ለሕዝብ የሚያስበው ማን ነው?

ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 በፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን እና ብሔራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ዕልባት አግኝቷል። የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ ዕርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመርና የሀገሪቱን የድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት እንዲከበር የማድረግ ዓላማ ያለው ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እንዲሁም ይህንን ተከትሎ በኬንያ ናይሮቢ የተፈረመው ባለ 12 ነጥብ የማስፈጸሚያ ሰነድ የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች የያዘ ነው።

የመጀመሪያው ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ማስከበር ነው። ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሚመነጭ ነው። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲካሄድ የማድረግ ሥልጣን ያለው የምርጫ ቦርድ እንደሆነ በግልጽ ተደንግጓል። ሆኖም ከዚህ ድንጋጌ በተቃረነ መልኩ በትግራይ ክልል ‹‹ምርጫ ›› ተካሂዷል በሚል የትግራይ መንግሥት መቋቋሙን ስሁት በሆነ መልኩ ለማወጅ መሞከሩ የሚታወስ ነው። በወቅቱም የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የተካሄደውን ‹‹ምርጫ›› እንዳልተካሄደ የሚቆጠር፤ በመግለጽ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቆ ነበር።

ይህንኑ ሃሳብ የሚያጸና ውሳኔ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ በተካሄደው ስምምነትም ሰፍሮ እናገኘዋለን። ምርጫው ሕገ ወጥ በመሆኑም በትግራይ የሽግግር መንግሥት ይቋቋማል፤ በሂደትም ምርጫ ተካሂዶ ክልሉን የሚያስተዳድር መንግሥት ይጸናል። ስለሆነም አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይ ሕዝብን ሰላም የሚያስጠብቀውና ሕጋዊ ውክልና ያለውም የፌዴራል መንግሥት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ በትግራይ ሕዝብ ተመርጫለሁ የሚል ሕጋዊ አካል የለም። ስለሆነም ከዚህ ውጭ የሚቀርቡ ጉዳዮች በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ተቀባይነት የላቸውም፤ በዚህ ጉዳይ ሊቀመጥ የሚችል ቅድመ ሁኔታም እንደሌለ በግልጽ ያስቀምጣል።፡

በሌላ በኩል የፕሪቶርያው ስምምነት በግልጽ ካስቀመጣቸው ነጥቦች ውስጥ ሌላኛው በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ መከላከያ ሠራዊት ብቻ መኖር አለበት የሚለው ነጥብ ነው። በስምምነቱ ላይ ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን ትጥቅ ማስፈታትን በተመለከተ ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የመከላከያ ኃይል ብቻ እንዳለ ከስምምነት የደረሱበት ጉዳይ ነው።

ይህንን ሁኔታ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ለማጓተት መሞከር አይችልም። በፕሪቶርያው ስምምነትም ሆነ በናይሮቢው የማስፈጸሚያ ሰነድ መሠረት ስምምነቱን ወደ ተግባር ከመለወጥ ውጪ ሊቀመጥ የሚገባ ቅድመ ሁኔታ አይኖርም። አሁን እንደሚታየው እስከ 200ሺ ሠራዊት እየቀለቡ ማስቀመጥ ከፕሪቶርያው ስምምነት ውጪ ነው።

ሌላው በፕሪቶርያው ስምምነት የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ውሳኔ ካሳለፉባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን የማስጠበቅ ሥልጣን የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ እንደሆነ በውል ሰፍሯል። በተለይም ከውጭው ዓለም ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችና ስምምነቶች ሁሉ ሊከናወኑ የሚችሉት በፌዴራል መንግሥት ብቻ መሆኑ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ነጥብ ነው። ይኸው ሃሳብም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 8 ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል።

በአጠቃላይ የፕሪቶርያው ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያጸናና የዜጎችን ሰቆቃ የሚቀርፍ ስምምነት በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚተገበር ነው። ስምምነቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤ የአማራና የአፋር ሕዝቦችን እፎይታ አጎናጽፏል።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ የሚያጸና ነው። በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችንና ሰብዓዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ለማድረስ መሠረት የጣለ ነው። በዚሁ መሠረትም በትግራይና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጠው የነበሩ የቴሌኮሙኒኬሽን፤ የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎቶች መልሰው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ አስችሏል። የሕዝቡን ችግር በፍጥነት ለመቅረፍም አሁንም ድረስ ሥራዎች በስፋት እየተሠሩም ይገኛሉ።

