
– በሲዳማ ክልል የተገነባው ‘ኢፋ ቦሩ’ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ
ሀዋሳ፡- የኦሮሚያና የሲዳማ ክልል ሕዝቦች ያላቸውን አንድነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ክልሎቹ በጋራ መሥራታቸውን እንደሚያጠናክሩ የአሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ ። በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ድጋፍ በሲዳማ ክልል ለኩ ከተማ የተገነባው ‘ኢፋ ቦሩ’ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል።
በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ዞን ለኩ ከተማ በኦሮሚያ ሕዝብና መንግሥት 170 ሚሊዮን ብር ፈሰስ ተደርጎበት የተገነባውን የለኩ ከተማ ቦሩ ኢፋ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን የአሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ በትናንትናው እለት በጋራ መርቀው ከፍተዋል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ክልሉ በትምህርት ዘርፍ እየሠራ ያለውን ሥራ አድንቀው የኦሮሚያ ክልል ለሲዳማ ክልል ያደረገው የትምህርት ቤት ግንባታ አበርክቶም ጅማሮ መሆኑ ጠቅሰዋል። በቀጣይ የጋራ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር ሁለቱ ሕዝቦች ያላቸውን አንድነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ሁለቱ ክልሎች አንድ ታሪክ ፣ ቋንቋና ጎሳን የሚጋሩ ናቸው ያሉት አቶ ሽመልስ ፤ ባለፉት ዓመታት የሁለቱ ሕዝቦች አንድነት በብዙ ውጣ ውረድ ያለፈ ቢሆንም ያንን በመሻገር የተለያዩ ስኬቶችን አስመዝግበው እዚህ ደርሰዋል ብለዋል። ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትምህርት ላይ ትኩረት ተደርጎ በሁሉም መስክ መሠራት አለበት ሲሉም ፕሬዚዳንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሲዳማ ሕዝብ በብዙ ፈተና አልፎ ክልሉን ለማደራጀት በርካታ ሥራዎች መሥራቱን ያደነቁት ፕሬዚዳንቱ፤ በቀጣይ ቀናት መጋቢት 18 እና 19 ክልሉ ለሚያከብረው የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ ዋዜማ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ፤ የኢፋ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደ ስሙ የነገው ትውልድ ተስፋ ነውና የኦሮሚያ ሕዝብና መንግሥት ስላደረገው አበርክቶ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። የሁለቱ ሕዝቦች አንድነት ዛሬ ላይ የተጀመረ አይደለም ያሉት አቶ ደስታ፤ ሲዳማ እንደ ክልል ሲመሠረት የኦሮሚያ ክልል የነበረውን ከፍተኛ አስተዋፅኦና ድጋፍም አስታውሰዋል።
የሲዳማ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት እና የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ ትምህርት ቤቱ የሁለቱ ሕዝቦች የትብብርና የትስስር እንዲሁም አብሮ የማደግ ምልክት ነው ሲሉ ገልፀዋል ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈ እና እያሻሻለ እዚህ ደርሷል በማለት ገልፀው ዘርፉ ልዩ ትኩረትን የሚሻ በመሆኑ በዚሁ መሠረት የሲዳማ ክልል ‹‹የሲዳማ ትምህርት ተሀድሶ ፕሮግራምን›› ቀርፆ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ፕሮግራሙ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማስፋትና ነባር ትምህርት ቤቶችን በማደስ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው ፤ እስከ አሁን በተሠራው ሥራም ተስፋ ሰጪ ውጤት ታይቷል ብለዋል።
በኦሮሚያ ሕዝብና መንግሥት በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ዞን ለኩ ከተማ የተገነባው ኢፋ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የከተማው ማህበረሰብ በተገኙበት በትናንትናው እለት ተመርቋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት በክልሉ ላስገነቡት ትምህርት ቤት ከሲዳማ ክልል እና ሕዝብ የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም