ግብፆች ጥያቄ ሲያቀርቡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በተደጋጋሚ በጎ ምላሽ ሲሰጣቸው ቆይቷል::›› ያሉት አቶ ፈቅአሕመድ፤ እንደዚያም ሆኖ አራት የውጪ ባለሙያዎች ተካተው በዓመቱ ብዙ ምርምር እና ጥናቶች ከተካሔዱ በኋላ ውጤቱ መውጣቱን፤ በዚህም ሶስቱም ሀገራት እና ባለሙያዎቹ የሚፈርሙበት ሪፖርት መዘጋጀቱን ያስረዳሉ:: በዚህ ጊዜ ሱዳን በጥናቱ አምና ከፍተኛ መለሳለስ ማሳየቷን፤ ግብፆች ግን በተቃራኒው ሴራ ላይ ማተኮራቸውን አቶ ፈቅአሕመድ ያስታውሳሉ::
‹‹ከኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጋር ሆነው ኢትዮጵያ ላይ በመዶለት፤ ግድቡን እንዴት እንደሚያወድሙ እና እንደሚደበድቡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ረብሻ እንደሚያስነሱ፤ እንዴት ጉቦ ሰጥተው ባለሙያዎች የሀሳባቸው ተገዢ ማድረግ እንደሚችሉ ሲመክሩ እንደነበር ተደርሶባቸዋል:: የሚሉት አቶ ፈቅአሕመድ፤ ግብፆች ሀዲዱን ለማደናቀፍ እና የተሳሳተ መረጃ እንዲወጣ ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን ሲጠቀሙም፣ ችግር ሲፈጥሩ እንደነበር፤ ይሄንኑም በቀጥታ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ዓለም እንደሰማ አስታውሰዋል::
ከሴራቸው ባሻገር ጥናቱ ከተካሔደ በኋላ በግብፅ በኩል ሁኔታዎች የበለጠ አስቸጋሪ ሆነው መቀጠላቸውን የገለፁት ተደራዳሪው አቶ ፈቅአሕመድ፤ ግብፆች ትልቅ ጭቅጭቅ ከመፍጠር እስከ ውይይቶችን ረግጦ እስከመውጣት የደረሰ የማደናቀፍ ሥራን ሲፈጽሙ እንደነበር ይገልፃሉ:: አለፍ ሲልም በድጋሚ ይጠና የሚል ጥያቄ አቅርበው እንደገና የተወሰኑ ጥናቶችን ለማካሔድ ገንዘብ ተከፍሎ አማካሪ ተቀጥሮ መሠራት ተጀምሮ እንደነበር በመጠቆምም፤ ይሄም ቢሆን እንደማያዋጣቸው ሲያውቁ ውድቅ ማድረጋቸውን ለጉዟቸው አስቸጋሪ እንደነበሩ አብነት ይጠቅሳሉ::
በዚህ እልህ አስጨራሽ በነበረው ሂደት ውስጥ ተደጋግሞ የሚገለፀው የግብጽ ተለዋዋጭ ባህሪ፣ በኋላ ላይ ድጋሚ አገርሽቶ በራሳቸው በሶስቱ ሀገራት ምሁራን እና ተደራዳሪዎች ጥናት ይካሄድ የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን፤ የራሳቸው ተመራማሪዎች ሳይቀሩ የተሳተፉበትን ጥናት ሲጨረስ እንደገና ውድቅ ማድረጋቸውን፤ ይህ ተለዋዋጭ ሃሳባቸውም ሂደቱን ፈታኝ አድርጎት እንደነበርም ነው ተደራዳሪው አቶ ፈቅአሕመድ የሚናገሩት::
ከዚህም በላይ ግብፆች ከሶስቱ ሀገራት በተጨማሪ አሜሪካ እና ዓለም ባንክ ድርድሩ ላይ እንዲሳተፉ በመገፋፋት፤ ኢትዮጵያ በቀጣይ በዓባይ ውሃ እንዳትጠቀም የሚያደርግ ስምምነት ለማስፈረም ብዙ ሞክረው የሞከረችበትን አካሄድ፤ እነዚህ ግብፅ ስትሔድባቸው የነበሩ መንገዶች ምን ያህል ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ የመጠቀም ብሔራዊ መብት እንዳይኖራት አስበው ሲሰሩ እንደነበርም አብራርተዋል::
ሆኖም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች፣ የዘርፉ ምሁራን እና መንግሥት በተለያየ አቅጣጫ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ግብፆች ሃሳባቸው ውድቅ እንዲሆን ማድረግ መቻላቸውንም ተናግረዋል:: እንደተደራዳሪው አቶ ፈቅአሕመድ ገለፃ፤ በዚህ ያላቆሙት ግብፆች ጉዳዩን ከውሃ ፖለቲካነት አሳልፈው ባልተለመደ መልኩ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲደርስም ሰርተዋል::
ግብፆች ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ይውሰዱት እንጂ፤ ለዓለም አቀፍ ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ነው በሚል፤ እዚያም ከደረሰ በኋላ ወደ አፍሪካ ሕብረት የተመለሰ መሆኑን በማብራራት፤ በሂደቱ የግብፅ ሙግት ምን ያህል የተካረረ እንደነበር አስታውሰዋል::
‹‹የአረብ ሊግንም ተጠቅመው ጫና ለመፍጠር ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ምንም ማምጣት አልቻሉም:: ›› ያሉት አቶ ፈቅአህመድ የኢትዮጵያ የውሃ ዘርፍ ምሁራኖች በሠሩት ትልቅ ሥራ ግብፅ ብዙ ብትሮጥም ውጤታማ የምትሆንበትን ዕድል መዝጋት መቻሉን፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ እንድትደርስ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል::
