ያልታሰበው ክስተት!

በስፖርት ዓለም በተለያዩ የውድድር መድረኮች ያልተጠበቁ አስደንጋጭ፣ አስደሳችና አሳዛኝ ክስተቶች ይፈጠራሉ። እነዚህ ክስተቶች ከውድድሩ በኋላ ግን የማይረሱ ገጠመኞች ሆነው ቢያልፉም በታሪክ አጋጣሚ የሚታወሱ ይሆናሉ።

ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች በእግር ኳስም ይሁን በአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ መድረኮች አስገራሚና ያልተጠበቁ ክስተቶች ሲገጥሟቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች አይተናል። ከትናንት በስቲያ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ በተካሄደ የአስር ሺህ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ጥላሁን ኃይሌ የገጠመውም ወደፊት ከሚታወሱ ያልተጠበቁ የስፖርቱ ገጠመኞች አንዱ ነው።

የረጅም ርቀት ኮከብ አትሌት የሆነው ጥላሁን ኃይሌ የ2025 ዘ ቴን በተባለውና የብር ደረጃ ያለው የዓለም አትሌቲክስ አህጉር አቀፍ የቱር ውድድር በአስር ሺህ ሜትር ተወዳድሮ ለማሸነፍ በቂ ዝግጅት አድርጎ ነበር ወደ ካሊፎርኒያ ያቀናው።

ውድድሩ ሲጀመር የገጠመው ግን ያልተለመደና ብዙዎች ያልጠበቁት ክስተት ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው፡-

ዳኛው ውድድሩን ለማስጀመር 29 አትሌቶችን ሰበሰቡ። አትሌቶችም ውድድራቸውን ለመጀመር የተኩሱን ድምፅ በጉጉት እየተጠባበቁ ነበር። በድንገት ግን ለዳኛው ከውድድር አዘጋጁ መልእክት ደረሳቸው! መልእክቱም ” ሩጫውን የማስጀመሪያው ሰዓት ገና ስለሆነ አትሌቶችን በትኑ ” ተባሉ። ዳኛውም አትሌቶቹን በትነው 2 ደቂቃ ሰጡ። በዚህ መሃል የተወሰኑት አትሌቶች መፀዳጃ ቤት የቀሩት ደግሞ ሰውነታቸውን ሟሟቅ ቀጠሉ። መፀዳጃ ቤቱ የሚገኘው የ200ሜ መነሻ ላይ ሲሆን ለአትሌቶች እንዳይርቅ ተብሎ ዳር ላይ ተደርጎ የተሠራ ነው። ዳኛው ብዙም ሳይቆዩ ግን በድንገት “ልጀምር ነው ተሰብሰቡ ” ሲሉ ለአትሌቶቹ አሳወቁ። ይህንን ሲሉ ግን የተወሰኑ አትሌቶች መፀዳጃ ቤት ነበሩ።

ዳኛው ውድድሩን አስጀመሩ። ተመልካቹም “ኧረ የተረሱ ሁለት አትሌቶች አሉ” ብለው መጮኃቸውን ቀጠሉ። ውድድሩ ሲጀምር ፈረንሳዊው ሲሞን ቤዳር እና ኢትዮጵያዊው ጥላሁን ኃይሌ የ200 ሜትር መነሻ አካባቢ ካለው መፀዳጃ ቤት በመመለስ ላይ እንደነበሩ የታየ ሲሆን በዚህም ምክንያት በቅደም ተከተል ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች በ80 እና 100 ሜትር ያህል ርቀው ለመጀመር ተገደዋል። ውድድሩ ለሁለት ቡድን ተከፈለ፤ ቀድሞ የተነሳው እና ጥላሁን ፈረንሳዊው አትሌት ያሉበት ከኋላ መከተሉን ተያያዙት።

