
በተፈጥሮ ሀብት፣ በሕዝብ ብዛትም ሆነ በአኩሪ ታሪክ ከአፍሪካ በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፤ የውሃ ሀብቷ፣ ከኢጋድ ሀገሮች መካከል አንድ ሶስተኛውን የሕዝብ ብዛት ቁጥር መያዟ እንዲሁም በቅኝ ያለመገዛት ታሪኳ ሰርክ የሚታወስ ነው። ታዲያ የእዚህ ሁሉ ፀጋዎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ለምን ድርቅ፣ ረሃብ፣ ስደት እና ግጭት መገለጫዎቿ ሆኑ የሚሉት ጥያቄዎች ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆነው ዛሬም ድረስ ዘልቋል።
ኢትዮጵያ ባላት አቅም ልክ ማደግ ያልቻለችበት እና ዜጎቿ በድህነታቸው ምክንያት አንገታቸውን ቀና ያላደረጉበት መንስኤዎች የተለያዩ መሆናቸው ቢነገርም፤ በዋናነት የውጭ ሴራ ስለመሆኑ ደጋግመው የሚገልጹ ብዙ ናቸው። ድርቅ፣ ረሃብ፣ ስደት እና ጦርነት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የተንሰራፋ መሆኑ የታወቀ ሃቅ ነው። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እና ሀገራቸውን ለማበልፀግ በየዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያም ሆኑ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መንግሥታት በየአቅማቸው በየዘመናቸው ጥረቶችን ማድረጋቸውን መካድ አይቻልም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያንንም ሆነ አጠቃላይ አፍሪካውያንን ከችግር እና ከመከራ የሚያወጣ መፍትሔ አልተገኘም። መንግሥታቱም መፍትሔ ከማፈላለግ አልቦዘኑም።
ኢትዮጵያን ከችግሯ እንድትላቀቅ እየተወሰዱ ካሉ የመፍትሔ ርምጃዎች መካከል ዋነኛው የሀገሪቷን የተፈጥሮ ሀብት በተለይም ውሃን በአግባቡ በመጠቀም ኃይል መሸጥ እና ከውሃ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን መሥራት አንደኛው ነው። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ እየተሳካላት መሆኑን በሕዳሴው ግድብ እየታየ ይገኛል። ሌላኛው የባሕር በር ባለቤት የምትሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። በዚህ እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የዕለቱ የወቅታዊ እንግዳ ያደረግናቸው የታሪክ ምሁር አሕመድ ዘካሪያን (ረዳት ፕሮፌሰር) ነው። ከእርሳቸው ጋር የነበረንን ቆይታ በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልገኛል የሚል ሃሳብ ሰንዝራለች። ይህንን ተከትሎ የተለያዩ ትርጓሜዎችን ሲሰጡ ይሰማሉ። በቅድሚያ ይህንን በተመለከተ ምን ይላሉ?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- ባሕሮች የዓለም ሕዝብ ንብረት ናቸው። በባሕሮቹ ላይ ሁሉም ድርሻ አለው። አትላንቲክ ውስጥ እኛም ድርሻ አለን። እዚያም ቢሆን የአቅም ጉዳይ ነው። ባሕሮችን እንዴት እንጠቀምባቸው የሚለው ሁሌም የተባበሩት መንግሥታት ጥያቄ አለ። አትላንቲክ ላይ ያለው ሀብት ለሁሉም የሚነሳ ጥያቄ ነው። ባሕሩን አትጠቀሙ ማለት አይቻልም። መርከቦቻችንን አይስሩ ማለት አይቻልም። የግድ መሥራት አለባቸው። ጅቡቲ ላይ ከአሥር በላይ ሀገራት ከሩቅም ከቅርብም መጥተው ቤዝ መስርተዋል። ኢትዮጵያ አትጠቀም የሚለው ዓይን ያወጣ ክርክር ነው።