ይህ ሁሉ ውጤት የመጣው በጥቂት ሰዎች ሳይሆን፤ ቀድሞም ቢሆን ልክ ግድቡ እንደተጀመረ የብሔራዊ ትምህርቶች ፓናል በመቋቋሙ እና ፓናሉ ሀገሪቷ ውስጥ ያሉ ከተለያዩ መንግሥታዊ ከሆኑ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ 20 የሚደርሱ የውሃ ዘርፍ ባለሙያዎች እና በተለያየ ዘርፍ ላይ ትልቅ ልምድ እና ተሞክሮ የነበራቸው ባለሙያዎች ሁሉንም ሥራ በመሥራታቸው መሆኑን አሳውቀዋል::
ተደራዳሪው አቶ ፈቅአሕመድ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ባለሙያዎች በፓናል ለዘጠኝ ዓመት ያህል ከግድቡ ጋር ተጉዘዋል:: በጉዟቸው ግድቡን በተመለከተ እያንዳንዱን ጉዳይ ይከታተሉ ነበር:: ከባድ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ለሶስት እና አራት ቀን ከከተማ ወጥተው ቀኑን ሙሉ በመስራት ሪፖርት ያደርጉ ነበር:: በየሳምንቱ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽት 4 ሰዓት ተሰብስበው አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ይወያዩ ነበር::
የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ባለሙያዎች ፓናል በዋነኝነት በሙያ ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ መስጠቱን አስታውሰው፤ በመንግሥትም በከፍተኛ ደረጃ ክትትል የሚደረግ መሆኑን፤ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድም በቅርብ ሲከታተል መቆየቱ፤ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግድቡ በኋላ መቆሙ ለተደራዳሪዎች ትልቅ ግብዓት እና አቅም ሆኖ ነበር ይላሉ::
ይሄ ማለት ግን ፈጽሞ ስህተቶች አልነበሩም፣ ችግር አልተፈጠረም ማለት አይደለም:: ስህተቶች ይኖራሉ የሚሉት ተደራዳሪው አቶ ፈቅአሕመድ፤ ስህተቶች ሲያጋጥሙ ወዲያው የመፍትሔ ርምጃዎች እየተወሰዱ ውጤት መምጣቱን ይናገራሉ:: አንዳንዴ ፈተናዎች ከውጪ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም እንደነበሩ በማስታወስ፤ ከውስጥ በነበረ ችግር ምክንያት የግንባታው በጊዜ አለመጠናቀቅ ድርድሩ ላይም ችግር ፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳሉ::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ መምህር እና የአባይ ውሃ ተደራዳሪ ረ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶክተር) በበኩላቸው፤ ጉዳዮችን በደንብ ነቅሰው ማውጣት በመቻላቸው እና ኢትዮጵያ አቋሟን በምን ዓይነት መንገድ መግለፅ እንዳለባት በመተማመን፣ እንዲሁም በጥበብ እና በዕውቀት ላይ በመመስረታቸው ድርድሩ የተሳካ መሆን ችሏል ብለዋል::
ድርድሩ የተጀመረበትን ሁኔታ ሲያስታውሱ፤ ቀድመው ግድቡን መሥራት የኢትዮጵያ መብት መሆኑን ተግባብተዋል:: ስለዚህ ገና መሬት ላይ መሠራት ሲጀምር ለግንባታው የማንንም የሌላ አገር ስጦታ፣ ርዳታም ሆነ ተፅዕኖ ሊኖር እንደማይገባ አረጋግጠው ወደ ድርድር መግባታቸውን ተናግረዋል::
‹‹በድርድሩም በዋናነት ጠብቀን ስንከላከል የነበረው ኢትዮጵያ በግብፅም ሆነ በሌሎች አገሮች የመገንባት መብቷ ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ነበር::›› ሲሉ የድርድሩ ማጠንጠኛ የኢትዮጵያን መብት ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ተፅዕኖ ላይ እንዳትወድቅ መከላከል እንደነበር ተደራዳሪው ዶክተር ያዕቆብ አሳውቀዋል::
ኢትዮጵያ ተፅዕኖ ሥር ሆና ምንም መሥራት እንደማትችል ተደራዳሪዎች መግባባት ላይ በመድረሳቸው፤ ተፅዕኖ ለመጋፈጥ እውቀት ላይ ተመሥርተው አስፈላጊ መረጃዎችን ለማቀናጀት እንዲሁም በድርድሩ አውድ ላይ እርስ በርሳቸው ለመመካከር ረዥም ጊዜ ይወስዱ እንደነበር አመላክተዋል::