ጥላሁንና ጓደኛው እንደምንም ብለው ተጋግዘው ከብዙ ዙሮች በኋላ ዋናውን ቡድን ተቀላቀሉ ። ተመልካቹም የጥላሁንና የፈረንሳዊውን አትሌት መጨረሻ ለማየት በጉጉት ይጠብቅ ጀመረ። በመጨረሻም ፈረንሳዊው አትሌት ቀድመው የተነሱት አትሌቶች ላይ ለመድረስ ብዙ ጉልበት አውጥቶ ስለነበረ ውድድሩን አቋርጦ ወጣ። በዚህም ምክንያት ውድድሩን የማሸነፍ አቅም የነበረው ጥላሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠበት አስር ሺህ ሜትር 26:52 በመግባት አራተኛን ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ጥላሁን ከኋላ ተነስቶ ለማሸነፍ ያደረገው ጥረት አድናቆትን ያተረፈለት ሲሆን ያስመዘገበው ሰዓትም በመጪው ክረምት በቶክዮ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የዓለም አትሌቲክስ ያስቀመጠውን ሚኒማ ያሟላ ሆኗል።

በውድድሩ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ደረጃዎች በመያዝ ኬንያዊው ኢስማኤል ሮኪቶ ኪፕኩሩይ

(26:50.21) ሲያጠናቅቅ፣ ኤርትራዊው ሀብቶም ሳሙኤል (26:51.06) ሁለተኛና ደቡብ አፍሪካዊው አድሪያን ዋይልድሹት ( 26:51.27) ሦስተኛ ሆነው ፈፅመዋል።

ጥላሁን ኃይሌ ከውድድር በኋላ በሥፍራው ለነበሩ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው አስተያየት ‹‹በደንብ ተዘጋጅቼ ስለነበረ ውድድሩን እንደማሸነፍ ጠብቄ ነበር፣ ግን አልተሳካልኝም። ውድድሩን ልንጀምር ወደመስመር ከተጠጋን በኋላ የውድድር አስጀማሪው ዳኛ ለመጀመር ሁለት ደቂቃ ስለሚቀር ወደ ኋላ እንድንመለስ እና ጡንቻችንን እንድናፍታታ ነገረን:: በዚህ ጊዜ የተወሰንን አትሌቶች ወደመፀዳጃ ቤት አመራን:: የቆየሁት ለአንድ ደቂቃ ያህል ቢሆንም ስመለስ የደረስኩት ሌሎች ተወዳዳሪዎች ውድድሩን ሲጀምሩ ነበር:: አንዳንድ ጊዜ ውድድሮች የራሳቸው የሆነ ያልታሰበ ክስተቶች አሏቸው:: ሙሉ ኃይሌን ተጠቅሜ ውጤት ለማስመዝገብ ብጥርም የማሸነፍ እቅዴ አልተሳካም። ውድድሩ የ800 ሜትር ቢሆን ኖሮ ቀድመው የጀመሩት አትሌቶች ላይ የመድረሱም እድል አይኖረኝም ነበር። ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቤ ግን ደስ ብሎኛል›› ብሏል::

ባለፈው ጥር በስፔን ቫሌንሲያ በተደረገ የጎዳና ላይ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር የራሱ ምርጥ የሆነ 27፡13 ሰዓት ማስመዝገብ ችሎ የነበረው ጥላሁን በርቀቱ የመጀመሪያ የትራክ (መም) ውድድሩ ላይ ያስመዘገበው ውጤትም ሁሌም ማሰለፍ ከሚፈቀደው ኮታ በላይ የሆነ ቁጥር ያላቸው ብዙ አትሌቶች ሚኒማ በሚያሟሉባት ኢትዮጵያ 8ኛው የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ሚኒማ ያሟላ አትሌት ለመሆን አብቅቶታል።

በመጪው የቶኪዮ የዓለም ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመወዳደር ከመብቃት አንፃር ግቡ ምን እንደሆነ ለቀረበለት ጥያቄ ጥላሁን ሲመልስ ‹‹በሁለቱ ርቀቶች 10ሺህ እና 5ሺህ ሜትር ላይ አተኩሬ በመሥራት ቢያንስ በአንዱ ሀገሬን ለመወከል የመብቃት ግብ አለኝ:: በካሊፎርኒያው የ 10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ የተሳተፍኩትም የትራንስፖርት እና የሆቴል ወጪዬን በራሴ ችዬ ነው::›› ብሏል::

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You