ግብፆች ሰዎችን የሚያበሳጭ ቀልድ ይችላሉ። በእነርሱ መበሳጨት የለብንም። ኢትዮጵያውያኖች መሥራት ያለብንን መሥራት ነው። እነርሱ አሉ ብሎ መደናገጥ አያስፈልግም። ለእነርሱ መልስ ለመስጠት ጊዜ ማባከን ተገቢ አይደለም። የዓለምን የዲፕሎማሲ ሥርዓትን ባላገናዘበ መልኩ የአፍሪካን ቻርተርም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተርን መሠረት አድርጎ መንቀሳቀስ እንጂ ሌሎች የሚናገሩት ነገር ብዙ ሊያስጨንቀን አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- የግብፅ መንግሥት የአፍሪካን ቀንድ ለመቆጣጠር ወይም አካባ ቢው ላይ ሰላም እንዳይሰፍን የሚሠራበት ሁኔታ እንዳለ ይነገራል። እውነት ነው?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡– ይሄ የግብፅ ፍላጎት አሁን የመጣ አይደለም። ከጥንት ጀምሮ አካባቢውን የማስተዳደር እና የመቆጣጠር ምኞት እንዳላቸው የታወቀ ነው። በመካከለኛውም ዘመን ኢትዮጵያ እና ግብፅ እንኳ ሰላምታቸው የሞቀ ነበር። አንዴ ይቀዘቅዛል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይሞቃል። ከሃይማኖትም ጋር ተያይዞ እሰጣ አገባ ውስጥ ነበሩ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጠቅላላ የዓባይ ሸለቆን እንቆጣጠራለን የሚል ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። ወደ ኢትዮጵያ የዘመቱበትም ጊዜ ነበር።
አሁንም በቋንቋም፣ በባሕልም፣ በሃይማኖትም ሆነ በአካባቢም ቀዳዳ እየከፈቱ ውስጣችን ይገባሉ። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው እኛ የተወሰነ ክፍተት ስናሳይ እነርሱ ያንን እየተጠቀሙ ወደ ውስጥ መግባታቸው የተለመደ ነው። አዲስ አይደለም።
በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ በተፋሰሱ ሀገሮችም በተለያየ መልኩ የቴክኒክ ድጋፍ ብለው እስከ ውስጥ ድረስ ይገባሉ። ለመቆጣጠር ይሞክራሉ። እኛም ጋር በተለያየ መልኩ ብዙ ሙከራዎችን አድርገዋል። የዛሬ አርባ ዓመት አካባቢም እንዲሁ ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር። አሁን የሚሠሩትም ሆነ በተደጋጋሚ የሚያቀርቡት ጥያቄ አዲስ አይደለም። ያለ እና የሚኖር ነው። ግብፆች የሳይኮሎጂ ችግር አለባቸው። ኢትዮጵያ ካደገች እኛ ድሃ እንሆናለን የሚል የመንፈስ ጭንቀት አለባቸው። አብረን እንደግ የሚለውን ሃሳብ አይቀበሉትም። ሃሳባቸው ሁልጊዜም እናንተ ድሃ ሆናችሁ እኛ ብቻ እንበልፅግ የሚል ነው። እኔ በበላሁት አንተ ተፈወስ የሚል የማይሆን ሃሳብ ደጋግመው ያስተጋባሉ። ባለኝ ግንዛቤ ግብፆች ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለኢትዮጵያ አንዴም አልተኙም።