እንደተደራዳሪው ረ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶክተር) ገለፃ፤ አካሔዳቸው ስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ በመተማመናቸው፤ግብፅ አስቀድማ ኢትዮጵያ እንድትፈርምባቸው የምትፈልጋቸው ጉዳዮች በምንም ዓይነት መስኮት ቀዳዳ እንዳያገኙ ማድረግ ችለዋል::
የድርድሩ ማጠንጠኛ ግድቡ በኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛት ውስጥ የሚገነባ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ሙሉ መብት እንዳላት ግብፆችም ሆኑ የግብፅ ወገኖች እንዲረዱት ለማድረግ አቅደው በመሥራታቸው ድርድሩ መሳካቱን አብራርተዋል::
ሆኖም በዋናነት ግብፅ፣ በተባባሪነትም ሱዳን ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፤ በተለይ አንዳንድ የአረብ ሀገራት እና ግብፅን በወዳጅነት የሚያዩ ሀገሮች ጫና በኢትዮጵያ ላይ ሲያርፍ እንደነበርም ጠቁመዋል::
‹‹ግብፆች የቅኝ ግዛት ስምምነታቸው ላይ ተመርኩዘው ሱዳኖች እና እነርሱ ብቻ መጠቀም ይፈልጉ ነበር::›› ያሉት ተደራዳሪው ረ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶክተር) ፤ ግብፆች ደጋግመው ይገልፁ የነበረው እና ይዘው የመጡት ሃሳብ ስምምነቶቹ እንዲፀኑ የሚሉ ነበሩ:: በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ደግሞ እነዚያ ስምምነቶች ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት በመሆናቸው ኢትዮጵያን አይመለከቱም:: ኢትዮጵያ እነዚያ ስምምነቶች አሉ ብሎ መቀበል ቀርቶ፤ ስምምነቶች የሚያስቀምጧቸው መብቶች የኢትዮጵያን መብቶች የሚፃረሩ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ይህንን ሊቀበሉ አይችሉም በማለት ግብፆች አቋማቸውን እንዲቀይሩ ሲታገሉ እንደነበር አስታውሰዋል::
በብዙ መልኩ በኋላ ሲያከራክር የነበረውን ጉዳይ ሲያስታውሱ፤ ግብፆች በተቻላቸው ሁሉ በድርድሩ ላይ አሞላሉን እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲወስኑ፤ ግድቡ ከእነርሱ ጋር አብሮ እንዲተዳደር እና ይህንን ሃሳባቸውንም ኢትዮጵያ እንድትቀበል በተጨማሪ በየጊዜው ከግድቡ ጋር የተያያዘ መረጃ ኢትዮጵያ በነፃ እንድትሰጣቸው እና በእነርሱ በኩል ያለውን መረጃ እንዳትቀበል የመሳሰሉት ፍላጎት እንደነበራቸው ተደራዳሪው ረ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶክተር) ተናግረዋል::
ኢትዮጵያ ራሷን በሚጠቅም ሌሎችን በማይጎዳ መንገድ ውሃውን ትሞላለች እንጂ፤ የግብፅን ተፅዕኖ ተቀብላ እንደማትፈፅም ለማሳመን ብዙ ተሠርቷል ሲሉ አብራርተዋል:: ‹‹ግድቡን አብረን እናስተዳድር የሚለውም ጭራሽ ሊሆን የማይችል መሆኑን እና ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሠራችውን ግድብ ሌሎች መጥተው ሊያስተዳድሩት እንደማይችሉ አስገንዝበናል›› ብለዋል::
በኢትዮጵያ በኩል የተደራዳሪዎቹ ዕውቀት ክህሎት እና የሀገር ፍቅር፣ የመንግሥት ያልተቆጠበ ክትትል እንደዚሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያደርግ የነበረው ድጋፍ በተጨማሪ ሕዝቡ ተደራዳሪዎችን እና መንግሥትን የሚጠብቅበት ሁኔታ በአንድ ላይ ድርድሩ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ የኢትዮጵያ መብት እንዲከበር እና ግድቡ እንዲጠናቀቅ ያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል::
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ልጆች ብልሃት በተሞላበት መልኩ ብዙ ችግሮችን ተቋቁመው ለሀገራቸው በፅናት ቆመው ታይተዋል:: የቃላት ጦርነቱን በብልሃት ተወጥተው ዋናውን የኢትዮጵያ ጥቅም አስከብረዋል:: ይህንን ተከትሎ ምሁራኖቹ እንደጠቆሙት፤ ያ ሁሉ ችግር አልፎ ግድቡ ለዚህ መብቃቱ እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን አመልክተው:: የነበሩት ድርድሮች እና የታለፉባቸው መንገዶች አጠቃላይ ሁኔታው ተቀምሮ ለወደፊት መማሪያ መሆን አለባቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ገልፀዋል::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም