
– ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ታርሷል
አዲስ አበባ፡- በዘንድሮ የበልግ ምርት ዘመን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 99 ሚሊዮን ኩንታን ምርት ለማግኘት መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። እስከ አሁን ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ መታረሱን ተመልክቷል
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በ2017 የምርት ዘመን በልግ አብቃይ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስከአሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሷል። ከዚህ ውስጥም 222 ሺህ መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል። በቀሪ ጊዜያት እቅዱን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ነው።
በአማራ፣ ኦሮሚያ ፣ ትግራይ ፣ ሲዳማ ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሱማሌ ክልሎች 3 ሚሊዮን 780 ሺህ 343 ሄክታር መሬት በማልማት 99 ሚሊዮን 235 ሺ 463 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል። ይህንን መሠረት በማድረግ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በተሠራው ሥራ እስካሁን 2 ሚሊዮን 441 ሺህ ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን 222 ሺ 334 ሄክታር የሚሆነው መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥም 19 ሺህ 727 ሄክታር መሬት በክላስተር የተሸፈነ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ኢሳያስ ማብራሪያ፤ በምርት ወቅት ለማምረት የታቀደውን ለማሳካትም በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ አስፈላጊ የሆኑ እንደማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦቶችን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ተደርጓል። የአየር ትንበያን መሠረት በማድረግም አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ አስቀድሞ መሬቱን እንዲያዘጋጅ ለማድረግም የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል።
በዘንድሮ የበልግ ወቅት በአጠቃላይ የምስራቅ አማራ፣ ደቡባዊ ትግራይ፣ ኦሮሚያ ታችኛው አካባቢ፣ አብዛኛው የደቡብ የሀገሪቱ ክፍል፤ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ የበልግ ዝናብን በመጠቀም በብዛት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮ የበልግ ዝናብ ምንም እንኳን በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም በአብዛኛው በልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ መደበኛ ዝናብ እያገኙ መሆናቸውን አመልክተው፤ ሚኒስቴሩ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት በየሳምንቱ መረጃ በመለዋወጥ አርሶ አደሩ አስቀድሞ የማሳ ዝግጅት እንዲያደርግ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የበልግ ዝናብ ዘግይቶ ከሚዘንብባቸው የሱማሌ ክልል ዞኖች በስተቀር በአሁኑ ወቅት በሁሉም አካባቢዎች ላይ መደበኛ መጠን ያለው ዝናብ እየዘነበ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ዕቅዱን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መሆኑን ገልጸዋል። በሱማሌ ክልልም ትንበያውን መሠረት በማድረግ አስቀድሞ የማሳ ዝግጅት መደረጉን አቶ ኢሳያስ ተናግረው፤ የዘርና ማዳበሪያ አቅርቦቱም ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆኑንና የዝናብ ጊዜውን ጠብቆ መሬት በዘር የመሸፈን ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል 239 ሺህ ሄክታር ለማረስ መታቀዱን አስታውሰው፤ እስከአሁን 224 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን፤ የቀረው 15 ሺህ ሄክታር መሬት በቀጣይ ቀናት ልማት ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ካለፈው የምርት ወቅት ጋር ሲነፃፀር በማሳ ዝግጅት፤ በማዳበሪያና በዘር አቅርቦት ረገድ የተሻለ ሥራ መሠራቱን መሪ ሥራ አስፈሚው ጠቁመው፤ ‹‹በተለይም የበልግ አብቃይና ያደረ ማዳበሪያ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የዘር ወቅታቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማዳበሪያና ዘር እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው›› ብለዋል።
በየሶስት ቀኑ በግብዓት ዘርፍ እየተገመገሙ ያሉ ክፍቶችን የማስተካከል ሥራዎች እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም ከዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም እንደ እጥረት ይነሳ የነበረው የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረት በዘንድሮ የበልግ ሥራ መፈታት መቻሉን አስረድተዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም