ባሕልና ጥበቦቻችን – ለአብሮነታችን

የ “ስለኢትዮጵያ” አጀንዳዎችና ሁነቶች መለያው እየሆነ በመጣው በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት “አብሮነት ስለኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የሚካሄደውን የፓናል ውይይት ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ልጆች የሰላም፤ የአብሮነት ተምሳሌት በሆነችው ሐረር ከተማ ላይ ተሰባስበዋል፡፡ በዕለቱም ስለ አብሮነት ሊመክሩ በአንድ መድረክ በአንድነት ተቀምጠዋል፡፡

ሰማንያ አራት ዓመታትን የመረጃ ምንጭም፣ የታሪክ ሰነድም ሆኖ ስለ ሕዝብ ሲሠራ የቆየው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በዚህ መድረክም፣ የወይና ደጋ የአየር ጠባይ በተላበሰችው ውብ ከተማ ኢትዮጵያዊያን ስለኢትዮጵያ እንዲመክሩ አሰባስቧል፡፡ የራሱ የሆነ ባሕል፣ የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ሥነ ልቦናዊ ዘይቤ እና መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር ያለው የሐረር ሕዝብም ይህንን ድግስ ተቀብሎ በሚገባ አስተናግዷል፡፡ የውቧ ሐረር መገለጫዎች ተዘርዝረው የማያልቁ በመሆናቸው እያንዳንዱን ለመጥቀስ ከብዶልና ሰዎች በዓይናቸው አይተው በአፍንጫቸው አሽተው በእጃቸው ይዳስሷቸው ዘንድ ጥቂቶቹን እንዲያዩም ግብዣዎች ተደርገዋል፡፡

ታሪክ እየሰነደ መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ከተማይቱን የመረጠው ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ከምትከሰትባቸውና ከምትገለጥባቸው ከተሞች መካከል ሐረር አንዷ በመሆኗ ነው፡፡ ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎሉ ጉዳዮችን በማንሳት በተለይም “ስለኢትዮጵያ” በሚል ስያሜ የፓናል ውይይትና የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ በሐረር ከተማ መካሄዱም ለዚሁ ነው፡፡ ሐረርም የሚመጥናትን ሁነት አስተናግዳ በልኳ ተገልጣበታለች፡፡

ምክንያቱም፣ እንደ ብሂሉ ሀሁ ሐረር የፍቅር ከተማነቷ፣ የአብሮነት መድረክነቷ በተሳታፊዎች በደንብ መዳሰስ ችሏል፡፡ ርግጥም በጎ ባሕልን ለአብሮነት መጠቀም እንዴት ይቻላል? በሚል የሚጠይቅ ቢኖር፤ ሐረርን መጎብኘትና መገንዘብ በቂ መሆኑን አሳይታለች። ለዛሬው የሀገርኛ ዓምድ ጉዳያችንም በዚህችው ከተማና በተጠቀሰው ሁነት ላይ “ስለ አብሮነት” ምን ተባለ? የሚለውን ከተወያዮች አንደበት አድምጠን ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ በተለይ እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን ባሕል አለን፤ ባሕላችን በጎነትን እንዴት ያሳያል፤ አብሮነትን እንዴት ያጠነክራል፤ እንዴትስ ወደፊት ያሻግረናል፣ የሚልና መሰል መሠረታዊ ጉዳዮችን እንዳስሳለን፡፡

መርሐ ግብሩን የመሩት የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚንስትሯ ሸዊት ሻንካ የመድረኩን ዋና ዓላማ በስፋት አብራርተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ሃሳብም፤ መድረኩ በአንድ በኩል ውይይትና የመነጋገር ባሕል እንዲዳብር ሲያስችል በሌላ በኩል ብሔራዊ ትርክት እንዲኖርና እንዲገነባ ያደርጋል፡፡ መርሐ ግብሩ ሀገራዊ መሆኑና የኢትዮጵያ ከተሞችን ያካለለ ተደርጎ መሠራቱ ሀገርን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስተዋወቅም ያግዛል፡፡ ያሉንን ባሕላዊ ሀብቶችን አውቆ ጥቅም ላይ ለማዋልም ያስችላል፡፡

ለታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሮዛ ዑመር በበኩላቸው እንዳሉት፤ በተለያየ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ብዝሀ -ማንነት ያለን ኢትዮጵያዊያን በጋራ ለምንገነባው ሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት፣ ንግግር፣ ውይይትና ምክክር ወሳኝነት አለው፡፡ ባሕላችን ደግሞ በዚህ ንግግራችን ውስጥ አንዱ መሆኑ የበለጠ ለመግባባት በር ይከፍትልናል፡፡

ባሕል ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ተቀራርበው ሃሳብ እንዲለዋወጡ የሚያስችልም ዓይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡ ስለሆነም ባለ ብዙ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና የተለያዩ የማንነት መገለጫ እሴቶች ያለን እንደመሆናችን መጠን ይህንን አዳብሮ ለአንድነት መገንቢያ መጠቀሙ ኢትዮጵያዊያንን በሰለጠነ መንገድ ለማራመድ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱና የተሻለ እድልን ለዜጎቻቸው እንዲሰጡ ያስችላልም፡፡

