ሳይንስና ቴክኖሎጂ የጭነት አገልግሎትን የሚያሳልጠው መተግበሪያ

ወንድማማቾቹ ወጣት ሙሉዓለም ምህረቱ እና ምስጋናው ምህረቱ ተወልደው ያደጉት በገጠር አካባቢ ነው። በዚያው አካባቢም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ አርሶ አደር እናታቸውን በግብርና ሥራ እያገዙ አድገዋል። በትምህርታቸው ልቀው በመሄድም ሙለዓለም ሁለተኛ ዲግሪውን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለመያዝ የበቃ ሲሆን፣ ምስጋናው ደግሞ በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል።

በአንድ ወቅት እናታቸው በሴት ጉልበታቸው ያመረቱት ድንች ወደ ገበያ ለማቅረብ የማጓጓዣ አገልግሎት ባለማግኘታቸው ምርቱ ሲበላሽ ይመለከታሉ። ተመልክተው ብቻ ዝም አላሉም፤ ይልቁንም ሙያቸውን ተጠቅመው ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ውስጥ ገቡ። ጥረታቸው ፍሬያማ ሆኖም የመፍትሔ ሃሳብ ያመነጫሉ።

ወጣቶቹ ለችግራቸው መፍትሔ ለማምጣት በሚያደርጉት ጥረት ሃሳቡ በይበልጥ ዳብሮ ውጤታማ ይሆን ዘንድ ከጓደኛቸው ወጣት ውብዓለም አፈራ ጋር እየተጋገዙ የሎጀስቲክ ችግርን የሚፈታ ‹‹ኢትዮ ጭነት ኦነርና ኢትዮ ጭነት ድራይቨር›› የተሰኘ መተግበሪያ መሥራት ችለዋል።

መተግበሪያውን የመሥራት ሃሳቡን እንደጀመሩ የሥራና ክህሎት እንዲሁም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴሮች ባዘጋጇቸው ኢንኩቤሽኖች ላይ ተሳታፊ ሆነው ሥልጠናዎች ወስደዋል። ሎጂቴክ በተሰኘው ፕሮግራም ላይም የሥራ እድል ፈጠራ /የኢንተርፕርነርሽፕ/ ሥልጠናዎች ማግኘት በመቻላቸውም የፈጠራ ሥራቸውን አዳብረው አሁን ለበቃበት ደረጃ አድርሰዋል።

ሦስቱ ወጣቶች መተግበሪያውን ከሠሩ በኋላ የኢትዮ ጭነት ሎጀስቲክ ቴክኖሎጂ የተሰኘ ድርጅት መሥርተው ብዙ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። የድርጅቱ የሶፍት ዌር ባለሙያና ሥራ አስፈጻሚ ወጣት ሙሉዓለም ምህረቱ እንደተናገረው፤ የመተግበሪያውን ፈጠራ ሃሳብ ያፈለቁት ከመመረቃቸው በፊት ቢሆንም፣ ይበልጥ አዳብረው እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ያደረጉት ግን ከተመረቁ በኋላ ነው። መተግበሪያውን መሥራት የጀመሩት ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን ፕላትፎርሙን ለመሥራት ደግሞ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ፈጅቷል።

እሱ እንዳብራራው፤ በጭነት አገልግሎት ዙሪያ ለመሥራት ሲያስቡ ጥናታዊ ጽሑፎችን አንብበዋል፤ የዳሰሳ ጥናትም አድርገዋል። በዚህ ሁሉም ችግሩ ምን ያህል ጥልቅ ነው? እንዴትስ ሊፈታ ይችላል የሚለው በደንብ ታይቷል።

እሱ እንደሚለው፤ በተለይ ሀገር አቋራጭ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ መኪናዎች የጭነት ትዕዛዝ ሳይኖራቸው ጭነት ፈልጋ ከአንድ ወደ አንድ ቦታ በመንቀሳቀስ የሚያባክኑት ነዳጅና ጊዜ መኖሩንም በሚገባ ተገንዝበዋል። መተግበሪያውን ወደ ሥራ በማስገባቱ በኩልም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የሎጀስቲክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ከሆነ መኪናው በቀላሉ ትዕዛዝ በመቀበል መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጥራል። በመዳረሻ ቦታ በኩልም እንዲሁ የጭነት ትዕዛዝ ይዘው የሚመላለሱበት አሠራር እንዲኖር ተደርጓል።

በሀገሪቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህንንም ዘርፍ ወደ ዲጂታል ለመምጣት በማሰብ የተሠራ መተግበሪያ ስለመሆኑም ይገልጻል። ‹‹መተግበሪያውን መሥራታችን ሀገሪቱ በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የያዘችውን እቅድ በማሳካቱ ረገድ እንደ ባለሙያ የራሳችንን ዐሻራ ለማኖር ያስችለናል›› ሲልም አስታውቋል ።

እሱ እንዳለው፤ መተግበሪያው ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅምት 2016 ነው ይፋ የተደረገው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስካሁን የገበያውን አዋጭነትና ማሻሻያዎች በማድረግ ፈንዶችን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉና ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል።

መተግበሪያው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። ዋንኛው ፈላጊና ተፈላጊን ያለምንም ውጣ ውረድ በቴክኖሎጂ እንዲተሳሰሩ ማስቻል ነው። ጭነት ማስጫን የሚፈልጉ ሰዎችና የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችን በቀላሉ በማገናኘት አገልግሎት አሰጣጡን ያሳልጣል።

በፍጥነት እንዲጓጓዙ የሚፈለጉ ምርቶችም በፍጥነት ቦታው ደርሰው የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለማድረግ ያረዳል። በተጨማሪም በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀጥተኛ ያልሆነ ተዘዋዋሪ የሥራ እድልን ይፈጥራል።

የሞባይል መተግበሪያውን ከአፕ ስቶርና በፕሌይ ስቶር በማውረድ መጠቀም ይቻላል። የጭነት ባለቤቶች ጭነት ሲኖራቸው ‹‹ኢትዮ ጭነት ኦነር›› የተሰኘውን መተግበሪያ በማውረድ በቀላሉ በመመዝገብ ማሳወቅ ይችላሉ። የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ወይም ባለቤቶች ከሆኑ ደግሞ ‹‹ኢትዮ ጭነት ድራይቨር›› የተሰኘውን መተግበሪያ በማውረድና ሌብሬያቸውን በማስመዝገብ ወይም በአካል ቢሮ ድረስ በመምጣት መመዝገብ የሚችሉበት አሠራር ተቀምጧል። ከተመዘገቡ በኋላም ስለትክክለኛነቱ ተገቢው ማጥራት ከተደረገና ከተረጋገጠ በኋላ መኪናው አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል። ሀሰተኛ የሆኑ ሌብሬዎች እንዳይመዘገቡ ድርጅቱ ማጣራት ላይ እንደሚሠራ ያስረዳል።

መተግበሪያው የጭነት አገልግሎት ፈላጊዎችንና አገልግሎት ሰጪዎችን ለማገናኘት የሚሠራ እንደመሆኑ አሽከርካሪዎች ያሉበትን ቦታ የሚያሳውቁበት ፕላትፎርም አለው ይላል። ይህ በመሆኑም መተግበሪያው አሽከርካሪዎች የት ቦታ ላይ እንደሚገኙ በቀላሉ ለማወቅ እንደሚያስችል ይገልጻል። የጭነት አገልግሎቱን የሚፈልጉ የጭነት ባለቤቶችም የሚፈልጉትን አገልግሎት፣ ትዕዛዝ ሲሰጡ በመተግበሪያው አማካኝነት እንዲገናኙ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።

‹‹የአገልግሎቱን ሂደት ሙሉ ለሙሉ የምንጨርሰው እኛ ነን፤ የጭነቱ ባለቤት የሚፈልገው ጭነት የሚፈልግበት ቦታ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ያለውን ሂደት በሙሉ እንቆጣጠራለን፤ አሽከርካሪው የጭነቱ ትዕዛዝ ወስደው ማጓጓዝ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ መዳረሻው እስኪረጋገጥ ድረስ ያለውን ሂደት በሙሉ እንከታተላለን›› ሲልም አብራርቷል።

