ትጋት በውጤት ሲታጀብ

ዜና ሐተታ

ትዳር ከያዘች ሁለት ዓመት እንደሆናት የምትገልፀው ዶክተር ትዕግስት የተመረቀችው የመጀመሪያ ልጇን ነፍሰጡር ሆና ነው:: መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓም የካቲት 12 ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ካስመረቃቸው ሴት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት:: ይች እንስት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች:: ዶክተር ትዕግስት በላይነህ በሕክምና ትምህርት ሦስት ነጥብ አምስት በማምጣት ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ሽልማቷን ተቀብላለች::

በሕክምና ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ብቻ ሳይሆን መመረቅ በራሱ ትልቅ ትግል እንዳለው ገልፃ፤ ለዚህ በመብቃቷ ፈጣሪዋን ታመሰግናለች:: ቤተሰቦቿ ከልጅነቷ ጀምሮ ለትምህርቷ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉላት እንደቆዩ የምትገልፀው ዶክተር ትዕግስት፤ ይህ ውጤት የእኔ ሳይሆን የቤተሰቦቼ ነው ትላለች::

ባለቤቴም ጥሩ ድጋፍ ያደርግልኛል የምትለው ዶክተር ትዕግስት፤ ትዳር ከያዘች በኋላ እንዲያውም የበለጠ በኃላፊነት ስሜት እንደተማረች ትገልፃለች::

ጥረት ካለ ሴትነት ከምንም ነገር እንደማይገድብ ጠቁማ፤ ከዚህ በላይ ጥረት ባደርግ ከዚህ በላይ ውጤት ማስመዝገብ እችል ነበር ትላለች:: ለየካቲት 12 ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና አብረዋት ለተማሩ ጓደኞቿ ምስጋና አቅርባ፤ በተለይ መምህራኑ ለውጤታማነቷ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልፃለች::

ወደ ፊት በተመረቀችበት ዘርፍ ለማገልገልና ራሷን በየጊዜው በትምህርት እያሻሻለች የበለጠ አገልግሎት ለመስጠት ማቀዷንም ታስረዳለች::

ሌላኛው ተመራቂ ዶክተር ኢፋ ደስታ ይባላል:: ሦስት ነጥብ ስምንት በማምጣት ባለ ከፍተኛ ውጤት የማዕረግ ተሸላሚነት ሜዳልያውን አጥልቋል:: ተወልዶ ያደገው ምዕራብ ወለጋ መሆኑን ይናገራል::

የሕክምና ትምህርት ብዙ ውጣ ውረዶች እንዳሉት የሚገልፀው፤ ዶክተር ኢፋ እንደምንም አልፎ ለዚህ መብቃቱን ይገልፃል:: ትምህርቱ ላይ ብቻ አተኩሮ ለዚህ እንዲበቃ በማድረግ የቤተሰብ አስተዋፅዖ ቀላል እንዳልነበርም ያስረዳል::

ኮሌጁ አብዛኛውን ደረጃዎች ያሟላ መሆኑን የሚገልፀው ዶክተር ኢፋ፤ ለእኛ ደግሞ የተለየ ቦታ ሰጥቶ አስተምሮናል ይላል:: በየደረጃው ሁኔታዎችን እያመቻቸ የተለያየ ዕድል እንደፈጠረላቸውም ይገልፃል::

በተለይም ለወጣቶች በታዳጊ ሀገር ከመኖራችን አኳያ በየቦታው ብዙ ተግዳሮት አለ የሚለው ዶክተር ኢፋ፤ እነዚህን ተግዳሮቶች መሸሽ ሳይሆን መጋፈጥ እንደሚኖርባቸው ይመክራል:: የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ፣ ዛሬ ያለፉበትን ለቀጣይ እንዲዘጋጁበትና ማኅበራዊ ግንኙነታቸው ማጠናከርና መረጃ መለዋወጥ እንዳለባቸው ገልጾ፤ ማንበብ ብቻውን ውጤታማ እንደማያደርግ ይጠቁማል::

በተለይ በሕክምና ትምህርት ብዙ ተግዳሮቶች አሉ የሚለው ዶክተር ኢፋ፤ ወደ መጨረሻ ብዙ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች እንደሚያልፉ ያስረዳል:: ነገር ግን እዚህ ጋር ለመድረስ ለእነዚህ ተግዳሮቶች ከመሸነፍ ይልቅ መበርታት እንደሚገባ ይጠቁማል::

ከቃለ መሐላው በፊት ገና ሙያውን ለማጥናት ስትገባ እምነቱን ጥሎብህ ለሚመጣው ተገልጋይ ከሚጠብቀው በላይ ሆኖ መገኘት እንደሚገባም ይገልፃል:: ሰውን ለማገልገል ሰው መሆንና ሕሊና ከቃለ መሐላ በላይ መሆናቸውን ይናገራል::

ኮሌጁ ባለፈው ዓመት ያገኘው እውቅና እንደነበረ ገልፆ፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ራሱ ብዙ ለውጦች እያሳየ እንደሚገኝ ይጠቁማል:: አንድ የሚጎለው ነገር ቢኖር የራሱ የሆነ የተማሪዎች ማደሪያ አለመኖሩ ነው የሚለው ዶክተር ኢፋ፤ ከዚህ ውጪ ለትምህርቱ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ያሟላል ብሎ እንደሚያምን ያስረዳል::

በየካቲት 12 ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኃላፊ ዶክተር አንተነህ ምትኩ በመርሐ ግብሩ ላይ ኮሌጁ እ.ኤ.አ በ2030 የጤና ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለመሆን ስትራቴጂክ ዕቅድ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: አገልግሎቱን በማስፋት በአሁኑ ጊዜ በቅድመ ምረቃ የትምህርት መርሐ ግብር የሕክምና ዲግሪን ጨምሮ በአጠቃላይ 19 የትምህርት ፕሮግራሞች እያስተማረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል::

በትምህርትና ምርምር ዘርፍ የቅድመ ምረቃ የሕክምና ትምህርት አሰጣጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ሥልጠና ባለሥልጣን በኩል የቀረበውን የሕክምና ትምህርት እውቅና በግንባር ቀደምነት መቀበሉንም አስታውሰዋል:: ለአንድ ዓመት ተኩል ያህልም አስፈላጊውን የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቶችን በመዘርጋት፣ ተፈላጊውን ሰነድ በማዘጋጀት፣ የተጀመሩትን የሕክምና ፕሮግራሞች በማስገምገም እንደሀገር ብቸኛ ተቋም መሆኑን አንስተዋል::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው ኮሌጁ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ማስመረቁን ጠቅሰው፤ ኮሌጁ የሠለጠነ የሰው ኃይልን ከማቅረብ አኳያ እያደረገ ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል::

ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ከመምህራኖቻቸው የቀሰሙትን እውቀት፣ ሙያና የሕይወት ተሞክሮ ጋር ቀምረው ለከተማዋ ብሎም ለሀገሪቱ የጤና ችግር መፍትሔ እንደሚፈልጉ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ነው የገለጹት::

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You