ኮንፈረንሶች፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እና መሬት ያልወረደው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው

“ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኮንፈረንስ እንድታስተናግድ መመረጧን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ”፤ “በተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት አዘጋጅነት “ርሃብ አልባ ዓለምን መፍጠር ይቻላል” በሚል ርዕስ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በኮንፈረንሱ ከ1500 በላይ ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ።”፤ “ሀገር አቀፍ የሕዝብ ኮንፈረንስ ከነገ ጀምሮ በ25 የኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች እንደሚካሄድ የብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ።” ዝርዝሩ ብዙ ሲሆን፤ ጥያቄው “ተጠቅመንባቸዋል ወይ?” የሚል ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያለፈውን ስድስት ወር አፈፃፀም በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት (መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ/ም) እንደተናገሩት “ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን አካሂዳለች። ይህ በአፍሪካ በቀዳሚነት የተመዘገበ ውጤት ነው።” አሁንም ጥያቄ ሆኖ በአእምሯችን ጓዳ ውስጥ ከተፍ የሚለው ያው ተመሳሳይ ጥያቄ ነው ፣ እሱም “ተጠቅመንባቸዋል ወይ?” የሚለው ነው።

ይህ ፀሀፊ እስከሚያውቀው ድረስ ጎብኚዎች ወደዚች ሀገር ይጎርፋሉ እንጂ አሟጠን ተጠቅመንባቸዋል ለማለት የሚያስደፍር ተግባር የለም። አክሱም ቢኬድ ልጆች የሆኑ፣ ከድንጋይ የሠሯቸውን መስቀልና የመሳሰሉትን ከ20 እና 30 ብር ያልበለጡ ነገሮችን ለሽያጭ ያቀርባሉ እንጂ የረባ ሱቅ እንኳን የለም።

አያቶቻችንን እጅግ እንድናደንቃቸው ከሚያደርጉን እጅ ሥራዎቻቸው መካከል አንዷ የሆነችውን፣ አዳዲ ማርያምን ለመጎብኘት ያ ሁሉ ፈረንጅ ይርመሰመሳል እንጂ እጁን ወደ ኪሱ እንዲያስገባ የሚያስገድደው (የሚያጓጓው) አንድም ነገር የለም። ሳማ ሰንበት ቢሄዱ (የቅርብ ጊዜውን ባላውቅም) አንዳንድ እዚህ ልንጠቅሳቸው ከማንፈልጋቸው ነገሮች ውጪ ሌላ ነገር የለም።

እነዚህ እግረ መንገድ የተነሱ እንጂ የዚህ ጽሑፍ አብይ ጉዳይ አይደሉም። የዚህ ጽሑፍ አብይ ጉዳይ (በተለይ፣ በዚህ ‹‹ኮንፈረንስ ቱሪዝም››፤ ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› ወዘተ እየተባለ በሚቀነቀንበት ሰአት) ኢትዮጵያ ከላይ የጠቀስናቸውን ኮንፈረንስ እዘጋጀች እንጂ “ተጠቀመች ወይ?” ከተባለ፤ መልሱ ቢያንስ በዚህ ፀሀፊ ደረጃ “አልተጠቀመችም” የሚል ነው የሚሆነው። ለምን? ከተባለ አሁንም መልሱ “ግልፅ አይደለም” ከሚለው የዘለለ አይሆንም።

የቅርብ ጊዜ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ (ረቡዕ ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም) የዓለም ባንክን የጠቀሰ ዘገባ እንደሚያሳየው በ2023 ከ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› በአውሮፓ የቱሪዝም ገበያ በግምት ከ401 ነጥብ 95 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በ2024 እስከ 459 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል ተብሎ ይገመታል።

በእስያ 183 ነጥብ47 ቢሊዮን ዶላር ከ‹‹ማይስ›› እንግዶች ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ በሰሜን አሜሪካ ከ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› ገበያ 130 ነጥብ 926 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ በኬንያ ከቱሪዝም ዘርፍ በየዓመቱ ከሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ በማግኘት ከቀጣናው በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። ሌሎችም ብዙ አሉ።

ይህ ጸሐፊ ካጋጠሙት ልምዶች አንዱን መጥቀስ ይፈልጋል። በአንድ ወቅት (በግል) ወደ ታንዛኒያ፣ ዳሬሠላም አቅንቶ፣ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ የተገማሸረ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ሆቴል (White Sands Resort & Conference Centre) በማረፍ ዓለም አቀፍ ሥልጠናና ሴሚናር ተካፍሏል። በሥልጠናውም ሆነ ቀጥሎ በነበሩት ቀናት በተካሄደው ኮንፈረንስ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች ነበሩ።

ይህ ሥልጠናና ኮንፌረንስ በተጠናቀቀ ማግስት (የሀገሪቱ መንግሥት ወይም ቱሪዝምን የሚመራው ተቋም ሥልጠናውን ካዘጋጀው አካል ጋር በመነጋገር ይመስለኛል) ከቁርስ በኋላ ምን የመሳሰሉ ሽንጣም መኪኖች ያረፍንበት ሆቴል በር ላይ ተደርድረዋል። “የታንዛኒያ መንግሥት ከተማዋንና ታሪካዊ ቦታዎቿን እንድትጎበኙ ጋብዟችኋል” በተባልነው መሠረት ወደየ መኪኖቹ ገባን። ከተማዋን ዞረን ጎበኘን። ደስ ትላለች።