አዲስ ዘመን፡-ግብፆች ምን ያህል ኢትዮጵያ ላይ እየሠሩ ነው?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- ውሃን በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘነበውን ዝናብ እያንዳንዷን ጠብታ ይቆጣጠራሉ። በተለያየ ስም የሚመጡትም ሆኑ ዲፕሎማቶቻቸው እንዲሁም የግብፅ ምሁራን እና አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሠራተኞቻቸው የሚመጡት ስለውሃው መመሪያ ተሰጥቷቸው ነው። አንድ ብርጭቆ ውሃ ቀነሰ ብለው ሪፖርት ያደርጋሉ። እነርሱ ውሃውን መቆጣጠር የሚፈልጉት እስከዚህ ድረስ ወርደው ነው። ውሃውን በየቀኑ ይጠቀሙበታል። ስለዚህ ሕይወታችን ነው ብለው ያምናሉ። የውሃ ፍሰቱን በየጊዜው ያጠናሉ፤ ያለበትን ደረጃ ያውቃሉ።
ችግሩ አሁንም እነርሱ እንደቀደመው ብቻቸውን መጠቀም ይፈልጋሉ። አትንኩት ይላሉ። ነገር ግን ይህ የማይሆን ነገር ነው። እኛም 130 ሚሊየን አካባቢ ደርሰናል። መንካታችን አይቀርም። ቁምነገሩ ተባብረን አብረን የፈጣሪን ፀጋ እንቋደስ የሚለው ነው። እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ሞኝ ሆነን በትንሽ ምክንያት እነርሱ በሚያጋግሉት እሳት እየተለበለብን ቆይተናል። አሁን ግን ጊዜው ደርሷል። መንቃት ያስፈልጋል።
የተፈጥሮ ሀብታችንን በሥርዓት ማንንም በማይጎዳ መልኩ መጠቀም አለብን። የተፈጥሮ ሀብታችንን መንከባከብ እና እንዲበለፅግ ማድረግ ግዴታችን ነው። አፈሩ እየተከላ ለእርሻም እና ለግጦሽ የማይመች የሆነው በእነዚህ ወንዞች ምክንያት ነው። አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የኢትዮጵያ አካል የዓባይ ተፋሰስ የሚነካው ነው።
ዓባይ ከጣና የሚሄደው ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ ከኤርትራ ጀምሮ ትግራይን ይዞ እስከ ታች እስከ ጋምቤላ ድረስ ያለው ኦሮሚያን እና አማራን የሚያካልል ሰፊ ተፋሰስ ወደ ግብፅ እየነጎደ ነው። አንድ ሶስተኛውን የኢትዮጵያን አካል የያዘ በየቀኑ ለግብፆች ውሃ የሚሰጣቸው እና አፈር የሚገብርላቸው ዓባይ ነው። እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥርም መጠነኛ ስለነበር፤ እነርሱ ሲጠቀሙ ኖረዋል። አሁን ግን ቁጥራችን እየጨመረ ፍላጎታችንም እያደገ በመምጣቱ መጠቀም የህልውና ጉዳያችን ሆኗል።
ግብፆች የከርሰ ምድር እና የባሕር ውሃ አላቸው። እነርሱ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን አትጠቀም ሲሉ፤ በጣም የሚያስገርም ነው። በግልፅ ለኢትዮጵያ ውሃ እየከለከሉ ነው። ይህ ደግሞ ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ ዓይነት ነገር ነው። ስለዚህ የእኛ ግንዛቤ ማደግ አለበት ጠላትነትን ማወጅ ሳይሆን የእነርሱን ሁኔታ መግታት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርጉትንስ ጥረት እንዴት ያዩታል?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- እነርሱ ሁልጊዜም የእርጎ ዝንብ ናቸው። የአፍሪካ ቀንድን ብቻ ሳይሆን ሊቢያን፤ የመንም፣ ሶማሊያም፣ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራትም ሲንከራተቱ እናውቃለን። ግጭት ለመፍጠር ወደ ኋላ አይሉም። ለእኛ መፍትሔው መንቃት ነው። ሥርዓቱ ግብፅን ለማስተናገድ ቢሞክርም የሶማሊያ ሕዝብ እምቢ ብሏል። እኛም ወንድማማችነት እና እህትማማችነታችንን የበለጠ አጠንክረን ማስኬድ እና ማስረዳት ይጠበቅብናል። ያጓደልነው ነገር ካለ እርሱን ማስተካከል የግድ ይሆናል።