ለዚህም ተወላጆቿ ብቻ ሳይሆኑ ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የመጡ ሕዝቦች ለሺህ ዓመታት ተፋቅረው፤ ተከባብረውና ተቻችለው የኖሩባትን እና እየኖሩ ያሉባትን የአብሮነት፣ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጇን ሐረር ከተማን በማሳያነት ማቅረብ ይቻላልም ነው ያሉት ወይዘሮ ሮዛ፡፡ ሐረር በመንግሥታቱ ድርጅት የባሕል፤ የትምህርትና የሳይንስ ማዕከል (በዩኒሲኮ) በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ ካስቻላት አንዱም እንዲህ ዓይነቱ ሕዝባዊ ባሕልና ሰላም የሰፈነባት ከተማ መሆኗን ጠቁሟል፡፡

በሐረር አንዱ የአንዱን ቋንቋ ይለምዳል፣ አንዱ የአንዱን ባሕል ያውቃል፣ ያከብርና በሰላምና በፍቅር መስተጋብር ተሳስሮ ይኖራል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዲህ ዓይነቱን እሴት በማስፋትና በማስቀጠል ለአብሮነት ለመጠቀም ፍቅር ወደ ነገሰባት ታሪካዊቷ ሐረር ከተማ መዝለቁ በብርቱ የሚያስመሰግነው ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

የዚህ መርሐ ግብር መድረክ አስተዋዋቂ በመርሐ ግብሩ እንዳለው፣ ባሕል የሀገር ነፍስ፣ ጥበብ ድምፁ ሲሆን፣ ስፖርት ልብ ትርታ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት መንታ መሰል ኃይሎች በአንድነት ሲሰባሰቡ ጠንካራ አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ቀርጸው ያወጣሉ። በመሆኑም ባሕሉ እንዲጠበቅና የዳበረ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ከምንም በላይ የማኅበረሰቡ መስተጋብር እንዲጠናከር ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እንደነዚህ ዓይነት ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ይሄ ዓይነቱን ኢትዮጵያዊነት የተላበሰ እሴት አርተር ራምቦን ከውቢቱ የፈረሳይ ከተማ ፓሪስ ወደ ሐረር ማስኮብለሉ፤ አያ ጅቦንም በፍቅሩ ነድፎና አሸንፎ በማላመድ አውሬነቱን ማስተው ሳቢና ማራኪ በሆነ መልኩ በመነባንብ ተገልጿል፡፡

በመርሐ ግብሩ ነዋሪዎቿ ራሳቸው ሙስሊምና ክርስቲያኑ እንዴት በእድሩ፣ በሰደቃው፣ በሰርጉና በሌላውም ልዩነቱ እንደተጠበቀ እንዴት የአንድነትና አብሮነቱን መስተጋብር እንደሚያጠናክር ልምዳቸውን ለታዳሚው አካፍለዋል፡፡ አቦ! እንደዚህ እኮ ነን እኛ፤ እንዲህ እናደርጋለን እያሉ የፍቅርና የአብሮነት ተምሳሌት የሚያደርጋቸውን ሁሉ ዘርዝረዋል፡፡

እንኳን ሰውና ግንድ ይጋጫልና አይጣሉም የሚላቸው የለም፤ እነሱም አንጣላምም ሆነ መቼም ጊዜ ተጣልተን አናውቅም አይሉም፡፡ ምክንያቱም ከቂምና በቀል ነፃ የሆኑ የዋህና ተቻችለው የሚኖሩ ናቸውና ሁሉን ረስተው ወዲያው ማንም ሳያስታርቃቸው በመነጋገራቸው ጠባቸው “የቁርስ ኩርፊያ ከምሳ አያልፍም” እንደተባለው በብርቱ የቀለለ ነው፡፡

በደምሳሳው ስለ ሐረር በምህታታዊ ፍቅሯ በማልመድ ከሰው ጋር ቀርቶ ከጅብ ጋራ መኖራቸውንና አንድ እንጀራ ለአሥር ተካፍሎ የሚበላባት እንግዳ ተቀባይ መሆኗን “አቦ” የሚሉት የማይዳሰሰው ፍቅር፤ የሚዳሰሰው ጀጎል ነዋሪዎቿ መስክረውላታል። ሰው በሃይማኖት ተለያይቶ በሰውነት የሚፋቀርባት ስለመሆኗም የነብዩን ሀዲስ ከምድር ሀይቆች ጋር አቆራኝተው የሚጠበቡት እነ ሊቃነ አባድር ይናገሩላታል፡፡