ከጉብኝቱ በኋላ ደስ ያለንን እንገዛ፤ ከተማዋ ያፈራችውን እንቋደስ (በገንዘባችን) ዘንድ ያልተወሰድንበት የገበያ ማእከል፤ ያልጎበኘናቸው ሱቆች፣ ሞሎች፣ መርካቶን መሳይ ገበያዎች የሉም። ባጭሩ ማንም ያችን ያገኛትን ዶላር ይዞ ወደ ሀገሩ የተመለሰ የለም። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይህንን መልእክት ማስተላለፍ ሲሆን የሚመለከተው ያስብበት ዘንድ በመተው ወደ ሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንመለስ።

ከቱሪዝም ዘርፎች መካከል አንዱ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ነው። ከሀገር ውስጥ ቱሪዝም መካከል ኮንፈረንሶችና የመስክ ሥራዎች (ፊልድ) ጥቂቶቹ ናቸው። ቁጥሩ ተዘነጋኝ እንጂ አንድ ሰው ካለበት አካባቢ ከስንት ኪሎ ሜትር በላይ ከሄደ (ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን) እሱ የሀገር ውስጥ ቱሪስት ነው። ይህ የዚህ ፀሀፊ ምደባ ሳይሆን የዘርፉ ሳይንስ ግድ ያለው ነው።

በዚህ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ምክንያት ሰዎች ከቦታ ቦታ እንደሚዘዋወሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ በእነዚህ እንቅስቃሴዎቻቸውም ኪሶቻቸው አብሮ ተጓዥ መሆናቸው የታወቀ ነው። ልዩነቱ የስፋት እና ጥበት እንጂ ሌላ አይደለምና ልክ እንደ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ሁሉ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችም ገንዘባቸውን ያንቀሳቅሱ፤ ኢኮኖሚው ይዘዋወር ዘንድ ሁኔታዎች ያስገድዳሉ። “ግን ይህ እየሆነ ነው?” እየሆነ አይደለም።

እንደሚታወቀው በሀገራችን የየመሥሪያ ቤቶች አዳራሾች ከተረሱ ቆይተዋል። ስብሰባዎች፣ ውይይቶች … ከመዲናዋ አዲስ አበባ ውጪ ከሆኑ ሰነባብተዋል። ይሁን እንጂ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ገፅታ ይታይባቸዋል? በፍፁም አይታይባቸውም። ኢኮኖሚው ይንቀሳቀሳል? አይንቀሳቀስም። ኮንፈረንሶቹ የተካሄደባቸው አካባቢዎችና ህብረተሰቡ (ሆቴሉ አልተባለም) ከእነዛ ኮንፈረንሶች ተጠቅመዋል? አልተጠቀሙም። ለምን??

በግልፅ እንደሚታወቀው፣ ቱሪዝም ይመለከተኛል የሚሉ ተቋማት ሳይቀሩ ልብ ያላሏቸው ጉዳዮች አሉ፣ አንዱ የውሎ አበሎች ከአዲስ አበባ ያለመውጣት ጉዳይ ነው።”ድሮ” ወደ መስክ የሚሄድ ሰው እንደ ነገ ሊሄድ ሲል እንደ ዛሬ የውሎ አበሉን ከቢሮው (ሂሳብ ክፍል) ይቀበልና ከማምሻው ጀምሮ “የወጪ” ካለ በኋላ በለሊት ጉዞውን ይጀምራል።

በቃ፣ ልክ ጉዞው በተጀመረበት ፍጥነት ወጪም ይጀመራል፤ አሁንም አሁንም “እጅ ወደ ኪስ …” የግድ ይሆናል። በተደረሰበት ሥፍራ ሁሉ በእጅ የማይዳበስ ኪስ የለም። የተገኘው ይገዛል፤ የተገኘው ይበላል፤ የተገኘው ይጠጣል። ኢኮኖሚው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ድፍን ኢትጵያን ይዞራል፤ ይህም በኢኮኖሚስቶች ቋንቋ “ሕጋዊ የገንዘብ ዝውውር” በሚል ይታወቃል።

ዛሬ፣ አበል እሚከፈለው ለመስክ የወጣው ሰው ምግብና መኝታው ይቻለውና ክፍያው አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋለ በ”አካውንት” ነው። የአዲስ አበባ ኢኮኖሚ ከአዲስ አበባ እንዳይንቀሳቀስ የተባለይመስል ብሩ እዚሁ ነው የሚታሸው። ታዲያ ኢኮኖሚው በየት በኩል ይንቀሳቀስ? ለመስክ ሥራ ካሉበት አካባቢ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተንቀሳቀሱ ዜጎች እንዴት ሀገራቸው ያፈራችውን ምርት ይቋደሱ? ሊታሰብበት ይገባል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You