የትግራይ ወጣቶች ዘመኑን የሚመጥን በሳል ፖለቲካዊ አካሄድን ይሻሉ!

የትግራይ ክልል ሰላም እና ልማት ከሁሉም በላይ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ ነው ። በጉዳዩ ዙሪያ የትግራይን ሕዝብ እንደ ሕዝብ የምወክል እኔ እና እኔ ብቻ ነኝ ፤ ከኔ በላይ ለአሳር ብሎ ማሰብ ሆነ አደባባይ ሞልቶ መጮህ በተለይም ካለንበት ዘመን የፖለቲካ እሳቤ አኳያ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ነውር ጭምር ነው።

የትግራይ ሕዝብ በየትኛውም መንገድ የሚመቸውን መምረጥ ፤ በሚፈልገው የመወከል ሠብዓዊ እና ሕገመንግሥታዊ መብት አለው። ለዚህም በቀደሙት ጊዜያት ብዙ ዋጋ የከፈለና ወደፊትም ለመክፈል የሚከብደው ሕዝብ አይደለም ። ምን እንደሚፈልግ እና የፈለገውን እንዴት እንደሚያገኝም ከትናንቶች ብዙ የተማረ ነው ።

በተለይም የትግራይ ወጣት ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ከመጣባቸው መንገዶች እና መንገዶቹ ካስከፈሉት እና እያስከፈሉት ካለው ያልተገባ ዋጋ አንፃር ፤ ነገዎቹን ብሩህ እና የራሱ ለማድረግ የሌሎችን ጣልቃ ገብነት የሚፈልግ አይደለም። የራሱን ዕድል በራሱ ለመወሰን የሚያስችል ተጨባጭ የሕይወት ተሞክሮ ባለቤት ነው።

እንደቀደሙት ዘመናት በፍረጃ ጠላት እየተፈጠረለት ፤ ከተፈጠሩለት “ጠላቶቹ ” ጋር በሚያደርገው ትርጉም የለሽ ግብ ግብ ውድ የሆነውን ሕይወቱን እየገበረ ፤ በራሱ ነገዎች ላይ እያመጸ የሚኖርበት ዘመን አብቅቷል። አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብም ሆነ የትግራይ ወጣት እጣ ፈንታ በሆነ ቡድን የሚወሰን አይደለም።

የትግራይ ወጣት በነጻነት፣ በዲሞክራሲ እና በፍትህ ስም በቀደሙት ዘመናት የሕይወት ዋጋ ከከፈሉት ወንድም እህቶቹ መራራ ሕይወት ብዙ ተምሯል ። ከነጻነት እና ከፍትህ ተጋድሎ ትርክቶች በስተጀርባ ስለነበረው እና ስላለው ተጨባጭ እውነታ አሁን ላይ ነጋሪ /ሰባኪ የማይፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል ። ከራሱ ሕይወት በቂ ተሞክሮ አካብቷል።

ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ፤ፍላጎቱን ለማሟላት ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል ። የራሱ የሆነ ፣ ዘመኑን የሚዋጅ አስተሳሰብ ባለቤት ነው ። አሁን የሚፈልገው መደመጥ ነው። አሁን የሚፈልገው የራሱን ዕድል በራሱ የሚወስንበትን እድል ነው ። አሁን የሚፈልገው ራሱን መሆን ነው ።

ከምንም በላይ የሚፈልገው ዛሬን ከትናንቶች የተሻለ ፤ ነገን ደግሞ ከዛሬ የተሻለ የሚያደርግ የሰላም እና የልማት መንገድን ነው ፤ ሁለንተናዊ ሰላም የሰፈነበት ሕይወት መምራት ነው፤ እንደትውልድ የራሱን የሕይወት ትግል አሸንፎ ፤ ለመጪው ትውልድ የተሻለ ዛሬን ፈጥሮ በሰላም እና በብዙ ተስፋ ማለፍ ነው። ይህ ደግሞ እንደ አንድ ጤነኛ ትውልድ የሚጠበቅበት ነው።

ከዚህ ውጪ የትግራይ ወጣትን ትርጉም አልባ ለሆኑ የትናንት አጀንዳዎች እና የቡድን መሻቶች / ፍላጎቶች የመስዋዕት በግ አድርጎ ለማቅረብ የሚደረጉ ጥረቶች ትውልዱን የሚመጥኑ አይደሉም ፤ የትውልዱን አሁናዊ ንቃተ ህሊና አሳንሶ ከማየት የሚመነጭ ያልተገባ ምልከታ ውጤት ነው። ፍጻሜውም ማንንም ተጠቃሚ ሊያደርግ የማይችል ፤በብዙ አክሳሪ ነው ።

የትግራይ ሕዝብም ሆነ የትግራይ ወጣት በየአደባባዮቹ ድምጹን ከፍ አድርጎ እያሰማ ያለው ስለ ሰላም እና ልማት ነው ። ይህንን ተጨባጭ ሊያደርግለት ከሚችል ሃይል ጋር ህብረት እና መስማማት አለው። የተሟላ ድጋፍ የሚያደርገውም ከዚህ መሻቱ ጋር ለተስማማ ሃይል ነው ።

ከዚህ ውጪ በሃይል እና በማስፈራራት ፤ በዛቻ እና በፍረጃ ሕዝብን አስገድዶ ለማያምንበት አጀንዳ ማሰለፍ አይቻልም። ይህንን ለማድረግ መሞከርም አንድም የሕዝብን ውሳኔ ያለመቀበል፤ ካልሆነም ፍጹም አምባገነን የመሆን እና የተስፋ መቁረጥ ጉዞ ጅማሬ ነው!

አዲስ ዘመን  መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You