የክፍያ ሥርዓቱንም እንዲሁ መተግበሪያ ላይ መከታተል የሚችሉበት አሠራር መዘርጋቱን አመልክቷል። አገልግሎት የተሰጠበት ክፍያ ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም ስለሚለውም የጭነት የመኪናው አሽከርካሪዎች መከታተልና ማወቅ ይችላሉ። እስከ 75ሺ ብር ያለው ክፍያ በቴሌ ብር የሚፈጸም ሲሆን፣ ከዚህ ከፍ የሚል ሂሳብ ከሆነ ደግሞ ክፍያው በባንክ በኩል የሚፈጸምበት አሠራር መዘርጋቱን ያመላክታል።

በአሁኑ ወቅት የጭነት ተሽከርካሪ በሚፈለግበት ሰዓትና ቦታ ላይ የማግኘት ችግር እንዳለ የጠቆመው ሙሉዓለም፤ ይህንን ችግር ለመፍታት የተማከል የጭነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ እንዲኖር አድርገናል ይላል። የጭነት አገልግሎት በሚጠየቅበት አካባቢ አቅራቢያ ያሉ የጭነት መኪናዎች አገልግሎቱን እንዲሰጡ እንደሚደረግም አስታውቋል።

በዚህ መተግበሪያ መገልገል የሚፈቀደው ለደረቅ ጭነት ብቻ መሆኑን ገልጾ፣ የፋብሪካ ምርቶችን፣ ሸቀጦችን ጭምሮ ማንኛውንም ዓይነት ደረቅ ጭነት የማጓጓዝ አገልግሎት እንጂ የፈሳሽ ጭነት አገልግሎት እንደማይሰጥ ተናግሯል።

እንደ ወጣት መሉዓለም ገለጻ፤ ድርጅቱ ጀማሪ ስታርትአፕ ሲሆን፣ መተግበሪያውን ሥራ ላይ ከዋለም ሁለት ወራት አስቆጥሯል፣ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች አውርደውታል። ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችም ተመዝግበዋል። በዚህ በአጭር ጊዜ በመተግበሪያው በመጠቀም ከሶስት ሺህ 200 ኩንታል በላይ ጭነት ተጓጉዟል።

መተግበሪያ አገልግሎት ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም እያስተዋወቁ መሆኑን ጠቅሶ፤ ‹‹ብዙ ሰዎች በፍጥነት አገልግሎት መስጠት እንድንጀምር ይጠይቁናል። ደንበኞች ከሚሰጡት አስተያየት በመነሳት የምናስተካክላቸው በደንብ እያስተካከልን ስለነበር ቶሎ ወደ ተግበር መግባት ስላልቻልን ጭነት ባለቤቶችና የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ መኪናዎች በቀጥታ ሲያገናኙ ነበር። አሁን ግን እኛ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት ወስደን በመተግበሪያው የጭነት ሂደቱ አልቆ የተባለው ቦታ እስከሚደርስ ድረስ አሽከርካሪው እንከታተላለን ›› ይላል።

የክፍያ ሂደቱ ባለው ገበያ የሚወሰን ሆኖ፤ በኪሎ ሜትር እንዲከፍሉ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን ሙሉዓለም ያነሳል። የእቃው መጠንና የቦታው ርቀት ይህንን ያህል ተብሎ በኪሎ ሜትር ሂሳብ የተሰላ ስለሆነ በኪሎ ሜትር ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል። አገልግሎት ፈላጊው የጭነቱን ልክ ሲመዘግቡ የኪሎ ሜትሩና የጭነት መጠኑን ስለሚሰጣቸው የሚከፍሉት ክፍያው በዚያ ማወቅ ይችላሉ። ማሻሻያ የሚያስፈልገው ከሆነ በመነጋገር ማሻሻያው ተደርጎ እንዲያወቁት የሚደረግበት አሠራር እንዳለም ያስረዳል።