ግብፆች ግን እንደፈረንጆቹ ቅኝ እንግዛ ዓይነት ሃሳብ ያላቸው ናቸው። ሱዳንንም ሲያሰቃዩ ነበር። ከድርጊታቸው መማር አለባቸው። የሶማሊም ሕዝብ ይነቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሶማሊያውያን፣ ኢትዮጵያውያን አጠቃላይ አፍሪካውያን በብዙ መልኩ መንቃት አለብን።
መገንዘብ ያለብን አመራሩ እና ሥርዓቱ ሁልጊዜም የውስጥ ችግራቸውን የውጭ በማድረግ ኢትዮጵያን እያነሱ መጮሃቸው የሚያስገርም ነው። የዓባይን እና የቀይ ባሕርን ጉዳይ ሲያነሱ የሚያወሩት የሚገርም ተረት ተረት ነው። ኢትዮጵያ ምንም መብት የላትም ይላሉ። ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር 60 ኪሎ ሜትር እንኳ አትርቅም። የባሕሩ ወላፈን እኛ ላይ ነው።
እኔ በተደጋጋሚ ሃሳብ የማቀርበው ለግብፅ መገናኛ ብዙሃን እና ለመንግሥታቸው ሳይሆን ለግብፅ ሕዝብ በቀጥታ ሊደርሰው የሚችለውን ሃሳብ ነው። ሕዝቡ መንቃት አለበት። እንደመተት ያዞሩበትን ነገር መፍታት አለብን። ‹‹ ዓረብ ነን፤ እኛ ልዩ ነን›› የሚለው ስሜት የትም አያደርሳቸውም። ‹‹እኛ የአፍሪካ መሪዎች ነን፤ አፍሪካን እንቆጣጠራለን›› የሚለው ሃሳባቸው የትም አይወስዳቸውም። የሚሻላቸው ሥርዓት ባለው መልክ፤
ለግብፅ ሕዝብ በሚገባው መልኩ ትምህርት መስጠት ነው።
የባሕር በር በምንም መልኩ በሕግም ሆነ በማንኛውም መንገድ ብንከራከር የምናገኘው ነው። በወቅቱም ቢሆን የቅኝ ግዛት ጥያቄ ሆኖ የወንድሞቻችን ችግር እንጂ አሰብ የእኛ ነው። የነበረው መሪ ሲመጣ በወቅቱ ባጋጠመው ውጥረት የባሕር በራችንን ሰጠ እንጂ፤ የባሕር በራችንን ፈልጎ የሰጠም አይመስለኝም። እዛም ያለው አፋር እዚህም ያለው አፋር አንድ ነው። ሕዝቡ የሚነጣጠል አይደለም።
ነገር ግን እኛ ሞኝ ከሆንላቸው እነርሱ ሌላውን ቂላቂል ማድረግ የሠለጠኑበት ነው። ቀልደኞች ናቸው። በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት ዓይነት በሽታ አለባቸው። በእኛ በኩል ዋናው ጉዳይ መንቃት ነው። ማንም ሰው እንዲጎዳ አንፈልግም። የወሰን ጥያቄ አፍሪካ ውስጥ ሁሌም የሚያጋጭ ነው። የኮሎኒ ጥያቄ እንደገና የሚጠየቅ ነገር ነው። እንደገና ወንድማማቾችን የሚያገናኝ ሥርዓት መምጣት አለበት። ከዛሬ ስድሳ ዓመት በፊት ጀምሮ አንነካውም የተባለው ነገር ዛሬ የግድ መነካት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከሴራ ወጥተን ወደ መተባበር ለምን መሄድ አልቻልንም?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- የ2063 አጀንዳ አንድ እያደረገን ነው። አብረን መተሳሰር አለብን፤ ንግዱ መሳለጥ አለበት እያልን ነው። የመንገድ ፍሰቱ የአውሮፕላኑም ሆነ የባቡሩ ሁኔታ ማደግ አለበት። አፍሪካ ውስጥ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ለመነገድ የንግድ ቀጣናዎች እየተቋቋሙ ነው። ድሬዳዋ እንደዛ ዓይነት ሁኔታ ታይቷል። ያንን መጠቀም ይገባል። አሁን የተለያዩ አፍሪካ አቀፍ ስብሰባዎች እየተካሄዱ ነው። የሁሉም ዓላማ እንቀናጅ፣ አብረን እንሁን እና አብረን እንሥራ፣ እንተባበር የሚል ነው።
ሩዋንዳን እንደ ምሳሌ ማንሳት ጥሩ ነው። አፍሪካዊ ሩዋንዳን ያለ ቪዛ መጎብኘት ይችላል። ይህም ትልቅ ለውጥ ይዞ መጥቷል። የ2063 አጀንዳ ትልቅ ለውጥ ይዞ እየመጣ ነው። አፍሪካ እየነቃች ነው። የኮሎኒ እና የሂትለር አስተሳሰብ ሄጄ በመምታት እቆጣጠራቸዋለሁ የሚለው መንፈስ እያበቃለት ነው። ሕዝቡ ወጣቱ መንቀሳቀስ ይፈልጋል። ሲንቀሳቀስ መብት እና ግዴታውን አስከብሮ አብሮ ለመልማት ነው።
አፍሪካ ትልቅ እንድትሆን የወጣቱ እንቅስቃሴ መገደብ የለበትም። ሥርዓት መኖር አለበት። እኔ እዚህ ተወልጄ አፍሪካ ውስጥ እንደፈለግኩ ሥራ መሥራት አለብኝ። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያዊ ዶክተሮች አሉ። በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ብዙ ኢንጂነሮች አሉ። በርግጥ ግብፆችም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ብዙ ሀገራት እየሄዱ ይሠራሉ። መንቀሳቀስ እና መሥራት የስብዕና ጥያቄ ነው። አንተ አትደግ አትልማ የሚባል ነገር ለማንም አይጠቅምም። በትክክልም የሚበጀው መተባበር ነው። ለዚህም የ2063 አጀንዳ አንድ ያደርገናል የሚል ተስፋ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተካሔደውን ስምምነት እንዴት ያዩታል?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- ሁለቱ መሪዎች ተጨባብጠው አይተናል። ሁሉም ጥቅሙን ለማስከበር እንደሚሯሯጥ መታወቅ አለበት። ለምን ጥረት አደረግክ ብሎ መጨቃጨቅ አያዋጣም። እኛ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ መሥራት እንጂ እዚህ ሄዳችሁ ለምን እንደዚህ አደረጋችሁ ማለት አያዋጣንም። በቀጣይ ብዙ ምክክሮች ይደረጋሉ። ሚኒስትሮች እየተነጋገሩ ነው። ግብፅ ሄደው ቢነጋገሩም ምንም መጨነቅ አያስፈልግም።
ኢትዮጵያውያን ሶማሊያዎች ሲመጡ ሰላማዊ ድርድር ላይ ማተኮር ሥራችን ሊሆን ይገባል። ለምን ሄዱ ብሎ እነርሱን መከታተል ዋጋ የለውም። ዋናው ጉዳይ የራሳችንን የቤት ሥራ መሥራት ነው። እንዳየነው የሶማሊ ሕዝብ ግብፆችን የሚቀበልበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፡- ከሀገራት ጋር የሚካሄዱ ስምምነቶች እና አፈፃፀማቸውን በተመለከተ ምን ይላሉ?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- ሁልጊዜም የእኛ ትኩረት ሰጥቶ መቀበል ነው። እንደ አፍሪካዊነት ካየን ደግሞ የአንዱ ችግር የሌላው ችግር ነው። እኛ ሀገር ረሃብ ካለ፤ ስደት እና ጦርነት ካለ፤ ሶማሊያም ሆነ ሌሎች ጎረቤት ሀገሮች አካባቢ ረሃብ እና ስደት ይኖራል። ችግር እንጋራለን። ሰላም ኖሮ የፈጣሪን ፀጋ መቋደስ ደግሞ ተገቢ እና ሕጋዊ ጉዳይ ነው። ቢያንስ ሰጥቶ በመቀበል ማመን የግድ ነው። የእኛ ጥያቄ እንዝረፍ ሳይሆን ተባብረን እናልማ ነው።
የኢጋድ ሕዝብ ወደ 300 ሚሊየን ነው። በዚህ ውስጥ ከአንድ ሶስተኛ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያ የኢጋድን አንድ አምስተኛ ስፋት የያዘች ሀገር ናት። ኢጋድ 1986 ሲቋቋም ትኩረቱ፣ ንግግሩም ሆነ ስምምነቱ ተፈጥሮ ሀብት ነበር። በዋናነት ደግሞ ስምምነቱ በረሃማነትን መከላከል ላይ ነው። ከ10 ዓመት በኋላ በረሃማነቱን ትተው ወደ አጠቃላይ ልማት ቀየሩት። የመጀመሪያው ምክንያት ግን በኢጋድ ሀገሮች ውስጥ በረሃማነቱ 70 በመቶ ነበር። በረሃማነቱን ለመከላከል እና የተፈጥሮ ሀብትን አብሮ ለመጠቀም ድርጅቱ ተቋቋመ።
ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች ሀገሮች መልማት አለባቸው። ያንን እያደረግን ነው። የተፈጥሮ ሀብታችንንም እያጋራን ነው። ግብፆቹ የጠሉት ኃይል ማጋራታችንን ነው። ነገር ግን ወደፊትም ቢሆን ያለንን እናጋራለን። እስከ ታንዛኒያ እየሄድን ነው። እነዚህን ነገሮች ስናይ እኛ ድርሻችንን እየተወጣን ነው። ለሶማሊዎችም ቢሆን ዋቢ ሸበሌ እና ገናሌን እየሠጠን ነው። የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑ አብረን እንቋደሰው እያልን ነው። በዛውም አብረን ልንጋራቸው የምንችላቸው ነገሮች ላይ መነጋገርም ሆነ መደራደር እንዲሁም መወያየት እንችላለን።
መፎካከርም ሆነ ግጭት ለማንም አይጠቅምም። አብረን ተባብረን ያለንን ተካፍለን መብላት አለብን። ምክንያቱም አሁን የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጥንቃቄ የሚፈልግ ሆኗል። ምክንያቱም የአንዱ አያያዝ እና አጠቃቀም ሌላው ላይም ተፅዕኖ ይኖረዋል። የአረንጓዴ ዐሻራ እኛ ብቻ ብናለማ ዋጋ የለውም። መነጋገር የተፈጥሮን ፀጋ መጋራት እና መተባበር በመልካም ጎን መቀጠል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ልማት ለአካባቢው ሀገራት ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- የተፋሰሱ ሀገራት የሕዝብ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። በሌላ በኩል ግብፅ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብቷን በሥርዓቱ ከተጠቀመችበት ዝናቡም እየሰፋ ይመጣላታል። ግድቡ ላይ የምታነሳው ጥያቄ ነበራት። አሁን ግድቡ አልቋል። ነገር ግን አሁንም ውሃ አልተቸገረችም። አካባቢው በውሃ እየለመለመ ነው። እንደሚነገረው የአየር ፀባይ ይቀየራል እየተባለ ነው። ወደፊት ግብፅ ትለመልምና ኢትዮጵያ የውሃ እጥረት ሊያጋጥመን ይችላል። በርግጥ በነገው ላይ ርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ዋነኛው ጉዳይ አሁንም ቢሆን ግብፅ ከኢትዮጵያ የበለጠ ውሃ አላት። የከርሰ ምድር ውሃ አላት፤ በአንድ በኩል ሜዲትራንያን ባሕር በሌላ በኩል ቀይ ባሕር አላት። በምንም መልኩ በውሃ ጥም አትሞትም። ቴክኖሎጂዋን ማሳደግ ብቻ ይጠበቅባታል። ኢትዮጵያ ግን የውሃ ማማም ሆና ብዙ ችግሮች አሉባት። ቦታዋ እኩል አይደለም። የውሃ አጠቃቀማችንም ሆነ የውሃ ፍሰቱ የተለያየ ነው። ሌሎችም ከውሃ ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮች አሉብን። እኛ ውሃ ተጠምተን ሌላውን እያጠጣን እንደገና የምንወቀስበት እና ጠላት የሚኮፈስበት ምክንያት የለም። በሌላ በኩል ቀደም ሲል እንዳልኩት ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው ያንን እያየን ነው። ነገር ግን የሩቋ ወዳጅም ሆነች ጠላት ግብፅ ምንም ዓይነት የሴራ ሥራ ብትሠራ ቦታ ታጣለች ባይ ነኝ። ግብፅ አደብ ገዝታ አፍሪካዊ ሆና የተፈጥሮ ሀብት የምንቋደስበት መንገድ ላይ መነጋገር የግዷ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለአፍሪካውያን ትብብር ሲያነሱ የአፍሪካ ሕብረትን በተመለከተ ምን ይላሉ?
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- የአፍሪካ ሕብረት በሚፈለገው መጠን ስኬታማ ያልሆነበት ምክንያት የአቅም ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ። አንድ እንዳንሆን ለረዥም ጊዜ ተሠርቶብናል። ለዘመናት ተከፋፍለናል። አሁንም እየከፋፈሉን እኛም ለመከፋፈል ዝግጁ እየሆንን ነው። ድርጅቱን ስኬታማ ያላደረገው ሀገሮቹ ደካሞች ስለሆንን ነው። 55 አካባቢ ነን። ገና አሁንም ቁጥራችን ይጨምራል።
ባለፉት 30 ዓመታት በብዙ ተከፋፍለናል። ፍላጎታችን ጥንካሬ ቢሆንም፤ በጀታችን ከሌሎች ነው። የምንተዳደረው በሌሎች ነው። ስለዚህ የሌሎች ጣልቃ ገብነት እስካለ ድረስ የውስጥ ችግራችን ይፈታል ማለት ያስቸግራል። ይህንን ተገንዝበን በራሳችን በጀት ራሳችንን ችለን እስካልሠራን ድረስ ጥንካሬን ብንፈልገውም ዋጋ የለውም፤ ጠንካራ መሆን አንችልም። የአፍሪካ ሕብረት እያለ ከሶማሊያ ጋር ስምምነት ለማካሔድ አንካራ መሄድ ተገቢ አልነበረም። ይህ የሚያሳየው በሕብረቱ በኩል አቅም አለመኖሩን ነው።
በውጭ ርዳታ የሚሠራ ከሆነ፤ የትናንቱ የቅኝ ግዛት የኮሎኒ ስሜት መኖሩ አይቀርም። ይህ ደግሞ አፍሪካውያን ፀጋችንን እንዳንረዳ ያደርገናል። እነርሱም በዚህ ላይ ይሠራሉ። እኛም ያንን ሳንገነዘብ ከሥርዓቱ እንወጣለን። በየጊዜው እየተጯጯህን ችግራችንን እያባባስን እንሄዳለን። እንነቃለን እንላለን፤ ነገር ግን በተግባር ስንነቃ አንታይም። ሁልጊዜ አፍሪካ ትነቃለች (አፍሪካ ራይዚንግ) እንላለን። ነገር ግን በርግጥ ነቃን? ተብሎ ሲጠየቅ መልስ የለም። አንዳንድ ጊዜ አንድን አካል ካነቁት ይንፈራገጥ እና ብዙ ነገር ያጠፋል። እንደዛ ሆነን ይሆን? አንዳንድ ጊዜ ተኝተን ስንነሳ ንብረት እያጠፋን ነው? በበኩሌ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጥያቄዎች አነሳለሁ። ብዙ ጊዜ ችግር መደበቅ እንወዳለን። ችግር በመደበቅ ደግሞ መፍትሔ አይመጣም።
ሕብረቱ በመኖሩ ምን ተጠቀምን? ምን ተጎዳን? የሚለው ላይ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል። ይህ ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ መጠናት ያለበት ጉዳይ ነው። ከ60 ዓመት በላይ ማደግ ያልቻልነው ለምንድን ነው? ስሙ ተቀየረ እንጂ ተግባሩ አሁንም ገና ነው። በርግጥ የተወሰኑ ነገሮች ተሞክሯል። መሪዎቹ እርስ በራሳቸው እንዲገማገሙ ቢታሰብም ጊዜያዊ ወሬ ሆኖ ቀረ። እናም ቆፍጠን ብሎ ችግርን ተረድቶ መፍትሔ ማፍለቅ ያስፈልጋል። የችግሩ መፍትሔ ከአፍሪካ ካልፈለቀ በሌሎች ገንዘብ እና ምክር መፍትሔ ይመጣል ብሎ ማሰብ በጣም ከባድ ነው። ችግራችንን ለመፍታት መሥራት ያለብን እኛ ባለቤቶቹ ነን። እኛ ብቁ ካልሆንን ሌላው በተቃራኒው በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት የሚል ነው። ይህንን ማወቅ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም አመሰግናለሁ።
አሕመድ (ረ/ፕ/ሮ)፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም