አዲስ ዘመን ድሮ

እኚህ ሁለት ሰዎች እነማን ናቸው? 1957 ዓ.ም እና 1963ዓ.ም አንድ ዓይነት ድርጊት፣ ተመሳሳይ ታሪክ፤ አጋጣሚ ወይንስ አንዱ ሰው እንደ ሁለት… አንደኛው ለ29 ዓመታት ሌላኛውም ለ48 ዓመታት ጾታቸውን በመቀየር ማንም ሳይጠረጥር ቀሚስ ለብሰው በግርድና ሠርተዋል:: አስፋው ደግፌ ስሙንም ለውጦ አሰፋሽ ደግፌ ነኝ ሲል፣ ሁለተኛው ሰው ደግሞ ሸዋዬ ደገፉ ነው:: “ደገፉ” እና “ደግፌ” የሚለውን የአባታቸው ስምም የሚያስጠረጥር ግን ያልተደረሰበት ነገር ያለው ይመስላል:: በ1957 ዓ.ም እና በ1963ዓ.ም በተለያዩ ዓመታት ውስጥ በፖሊስ ከተያዙ በኋላ በሰጡት ቃል፤ ሁለቱም ቀሚስ መልበስ የጀመሩት ከልጅነታቸው ጀምሮ መሆኑን ያስረዳሉ:: ሁለቱም በግርድና ሲሠሩ የነበሩ ናቸው:: አስፋው ደግፌ ራሱ ሸዋዬ ደገፉ ይሆን? ሌላኛው አስገራሚ መረጃ ደግሞ “ላሟ መኪናውን ገጨች” ይለናል:: በጊቱም ፍየል ወልዳለች:: እንዲሁም ከጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎች መካከል ሁለቱን ለዛሬ እናስታውሳቸው::

ላሟ መኪናውን ገጨች

ህዳር 30 ቀን ባለፈው ማክሰኞ አንዲት ላም ሳንፎርድ ትምህርት ቤት አጠገብ በሚገኘው መንገድ ስታቋርጥ ቁጥሩ 1 ሺህ 355 የሆነ ማርቸዲስ መኪና ገጭታ አደጋ አድርሳበታለች:: በግጭቱ ላሟ አንዳችም አደጋ ሳይደርስባት መኪናውን ግን እንክትክቱን አውጥታዋለች::

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 2 ቀን 1952 ዓ.ም)

ወንዱ 29 ዓመት ሴት ነኝ ብሎ ኖረ

መጋቢት 1 ቀን 1957 ዓ.ም አቶ አስፋው ደግፌ የተባለ የ36 ዓመት ሰው ስሙን ለውጦ፣ ቀሚስ በመልበስ ግርድና እየተቀጠረ፣ እንጀራ በመጋገርና ወጥ በመሥራት በጠቅላላው ሴት መስሎ ሃያ ዘጠኝ ዓመት ከኖረ በኋላ በዚህ ወር ውስጥ በፖሊስ ምርመራ ጾታው ተገልጦበታል::

አቶ አስፋው ወይዘሮ አሰፋሽ ደግፌ በሚል የሴት ስም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ሲኖር ጾታውን ያወቀ አንድ ሰው እንዳልነበረ ተገልጧል:: ከብዙ ሰዎች ቤት በግርድና ከመቀጠሩም ሌላ በደብረ ዘይት ከተማ በአቶ ገብሩ ጻድቅ የእህል በረንዳ ቤት ተከራይቶ ጠላ ይሸጥ እንደነበር ታውቋል::

ምስጢሩ የተገለጠው እህል ሰርቀሃል በመባል ጥር 3 ቀን 1957ዓ.ም ተይዞ በፖሊስ ሲመረመር መሆኑ ተመልክቷል:: ቀሚስ መልበስ የጀመረው በ1928ዓ.ም ነው:: ምክንያቱን ሲያስረዳ “ከተወለድኩ ጀምሮ ስለሚያመኝ ቀሚስ በመልበስ ሴት ለመምሰል የሞከርኩት በዚህ ብቻ ነው” ሲል አቶ አስፋው አስረድቷል:: ለግርድና ተቀጥሮ ሲያገለግል ከተቀበላቸው የምስክር ወረቀቶች መካከል በወንድ ስም ይጠራዋል:: አቶ አስፋው ካሁን ቀደም እንደዚሁ እህልና ዱቄት መስረቁ ተመስክሮበት ክሱ ለፍርድ ቀርቧል::

(አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 1957ዓ.ም)