ሌላው የፕሪቶርያው ስምምነት የማዕዘን ድንጋይ ግጭትን በዘላቂነት ማስቆም ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ለ10 ቀናት ከመከሩ በኋላ በዘላቂ ግጭት ለማቆም ተስማምተዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ለማረጋገጥ በርካታ መስዋዕትነት የከፈለ ሕዝብ ነው። በመስዋዕትነቱም የሀገሩን ሉዓላዊነት አጽንቷል፤ አንድነቱን አጠናክሯል፤ ዳር ድንበር አስከብሯል። የኢትዮጵያን መፍረስ ለሚመኙ ባዕዳን በቂ ትምህርት ሰጥቷል።

ከላይ የተዘረዘሩት ዋንኛዎቹ የፕሪቶርያው ስምምነት አካል ሲሆኑ ስምምነቱ ከተፈረመበት ከጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ያለው አተገባበር ግን የተሟላ ነው ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል። በዚህ ረገድ በስምምነቱ መሠረት የተፈጸሙ ጉዳዮችን እና ቀሪ የቤት ሥራዎች ምንድን ናቸው የሚለውን መመልከቱ አስፈላጊ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ የፕሪቶርያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን የኢፌዴሪ መንግሥት በጽኑ ያምናል። ይሄንንም በተመለከተ የፌዴራሉ መንግሥት ከመነሻው እስካሁን ያለው አቋም ወጥ እና የማይናወጥ ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የፕሪቶርያው ስምምነት ከተፈረመበት ማግስት ጀምሮ ከአቋም ባሻገር ተግባራዊ እንቅስቃሴም አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። ከስምምነቱ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተመራ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች ያሉበትን ቡድን ወደ ትግራይ በመላክ የመጀመሪያውን ሰላማዊ ግንኙነት የጀመረው የፌዴራል መንግሥት ነው።

የፌዴራል መንግሥት ተቋማትና ክልሎች ለትግራይ ሕዝብ ድጋፋቸውን ያሳዩት ወዲያው ነው። የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በመቀሌ ተገኝተው ለሕዝቡ ያላቸውን አጋርነት በማሳየት የሚቻላቸውን ድጋፍ በዓይነትና በገንዘብ አድርገዋል።

በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት የገዢው ፓርቲ ሊኖረው የሚችለውን ድርሻ በመተው ሕወሓትና ወታደራዊ አመራሮች ጊዜያዊ መንግሥቱን እንዲያቋቁሙ አድርጓል። ምክንያቱም ከልዩ ልዩ አካላት ተውጣጥተው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የሚካተቱ አመራሮች እስኪተዋወቁና እስኪግባቡ ድረስ የትግራይ ሕዝብ የችግር ወቅት እንዳይራዘም በማሰብ ነው። በዚህም ለትግራይ ሕዝብ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ከፕሪቶርያው ስምምነት በላይ በመሄድ አረጋግጧል።

ለትግራይ ሕዝብ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲቻል የባንክ፣ የቴሌኮም፣ የመንገድ፣ የጤና፣ የትምህርትና የርዳታ ሥራዎችን የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች በትግራይ ተገኝተው ከክልሉ ቢሮዎች ጋር እንዲወያዩ የተደረገው የፕሪቶርያ ስምምነት በተፈረመ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነው። እነዚህ የሥራ ኃላፊዎች በጀትና ባለሙያዎችን በመመደብ በክልሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ አስችለዋል።

በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን የትምህርት ሂደት ለማስቀጠል ልዩ ልዩ ሥራዎች ተከናውነዋል። የሰው ኃይልና የተቋም ዐቅም ግንባታ፣ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ሥልጠና፤ የዩኒቨርሲቲዎችን የአመራር ቦርድ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል። በትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በኩል 165.8 ሚሊዮን ብር በዕቅድ ተካትቶ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል። ለአንደኛና ለሁለተኛ ሩብ ዓመታት ማስፈጸሚያ 517.9 ሚሊዮን ብር በገንዘብ ሚ/ር በኩል ለክልሉ ተልኳል።

በትምህርት ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት 1.46 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ በ2017 በትምህርት ቤቶች ላይ ለሚሠሩ ሥራዎች የ111.08 ሚሊዮን ብር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። የትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ 441.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል።

የሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ ተመልሷል። በፋብሪካና በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ አካላትን በመደገፍ ሥራ ጀምረዋል። ለወርቅ ሥራ የሚያገለግሉ ሁለት ከባድ ተሽከርካሪዎች በርዳታ ተለግሰዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የክልሉን የዘርፍ መሥሪያ ቤት ለማጠናከር ከተወሰዱ ርምጃዎች ባሻገር ለካፒታል በጀት 4.9 ቢሊዮን ብር፤ ለመደበኛ በጀት 11.4 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 400 ሚሊዮን ብር፤ በድምሩ 16.7 ቢሊዮን ብር በ2015/16 ለክልሉ ተሰጥቷል። በክልሉ ለሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በድምሩ 5.1 ቢሊዮን ብር ተላልፎላቸዋል። በልማት አጋሮች በኩል ደግሞ የ1.7 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ ተደርጓል።

ከእነዚህም በተጨማሪ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችን በማስተባበር እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር በክልሉ ባቋቋመው ጽ/ቤት በኩል፣ በትግራይ ለሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እና ለአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክቶች በድምሩ ከ565 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ ተደርጓል። የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክትም 65 ሚሊዮን ብር ለክልሉ ተላልፏል።

በጦርነቱ ማግስት የክልሉን የጤና ዘርፍ ዐቅም ለመገንባት እንዲቻል 164 ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ተመድበው ድጋፍ እንዲሰጡ ተደርገዋል። ሁሉንም በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት በመደገፍ ወደ አገልግሎት ለመመለስ የተቻለ ሲሆን፣ ሁሉም ሆስፒታሎች ተኝቶ የማከም አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ተችሏል። በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ሁለገብ እንቅስቃሴ 217 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ተችሏል።

በ2016/17 13.4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለክልሉ የቀረበ ሲሆን፣ ለ1427 አርሶ አደሮች መጠቀሚያ የሚሆን 1720 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በዚሁ የምርት ዘመን ፕሮጀክቶች በኩል ለክልሉ ተገዝቶ ሥራ ላይ ውሏል። ለዘንድሮ ዓመት የበጋ መስኖ 115ሺ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ተጓጉዟል። ለግብርና መገልገያ የሚሆኑ የትራክተሮች፣ የውኃ ፓምፖች ድጋፍ ለአርሶ አደሮች ተለግሷል። ሰሞኑንም 585 ትራክተሮችን ገዝቶ ለክልሉ አስረክቧል።

በሕወሓት ወገን ግን አሁንም በበርካታ ሺ የሚቆጠር ታጣቂ ትጥቅ አልፈታም። ሠራዊት አልተበተነም። እነዚህ ቡድኖች ሰብዓዊነት እና ፖለቲካን በመቀላቀል የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዳይመሰሉ ተግዳሮት ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም በጦርነቱ የተሳተፉ ወጣቶች በመልሶ ማቋቋም ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የሚደረገውንም ጥረት ሲያስተጓጉሉ ታይተዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣም እንቅፋት በመሆን ክልሉ ዳግም ወደ ግጭት እና ጦርነት እንዲገባ ሲገፋፉ ተስተውለዋል።

ከሁሉ በከፋ መልኩ ክልሉ ያለውን በጀት ለልማት እንዳያውለው ከ200ሺ በላይ ሠራዊት በማከማቸት እና በመቀለብ በወር እስከ 8 ቢሊዮን ብር በመገፍገፍ ትግራይ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንድትቆይ የተደረገበት መንገድ ከተስተዋሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው።

ስለዚህም እነዚህ የተሳሳቱ አካሄዶች ፈር ሊይዙ ይገባል። የጦር መሣሪያ በመሰብሰብ እና ታጣቂ በማከማቸት የሕዝብን ጥቅም ማረጋገጥ አይቻልም። የሕዝብ ጥቅም የሚረጋገጠው ሰላም በማስፈን፤ ልማትን በማረጋገጥ እና ዲሞክራሲን በማጠናከር ነው። ለሕዝብ የሚጠቅመው ትራክተር እንጂ የጦር መሣሪያ አይደለም። ስለዚህም በትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ከመናቆር እና ከግጭት አዙሪት በመውጣት የትግራይ ሕዝብ የሰላም አየር የሚተነፍስበትን መንገድ መቀየስ ይጠበቅባቸዋል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You