
አዲስ አበባ፡- የሀገርን የሳይበር ደህንነትን ለመጠበቅና ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተገነባ እንደሚገኝ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትእግስት ሃሚድ ገለጹ። ኢትዮጵያ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ልታዘጋጅ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በአዲስ አበባ የሚዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ አስመልክቶ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ ዲጂታላይዜሽን የሀገርን ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ለማሳለጥ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ነገር ግን ሊያመጣ የሚችለውን የደህንነት ስጋት መቆጣጠርና መከላከል ካልተቻለ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። እንደ ሀገር ይበልጥ ወደ ዲጂታላይዜሽን በገባን መጠን የሳይበር ወንጀሎች ስጋት በእኩል ደረጃ እየጨመረ ይመጣል። በመሆኑም የሀገርን የሳይበር ደህንነት ለመጠበቅና ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም ለመገንባት እየተሠራ ነው።
በተለይም በአሁኑ ወቅት እተስፋፉ ያሉት እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የመሰሉ ቴክኖሎጂዎች በመጡበት ወቅት የሳይበር ጥቃት በአይነትም ሆነ በመጠን በእጅጉ እየጨመረ ይመጣል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ እንደ ሀገር የመከላከል ሥራዎችንም በዚሁ መጠን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና ቅንጅታዊ አሠራርን በማሳለጥ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያዘጋጁት ኤክስፖ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሳይበር ጥቃትን በመካለከል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሊኖራት የሚገባውን ተጠቃሚነት ለማሳደግና በዘርፉ ያላትን አቅም ለማሳየት ይረዳል ብለዋል።
ወርቁ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፤ ቴክኖሎጂ ከቅንጦት ይልቅ ለህብረተሰብ ስለሚኖረው አስፈላጊነት ያለው ግንዛቤ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። በተለይም በአፍሪካ በጤናው፤ በትምህርት፤ ድህነትን በመቀነስና የምግብ እጥረትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መፍትሄዎችን ለማመላከት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ መሠረተ ልማት ባልተሟላላቸው ታዳጊ ሀገራት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለማህበረሰቡ በርካታ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል። ከዚህ አኳያ ኤክስፖው ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች ያስመዘገበችውን ስኬት ለማሳየት ፤ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እንደ ሀገር የተገኙ ውጤቶችን ለማስተዋወቅ የሚያስችል መድረክ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪ ሀገሪቷ በቴክኖሎጂው መስክ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መስጠት የምትችለውን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅና ቀጣይ ትስስሮችን ለመፍጠር የሚጠቅም ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ከግንቦት 8 እስከ 10 በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል እንደሚካሄድ ተገልጿል። በኤክስፖው ከ100 በላይ የሀገር ወስጥና ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ከ50 በላይ ስታርትአፖች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡ ይሆናል። ከ20 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡና የተለያዩ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ከአስር ሺህ በላይ ታዳሚዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም