
በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ አንዲት ሴት ልትወልድ ስትቃረብ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ይደረጋሉ። ከወለደች በኋላም የአራስነት ቆይታዋን ጨርሳ እስክትወጣ የሚደረጉ የተለያዩ ባሕላዊ ሥርዓቶች አሉ። ከመውለዷ በፊትም ሆነ ከወለደች በኋላ የሚደረጉ ሥርዓቶች በብሔረሰቡ ባሕላዊ የአኗኗር ዘይቤ የተቃኙ እጅግ ውብና ድንቅ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡
ሆኖም እነዚህ ለአራሷም ሆነ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የሆኑ እሴቶች እና የጎላ ባሕላዊ ይዘት ያላቸው ዝግጅቶች አብዛኞቹ እየተረሱ መጥተዋል። አንዳንዶቹም በፈረንጅ ባሕል ተወረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ ሳምራዊት ግርማ ይሄ የኦሮሞ ብሔረሰብን ባሕል እየሸረሸረ የመጣው ሁኔታ በብርቱ ሲያሳስባት ቆይቷል፤ ውልደቷና እድገቷ ከወደ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ መነሻ የሆነች ጋዜጠኛን ልብም አነሳስቷል። ሦስት ልጆች በመውለድ ከእናቷ ልምድ ቀስማ በባሕሉ መሠረት የታረሰችበትና ያለፈችበት መሆኑም ደግሞ ባሕሉን ለማጣጣም አስችሏታል፤ ይሄ ባሕል መረሳትም ሆነ መበረዝ የለበትም የሚለው ሃሳብ ታዲያ ባሕሉ ሳይበረዝ በትክክል ሊቀመጥ ይገባዋልና ብዕሯን ልታነሳ ወደደች።
የመጽሐፉ ርዕስ «ዑልማ» ይባላል። 80 ገጾች ያሉት ሲሆን በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የተፃፈ ነው። በቅርቡ በኦሮሞ ባሕል ማዕከል ተመርቋል። «ዑልማ » በአማርኛ ሲተረጎም «አራስነት» ማለት ነው የምትለው ጋዜጠኛዋ ሳምራዊት መጽሐፉን ለመፃፍ ያነሳሳትም ማኅበረሰቡ ወደ ነባር ባሕሎች እንዲመለስ ማስቻል ስለመሆኑም ትናገራለች።
ጠቃሚ ባሕላዊ እሴቶቹን አስመልክታ ስታብራራ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ አንዲት ሴት ልትወልድ ስትቃረብ፤ በተለይም ስምንት ወር ሲሆናት ፤ ዘጠኝ ወሯ ሲገባም ለእርሷ የሚሆኑ ባሕላዊ ምግብ እና መጠጦች ይዘጋጃሉ። ከገብስ እና የተለያየ ጠቃሚ የንጥረ ነገር ይዘት ካላቸው የእህል ዘሮች የሚዘጋጀው ገንፎ ዋናው ነው። ገንፎ እና ሻሜታ ከተለያዩ የእህል አይነቶች ቀድሞ ይዘጋጃል። ገንፎ ወላድ ሴትን ያጠነክራል፤ ጉልበትም ይሆናታል ተብሎ በመታሰብ የሚዘጋጅ ነው። እንዲሁም ጡቷ ወተት እንዲያግት በሚልም የአጥሚት እህል በበቂ ሁኔታ ይዘጋጃል። አጥሚቱም የተለያየ ንጥረ ነገር ከያዙ የተለያዩ የእህል ዘሮች ነው የሚዘጋጀው። ሁለቱም በጽንስ ላለውና ለሚወለደውም ልጇ ይጠቅማሉ ተብለውም ነው የሚዘጋጁት። ዝግጅቱ ከወሊድ በፊት እና በኋላ ያለውን ሂደት የሚሸፍን ነው። በተለይ ነፍሰ ጡሯ የኢኮኖሚ አቅሟ የተሻለ ከሆነ ከወሊድ በፊት እና በኋላ ለሚከናወነው ሥነሥርዓት «ቡነቀላ» በቅቤ የታሸ ያልተፈለፈለ ቡና ይዘጋጃል። ጠጅ ይጣላል፤ ጠላም ይጠመቃል። ኢኮኖሚዋ ዝቅተኛ ከሆነ እና ባሕላዊ ምግቡን ማዘጋጀት ባትችል እና ቤተሰቦቿ አጠገቧ ባይኖሩም እንኳን በብሔረሰቡ ባሕል ዘንድ ባሕላዊው ሥርዓቱ ሳይደረግላት አትወልድም፤ ከአራስ ቤት አትወጣም፡፡