48 ዓመታት ቀሚስ የለበሰው ወንድ ተከሰሰ

48 ዓመት ሙሉ እንደ ሴት ቀሚስ በመልበስ ሸዋዬ ደገፉ በመባል በሴት ስም ይጠራ የነበረ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ::

ሸዋዬ ደገፉ የወንድ ጾታውን በመደበቅ ቀሚስ ለብሶ በሴት ስም በመጠራት ካሳለፈው 48 ዓመታት ውስጥ በናዝሬት 10 ዓመት፣ በአሰላ ከተማ አራት ዓመት፣ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ 11 ዓመት በታላላቅ ሰዎች ቤት በሴት ሥራ ሙያ እየተቀጠረ መኖሩን ገልጿል::

ሸዋዬ የወንድነት ጾታው እንዳይታወቅበት በአገጩ ግራና ቀኝ በመጠኑ የሚበቅለውን ጢም በየዕለቱ ይላጫል:: ጠጉረ በራ በመሆኑም ዘወትር እንደ ሴት ሻሽ ይጠመጥማል:: የጆሮ ጉትቻም እንደማይለየው ታውቋል::

ሸዋዬ በትውልድ ሀገሩ በየረርና ከርዩ አውራጃ በኢጀሬ ከህጻንነቱ ጊዜ ጀምሮ የሴት ቀሚስ ይለብስ እንደነበር ጠቅሶ ወደ ፊትም እስከ ዕለቱ ሞቱ ድረስ ቀሚስ መልበሱን እንደማይተው አስረድቷል::

ተከሳሹ የሴቶቹን ሙያ አጠናቆ የሚያውቅ መሆኑን ገልጾ ከህጻንነቱ ጀምሮ ዘፈን የሚወድ፤ በዚህም ሙያ ብዙ ጊዜ እንደተጠቀመበት አረጋግጧል::

ሸዋዬ ደገፉ በናዝሬት፣ በአሰላና በአዲስ አበባ እየተዘዋወረ ለ25 ዓመታት ተቀጥሮ በሚያገለግልበት ጊዜ የወንድነት ጾታው ያልታወቀበት መሆኑን አስረድቷል::

ሸዋዬ ዘመዶቹን ለመጠየቅ ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ኤጀሬ ሲጓዝ ለጥቂት ጊዜ በናዝሬት ከተማ በሴት ሥራ ሙያ ተቀጥሮ ገንዘብ ለማግኘት ባለው ዕቅድ መሠረት በከተማው ውስጥ ሲዘዋወር ፖሊሶች በጥርጣሬ ያዙት:: ከዚያም ሲጠየቅ ወንድ መሆኑንና በዚሁ በሴት ሁኔታ 48 ዓመታት ሙሉ መኖሩን አስረድቷል::

በዚህም ጾታ የመለወጥና ቀሚስ የመልበስ አድራጎቱ ተከሶ አዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቧል:: ሆኖም በዚሁ ሁኔታ ለመኖር የፈለገበት ምክንያት በሚገባ እስኪጣራ ድረስ በዋስ መለቀቁ ታውቋል::

(አዲስ ዘመን የካቲት 6 ቀን 1963 ዓ.ም)

በግ ፍየል ወለደች

ሊበን ቀበሌ ደንጉማ ማርያም ከሚባል ቦታ አንዲት በግ የፍየል ግልገል ወለደች:: የተወለደውም ግልገል ጅናው ከፍየል ጅና ይሰፋል::

የጎጃም አዣንስ፤ አለቃ መብራቴ እንግዳ

(አዲስ ዘመን ግንቦት 17 ቀን 1937ዓ.ም)

አንድ ጥያቄ አለኝ

-ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ

*እኔና ሚስቴ እየተጣላን ተቸግረናል:: ገላዬ በሙሉ በጠጉር የተሸፈነ ነው:: ይህ ደግሞ ሚስቴን አያስደስታትም:: ሁል ጊዜ ታጉረመርማለች:: ባለቤቴን ለማስደሰት የገላዬን ጠጉር ምን ላድርገው?

-እንደ ጢምህ በየጊዜው እንዳትላጨው የባሰ እንደ እሾህ ልትዋጋ ነው:: እንዲህ አድርግ፤ አንገቱ ድረስ የሚቆለፍ ፒጃማ እየለበስክ ተኛ::

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 1964ዓ.ም)

*ሁለት እግሮቹ በእርዝማኔ እኩል ያልሆነ ሰው ካለ እባክህ ንገረኝ?

-ሞልቶ፤ ሜዳው ሙሉ ብቅ ጥልቅ የሚል ብቻ አይደለም እንዴ? ስንቱን ልንገርህ?

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You