በኩንታል መጠናቸው አይታወቅም ተብለው የሚታሰቡ የቤት እቃ ዓይነቶቹን የክፍያ መጠን ለማወቅ የሚጫንበት መኪና ዓይነት ይወስነዋል የሚለው ወጣት ሙሉዓለም፤ በአይዙሱ፣ በኤፍ ኤስ አር፣ በፒካአፕ እና በመሳሰሉት የጭነት መኪና ዓይነቶች ሊጫኑ ስለሚችሉ የጭነቱ ባለቤት የሚያስጭንበትን የመኪና ዓይነት ከመረጠ በኋላ የተመረጠው መኪና የሚጨነው የኩንታል መጠን ስለሚታወቅ የኩንታል መጠኑን በኪሎ ሜትሩ አብዝቶ ሂሳቡን አስልቶ የሚያሳወቅ አሠራር እንዳለ አስታውቋል።

‹‹እስካሁን እየሰጠን ባለነው አገልግሎት የጭነት ባለቤቶች ወይም ደንበኞች አገልግሎታችንን እንደወደዱት አስተያየት ይሰጡናል። ‹ቀደም ሲል ጭነቱን ማን እንደጫነው የምናውቀበት ሁኔታ ስላልነበር የመኪናውን ታርጋ ብቻ ይዘን ነው በእምነት የምንሰጠው። የእናንተ መተግበሪያ ብዙ ነገሮች አቅልሎልናል ›ሲሉ አስተያየት ይሰጡናል›› ይላል።

በመተግበሪያው ዲጂታል ውል ወሰደው ጭነቱን ስለሚያጓጉዙ ማን እንደሚያጎጉዝና ጭነቱ የት እንደደረሰ ጭምር መከታተል የሚቻልበት አሠራር እንዳለም ጠቅሶ፤ አገልግሎቱን ወደፊት ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ለማያያዝ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝቧል።

ወጣት ሙሉዓለም እንዳብራራው፤ የኢትዮ ጭነት ሎጀስቲክ ቴክኖሎጂ ድርጅት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች እና ድርጅቶች ባሉበት ሆነው መተግበሪያውን በማወረድ ብቻ አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። የጭነት ባለቤቶች ኢትዮ ጭነት ኦነር መተግበሪያ በመጫን መመዝገብ ይችላሉ። የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ወይም ባለቤቶች /ኢትዮ ጭነት ድራይቨር/ መተግበሪያን በማውረድ ከፒካፕ መኪና ጀምሮ እስከ ትልቅ ሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች /የኤክስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ድረስ/ መመዝገብ ይችላሉ።

እንደ እሱ ገለጻ፤ የጭነት ባለቤቶች ጭነት ሲኖራቸው በመተግበሪያው ላይ ገብተው ትዕዛዛቸውን ያሳውቃሉ። የጭነት መኪናዎቹ በሄዱበት ቦታ ያንን ትዕዛዝ አይተው ክፍያውንና ሁሉንም ነገር በሙሉ አረጋግጠው መስማማታቸው በመግለጽ ውል ይወስዳሉ። ከዚያ ጭነቱን በተባለው ቦታ ያደርሳሉ። በዚህ ሂደት የጭነቱ ባለቤት ጭነቱ መድረሱን መከታተል የሚችልበት አሠራር መዘርጋቱን ያመላክታሉ።

‹‹የድርጅቱ የመጀመሪያ ጥቅሙ የማህበረሰቡ ችግር ተፈትቶ አገልግሎትን በቀላሉ መስጠት መቻሉ ነው›› የሚለው ወጣት ሙሉዓለም፤ ሌላው ድርጅቱ የሚያገኘው ጥቅም ደግሞ ከእያንዳንዱ ከሚጓጓዝ ጭነት ሦስት በመቶ ያህል ኮሚሽን ይወሰዳል። የጭነት አሽከርካሪዎች በመተግበሪያ ከተመዘገቡ በኋላ ለአንድ ወር ያለ ምንም ክፍያ መጠቀም የሚችሉ ቢሆንም፣ በዓመት 998 ብር ይከፍላሉ ሲልም አስገንዝቧል።

ሙሉዓለም እንደሚለው፤ መተግበሪያው የጭነት አገልግሎቱ እንዲሳለጥና ዲጂታል እንዲሆን ያስችላል። ዲጂታል ሆነ ማለት ደግሞ እያንዳንዱ የጭነት ተሽከርካሪ ፈላጊ በሚፈልግበት ሰዓትና ቦታ የጭነት አገልግሎት በአቅራቢያቸው እንዲያገኝ ያስችላል። የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ወይም ባለቤቶች በሚፈልጉበት ጊዜ ጭነት እንዲያገኙና የጭነት ትዕዛዝ ሳይኖራቸው ወደተለያየ ቦታ እንዳይሄዱ ያስችላቸዋል። ጭነት ፍለጋ ከአንዱ አካባቢ ወደ አንዱ በመጓጓዝ የሚወጣውን ወጪ ይቀንስላቸዋል። የተማከለ የጭነት አገልግሎት እንዲኖር ያደርጋል።

አሁን በሀገር ደረጃ የሎጂስቲክ ሥራው በማኑዋል እንደሚሠራ ጠቅሶ፣ አገልግሎቱን ለማግኘት ብዙ የደላላ ሰንሰለቶችን ማለፍን እንደሚጠይቅም አመልክቷል። ከዚህም በላይ የታሰበውን አገልግሎት ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻል። መተግበሪያው ለዚህ መፍትሔ መስጠቱን ገልጾ፣ ብዙ ቦታዎች ላይ ከደላሎች ጋር ከመደዋወል ይልቅ መተግበሪያውን በማውረድ በእጅ ስልክ ብቻ በመጠቀም በአጭር ጊዜ በአቅራቢያቸው ያለውን ጭነትና የጭነት ተሽከርካሪ እንደሚያገኙ አስታውቋል።

በቀጣይ ድርጅቱ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡትን የጉልበት ሠራተኞች በሲስተሙ እንዲገቡ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መሆኑንም ጠቁሟል። ከነዚህ የጉልበት ሠራተኞች የት ቦታ ላይ የሚጫን ወይም የሚራገፍ ጭነት አለ የሚለውን ከመተግበሪያው እንዲያገኙ በማድረግ የሥራ እድል እንዲፈጠርበት የሚደረግበት አሠራር እንደሚኖረውም ጠቁሟል።

ሙሉዓለም እንዳብራራው፤ ድርጅቱ በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እየገባ ስለሆነ ለ20 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዶ እየሠራ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ በአምስት ዓመት ውስጥ ከ21ሺ በላይ አሽከርካሪዎችን ወደ ዲጂታል ሲስተሙ ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ በመሆኑ በተዘዋዋሪም ለጭነት መኪና አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው የሥራ እድል ለመፈጠር አልሞ እየሠራ ነው።

ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ወራት ወደ ሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የጭነት አገልግሎት መስጠት መቻሉን ጠቅሶ፣ በቀጣይም በመላ ሀገሪቱ አገልግሎቱን በማስፋት ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል። አሁን ላይ በመተግበሪያው ብዙ የጭነት ባለቤቶች በመመዝገብ ላይ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ የመኪና ባለቤቶችም እንዲሁ ቢመዘገቡ በርካታ ሥራዎች ማግኘት የሚችሉበት ሰፊ እድል እንዳለም አመላክቷል።

‹‹ሥራውን ለማስፋት ደንበኞች ምን ይፈልጋሉ? የሚለው ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው›› የሚለው ሙሉዓለም፤ በነጋድራስ የንግድ ሥራ ውድድር ላይ መሳተፋቸውን ጠቅሷል፤ ይህም ሥራቸውን ለማስተዋወቅ ሰፊ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግሯል። ‹‹በውድድሩ ሁለተኛ በመውጣት የአምስት መቶ ሺህ ብር ሽልማትና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለ ማስያዣ 10 ሚሊዮን ብር ብድር አግኝተናል፤ ይህም ሥራችንን ለመስፋፋት በእጅጉ የሚያግዘንና ያለመነውን ግብ ለማሳካት ያስችለናል›› ብሏል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You