ይሄ ባሕል የማኅበረሰቡን የአብሮነት መስተጋብር የሚያጠናክር ከመሆኑ የተነሳ የገንፎና የአጥሚት እህሉን ጨምሮ ከመውለዷ በፊትና በኋላ ያለውን ሥነሥርዓት በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት በአቅራቢያዋ በሚገኙ ሰዎችና በጎረቤቶቿ ይደረግላታል። ይሄ ዝግጅት ምንም ልጅ ላልወለደች ሴትም ልጅ ወልዶ እስከመስጠት የሚደርስ መሆኑን ጋዜጠኛ ሳምራዊት ታወሳለች። እንደ እሷ ገለፃ ባሕሉ ማኅበረሰባዊ አብሮነቱን፤ መተሳሰቡን እና ፍቅሩን አብዝቶ ከማጠናከሩ የተነሳ ብዙ ልጅ ያላት ሴት ለሌላት ወልዳ የምትሰጥበት ሂደት አለ። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ልጅ ተወልዶ የተሰጣት ሴት ባትወልድም የግድ ሁሉንም ወግ ማዕረግ ማየት አለባት ተብሎ ይታሰባል። የገንፎና የአጥሚት እህልን ጨምሮ የተለያዩ ምግብ እና መጠጦች ዝግጅት ሥነሥርዓትም ይደረግላታል። ልጅቱ ወይም ልጁ ተወልዶ ከመሰጠቱ በፊትም የገንፎ እና ሻሜታ ቀመሳም ሆነ በዚሁ ወቅት የሚካሄደው ምርቃትም ይከናወናል። ምርቃቱ የተሰጣት ልጅ እንዲያድግላትና በፈጣሪ እንዲባረክላት፤ ከማድረግ ባሻገር ጧሪ ቀባሪ፤ ጋሻ መከታ እንዲሆንላትም ምኞት መግለጫም ጭምር ነው።
በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ይሄ ለወለደችውም ሆነ ላልወለደችውና ልጅ ተወልዶ ለተሰጣት ሴት የሚደረገው ዝግጅት ብዙ ጊዜ የሚከናወነው በወላዷ ሴት የቅርብ ዘመዶች ነው። በሚዜዎቿና ጎረቤቶቿም ጭምር ይከናወናል። ‹‹በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ሴት ልጅ የመጀመሪያ ልጇን እናቷ ጋር እንድትወልድ ይመከራል» ትላለች ጋዜጠኛዋ። ይሄም ባሕል ከእናቷ ልጅ አስተቃቀፍ እና አያያዝ፤ በወሊድ የተጎዳ ሰውነቷን በምግብ እና መጠጥ እንድትንከባከብ የሚያስችላት በአጠቃላይም ልጇን እንዴት መንከባከብ እንዳለባት ልምድ የምትቀስምበት ነው። ባሕሉ እናቷ በልጅ አያያዝ ጉዳይ በደንብ አድርጋ እንድታሠለጥናት በአራስ ቤትም በቂ እንክብካቤ ስለምታደርግላት ወገቧ እንዲጠነክር ያስችላል ተብሎ ይታሰባል።
በጋዜጠኛዋ የተፃፈው ‹ዑልማ› መጽሐፍ በተለይ ከተሞች አካባቢ እየታየ ያለውን በባሕል ወረራ «ቤቢ ሻወር» በሚል መተካት፤ እንዲሁም ነባር ሀገራዊ ባሕሎች እየተረሱ በመሆኑ አሁን ላይ ባሕሎቻችንን የሚመልሱና የሚያስታውሱ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፤ በመሆኑም «ዴሱ ኤቢሱ» ወይም ወላድን መመረቅ የሚለው በመጽሐፉ በስፋት ተገልጿል።
ለአራሷ ታስቦ የተዘጋጀው የገንፎ እህል እና ከገንፎ ጋር አብሮ የሚቀርበው መጠጥ ሻሜታ የሚመረቀው (የሚቀመሰው) በዚሁ ወቅት ነው። ሻሜታ በኦሮሞ ባሕል ዘንድ ብዙ ጊዜ ለወላድ ሴት የሚዘጋጀው ከገንፎ ጋር አብሮ የሚቀርብ ነው።
በብሔረሰቡ ባሕል ዘንድ ለመውለድ የደረሰችው ነፍሰ ጡር ሴት ከመውለዷ በፊት ገንፎውንና ሻሜታው ለቅምሻ ይቀርባል። ቡናው ይፈላል፤ ሚዜዎቿ፤ የቅርብ ዘመዶቿ ጎረቤት ገንፎውን እና ሻሜታውን ለመቅመስ ከሚጠሩት የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ናቸው።