ያኔ ሃይማኖት ከመምጣቱና ቁርአን ቅዱስ መጽሐፍ ከመውረዱ፤ በፊትም ሰው በሰውነቱና በፈጣሪ ፍጡርነቱ እርስ በርሱ ተሳስቦና ተፈቃቅሮ ይኖርባት የነበረች ስለመሆኗም ያነሱላታል፡፡ ሐረር ለዘመናት በኢትዮጵያ ስር ሰድዶና ባሕል መስሎ የቆየው የመገፋፋትና የመጠላላት አሜከላ ያልወረሳት ስለመሆኑም እንኳን ነዋሪና ተወላጆቿ እንግዳ ይናገርላታል፡፡

በዚህ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ መኳንንት ተፈራን ጨምሮ፣ ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ፤ የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሮዛ ዑመር፣ የፌዴራልና የክልል አመራሮች፤ ሚኒስትር ዴኤታዎች፤ ምሁራኖች፤ ከኢፌዴሪ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ባህል፣ ስፖርትና ባሕላዊ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወርቅሰሙ ማሞ፣ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ የሃይማኖት አባቶች፣ የስፖርትና ኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ተማሪዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ታድመዋል፡፡

ስለ አብሮነት በሚያወሱ የኪነ-ጥበብና ዶክመንተሪ ሥራዎች፤ የፓናል ውይይቶች እያዋዙም ስለኢትዮጵያ በስፋት መክረዋል፡፡ ባሕሉን ለአንድነታችን እንዴት እንጠቀም ሲሉም እርስ በራሳቸው ተጠያይቀዋል፡፡ ስለሚሰፋበትም ሁኔታ መላ መትተዋል፡፡

“የብዝሀ ባሕል ተፈጥሯዊ ድንጋጌዎች” በሚል ርዕስ ጽሑፋቸው ይኩኑ አምላክ፣ ከህዋስ እስከ ሰው፤ ከሰው እስከ ማኅበረሰብ፤ ከማኅበረሰብ እስከ ኅብረተሰብ፤ ከኅብረተሰብ እስከ ሕዝብ፤ ከሕዝብ እስከ ሕዝቦች ያለውን ሁለንተናዊ መስተጋብር በሚገባ በመዳሰስ ባሕሉ የሚሰፋበትን አመላክተዋል፡፡ ይሄ ሁሉም አንድነት በልዩነት ውስጥ እየጎለበተ እንደሚመጣ አሳይተዋል። እልፍ አእላፍ ህዋሳቶቻችን በውስጣችን ሳይጋጩ መንሸራሸራቸው ማሳያ አድርገው ኢትዮጵያዊያኖች አብሮነታቸውን በዚህ መልክ ማስቀጠል ስለመቻላቸውም መክረዋል፡፡

ሌላኛው ጽሑፍ አቅራቢ እዝራ አባተም “ኪነ ጥበብ የወልና ብሔራዊ ትርክትን ለመገንባት ያለው ሚና ምንድነው” በሚል ርዕስ ኪነጥበብ ለአንድነት ያለውን አበርክቶ አንጸባርቀዋል፡፡ በወል ትርክቶቻችንና አንድ በሚያደርጉ ጉዳይ ላይ ለመሥራት ኪነ ጥበብ ትልቅ አቅም ያለው ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡ የዓለም ጥናቶችን ዋቢ አድርገውም የፈጠራ ኢንዱስትሪ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ብዙ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ያሉበት ዘርፍ ስለመሆኑና እዚህ ዘርፍ ላይ ያለውን አቅም በደንብ መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ሦስተኛው ጽሑፍ አቅራቢ ወገን ዋልታ (ዶ/ር)፣ በጽሑፋቸው ስለ ስፖርት ሰብከዋል፡፡ ስፖርት በአብዛኛው አንድነትና ትብብር ስለመሆኑም ጠቅሰዋል። ዓለምን አንድ ያደረገው ስፖርት ሀገራችንን አንድ የማድረግ አቅም እንዳለውም ተሞክሯቸውን አጋርተዋል፡፡

በተመሳሳይ ጽሑፍ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ዑስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ባለፈው ታሪክ መኩራት የሚቻለው ዛሬ ሌላ አዲስ ታሪክ በመሥራት እንደሆነ በጽሑፋቸው አስረድተዋል፡፡ መጥፎውን የሚሰብኩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ወቅሰዋል፤ በጎ በጎውን እንዲያጋሩም መክረዋል፡፡

ባሕል፤ ኪነጥበብ፤ ስፖርት፤ ለአብሮነት አስተዋጽኦ እንዳለውም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አብሮነትም እንዲሁም ለሐገር ግንባታ ይሄንኑ መጠቀም አስፈላጊ ስለመሆኑም መክረዋል፡፡ በጥቅሉም መድረኩ ባሕል፣ ጥበብና ስፖርት ለኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ፣ ለኢትዮጵያውያንም አብሮነት ያላቸው አበርክቶ ከፍ ያለ እንደመሆኑ፤ እነዚህን በልኩ መጠቀም እንደሚገባ የጋራ መግባባት የተፈጠረበት ነበር፡፡

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You