ከዚሁ ቅምሻ ጋር ተያይዞም የቅምሻ ታዳሚዎቹ በሙሉ ነፍሰ ጡሯን ሴት በመመረቅ የሚያከናውኑት ሥነሥርዓትም አለ። በዚህ ሥነሥርዓት የመውለጃ ወሯ ለተቃረበው ወይም ለገባው ነፍሰ ጡር ሴት «ዴሱ ኤቢሱ» በተሰኘው ምርቃት ይሄውም የተበላው ገንፎ ገበታ ከፊታቸው ላይ ሳይነሳ ገበታውን በእጃቸው ይዘው «ምጥሽን ያቅልለው፤ በሆድሽ የተሸከምሽውን ማርያም በእጅሽ ታድርግልሽ፤ የምትወልጅው ይባረክ» ብለው ይመርቃሉ፤ ምርቃቱ ለመውለድ የተቃረበችው ሴት እንዳትፈራ፣ አወላለዷን እያሰበች እንዳትሸበር፤ እንዳትጨነቅ ይረዳታል። ነፍሰ ጡሯ እርግዝና የመጀመሪያ ከሆነ የቅምሻው ታዳሚዎች ያላቸውን ልምድም ያካፍላታል፡፡
ጋዜጠኛ ሳምራዊት በዋናነት ዑልማን ለመጻፍ ያነሳሳት ባሕሉ ለነፍሰ ጡር ሴት ተስፋ የሚሰጥና በብርቱም የሚያጠነክር እሴት አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ቤቢ ሻወር ወደሚለው ፈረንጅኛ እየተቀየረ መምጣቱ አሳስቧት መሆኑን ደጋግማ ትናገራለች።
አሁን አሁን« ቤቢ ሻወር» ተብሎ የሚደረገው ዝግጅት እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ እንዲሁም ባሕልንም የሚያጠፋ ነው። ስለዚህ ወደ የባሕሎቻችን እንመለስ። በየትኛውም ብሔረሰብ ዘንድ ተመራጩና በሰላምና ፍቅር የሚያኖረን ባሕላችን ነው። ምርቃትና ምስጋና ነው። ሀገራዊ ባሕልን በባሕር ማዶው መጤ ባሕል መተካቱ ከጉዳቱ ይልቅ ጠቀሜታ የለውም።
ጋዜጠኛ ሳምራዊትም ይሄንኑ የተበረዘ ባሕል ከመታዘብ በመነሳት ለሥራ ወደ ተለያዩ ዞኖች በተንቀሳቀሰችበት አጋጣሚ ሁሉም ትክክለኛውን እሴቶች እና ነባር ባሕሎች ከምንጫቸው ስትሰበስብ ዓመታት አሳልፋለች። ሙሉ በሙሉ በቤቢ ሻወር የተተካውን ልማድ ወደ ባሕል ለመመለስ ይህን የራሷን ጥረት ለማድረግ መነሳቷን ትናገራለች።
በኦሮሚኛ «ዑልማ» በአማርኛ አራስነት የተባለውን መጽሐፍ መጻፏ ለዚህ ማሳያ ነው። ይሄን መጽሐፍ ለመጻፍ ሌላው ያነሳሳት የተበረዘውን ባሕል ወደ ነበረበት ለመመለስ ማሰብ ብቻ አይደለም። በተጨማሪም በርካታ ጠቃሚ እሴቶች ያሏቸው ሌሎችም ከወሊድ ጋር የተያያዙ እና በወሊድ ጋር የሚተሳሰሩ ባሕላዊ ሥርዓቶች ለማሳወቅ ጭምር ነው። ይህም አንዱ ከወሊድ በኋላ የሚከናወነው «ሸነን» የሚባለው ነው። በዚህ ሥነሥርዓት ሴት ከወለደች ጊዜ ጀምሮ እስከ አምስት ቀን እንኳን ማርያም ማረችሽ እያለ የሚጠይቃት ሰው ቢኖርም በአምስተኛው ቀን ገንፎ ብሉ ተብሎ የአካባቢው ሰው ይጠራል። ሴቶች ተሰባስበው ገንፎ ይገነፋና ይበላል። በዚህ ቀን የወለደችው ሴት ጥሩ መዓዛ ያለው ቅጠላ ቅጠል ከጫካ ተፈልጎና ተመርጦ ይመጣና ተቀቅሎ ሰውነቷን ትታጠባለች፤ ከቅጠሉም ትታጠናለችም። ቅጠላ ቅጠሉን የሚያመጡት በዕድሜ የገፉ ሴቶች ናቸው። በዚህም ወገቧ እንዲጠነክር፤ ድካሟን እንድትረሳ፤ ነፋስ እንዳያገኛት ያደርጓታል ተብሎ ይታሰባል፡፡
አሁን ላይ እናቶች ለአራሷ በዚህ መልኩ አስተካክለውላት የሚሄዱበት ባሕልም እየተዘነጋ መምጣቱን ሳምራዊት ትናገራለች። የተወለደውን ሕጻን በዘጠነኛው ቀን ፀሐይ መሞቅ አለበት። አራሷ ወደ ፀሐይ የምትወጣውም ራሱን በቻለ ዝግጅት ነው። በቤተሰብ ታጅባ ቡና ተፈልቶ እየተበላ እየተጠጣ ነው። ለሕፃኑ ስም የሚወጣለትም በዚሁ ጊዜ ነው።
ወላዷ ሴት አራስነቷን ጨርሳ የምትወጣበት እና «ዑልማ በሁ» የሚባልም ሥነሥርዓት አለ። ይሄ ሥነሥርዓት በአብዛኛው ከወለደች 40 ቀን ሲሆናት የሚከናወን ነው። ከዚህ ሥነ ሥርዓት በኋላ ወንዝ መሻገር፤ ገበያ እና የፈለገችበት መሄድ ትችላለች። ሠራተኛም ከሆነች ወደ ሥራዋ መግባት ትችላለች። ለመታረስ ወደ እናቷ ጋር የሄደችውም ከዛ በኋላ መመለስ ትችላለች። ወደ እናቷ ቤት ስትሄድም ሆነ ወደ ባሏ ቤት ስትመለስ ክብር ባለው ዝግጅትና ሥነ ሥርዓት ነው። ይሄም «ቡነ ቀላ » ተዘጋጅቶ፤ ዳቦ ተጋግሮ ቡና ተፈልቶ ተመርቃ ከአራስ ቤት ወደ ውጪ የምትወጣበት ሥርዓት ነው፡፡
ጋዜጠኛ ሳምራዊት እንደምትለው፤ እነዚህ ክንዋኔዎች በሕይወታችን የምናደርጋቸው ባሕሎች ናቸው። እነዚህን የአብሮነት እሴቶች እያዳበርን ብናስቀጥል ወደማንነታችን መመለስ እንችላለን። ርስ በርስ የሚያጋጨንም አይኖርም። የምንመኛትን ኢትዮጵያ በጋራ ለማቆምም ጽኑ መሠረት ይሆኑናል የሚል ዕምነትም አላት ደራሲዋ።
በነዚህ ባሕላዊ እሴቶች ዙሪያ ሴቶች ሲሰባሰቡ ስለ ሀገር፤ ስለ ልጆች አስተዳደግ፤ ብዙ ነገር ይጋራሉ፤ ይደጋገፋሉ። መብላት መጠጣት ብቻ ሳይሆን ባሕላቸውን ያሳድጉበታልና ወደዚህ ባሕል መመለስ ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ትመክራለች፡፡
ባሕሉን ለመመለስ ልክ እሷ እንደፃፈችው መጽሐፍ ሁሉ ተጠንቶ የተሠራና አሻራውን የሚያስታውስ ሊኖር ስለመገባቱም ትገልጻለች።
ስለ ባሕሉ የሚያውቁትን ከዞን አንስቶ እስከ ወረዳ ያሉ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች አግዘዋታል። ኦሮሚያ ሰፊ ክልል ከመሆኑ አንፃር በዚህ መጽሐፍ ማካተት አይቻልም። የሚለያዩበት ባሕላዊ ምግብ ሊኖር እና አንዱ ጋር የሚታወቀው ሌላው ጋር ላይታወቅ ይችላል። በመሆኑም እሷ ተወልዳ ካደገችበት ምሥራቅ ወለጋ ነቀምቴ በመነሳት ነው መጽሐፉን የፃፈችው። ምሥራቅ ወለጋ፤ ምዕራብ ወለጋ፤ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፤ ቄለም ወለጋ እንዲሁም ጅማ፣ ኢሉ አባቦራ እና ቡኖ በደሌ የሚባሉ ሰባት ዞኖች ተካትተዋል። ምክንያቱን ስትገልጽ የነዚህ ባሕል ይመሳሰላል ትላለች። መሠረታቸው (ኦሪጅናቸው) የመጫ ኦሮሞ ነው የሚባሉት። እነዚህን በአንድ ላይ ማካተቷ ለመጻፍ ያመቻት መሆኑን ታነሻለች። ደራሲዋ ሌሎች ተቀራራቢ ባሕል ያላቸውን የኦሮሚያ ክልል ዞን ባሕሎችን አካታ .ዑልማ. ወይም አራስነት የተሰኘውን ቁጥር ሁለት መጽሐፍ የመጻፍ እቅድንም ልቧ ሰንቋል።
መጽሐፉ ወደ ቀድሞ ማንነታችን መመለሱና የማኅበራዊ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ ባሕላዊ እሴቶች በመያዙ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ መሆን አለበት። በዚህ በኩል የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮዎችን ጨምሮ ማንነቴን ያሉ አመራርና የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ግድ ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም