
ኢትዮጵያ ቡና፣ ሶያ እና በተወሰ መልኩ የእንጨት ምርቶችን ወደ አውሮፓ ገበያ ትልካለች። የምርት አቅራቢዎች እነዚህን ምርቶች ወደ አውሮፓ በሚልኩበት ጊዜ ምርቶችን የሚቀበሉ የአውሮፓ ሀገራትም ያስቀመጡትን መስፈርት ማሟላታቸውን እያረጋገጡ ይገዛሉ። ከመስፈርቱ አንዱ ምርት የሚልኩ ሀገራት ስለሚልኩት ምርት ትክክለኛ መረጃ ለተቀባይ ድርጅቶች መስጠት ወይም ስለአመራረቱ ሁኔታ ማብራራት ነው።
ከዚህ በፊት በአቅራቢው እና በድርጅቱ መሐከል ሊረጋገጥ የሚገባ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ እንደ ሕግ ተደንግጓል። ከዚህ መነሻነትም አንድ ላኪ ለአውሮፓ ገበያ ምርት በሚያቀርብበት ወቅት ከደን ጭፍጨፋ ጋር ያልተገናኘ፣ ከነጻ አካባቢ የተወሰደ መሆኑን ማረጋገጥ እና ስለ አካባቢው አጠቃላይ ሥነ-ምህዳር መግለጽ ይጠበቅበታል።
የአውሮፓ ህብረት እ.አ.አ በ2026 ተግባራዊ የሚደረግ “የአውሮፓ ህብረት ከደን ጭፍጨፋ ነጻ ደንብ” የሚል መመሪያ አውጥቷል። ይህን በተመለከተ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መድረክ ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ግርማ ማሞ እንደሚናገሩት፤ ከዚህ በፊት ወደ አውሮፓ ገበያ ምርት በሚላክበት (ኤክስፖርት) በሚደረግበት ወቅት አካባቢ፣ ማህበራዊ ኃላፊነት፣ የሥራ ደህንነት እና ሌሎች ሊረጋገጡ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ያነሳሉ።
እነዚህ ሊረጋገጡ የሚገባቸው ጉዳዮች አሁን አንድ ደረጃ አድገዋል፤ በተለይም ከደን ጭፍጨፋ ጋር ተያይዞ አውሮፓ ህብረት ሕግ አድርጓቸዋል። ከዚህ አኳያም ማንኛውም ሀገር ወደ አውሮፓ ሀገራት የሚያስገባው ምርት ከደን ጭፍጨፋ የጸዳ መሆኑን ላኪው ማረጋገጥ ይኖርበታል ሲሉ ይገልጻሉ።
ህብረቱ በአውሮፓ ገበያ ላይ ተጽኖ የሚያደርሱ ሰባት ምርቶችን ለይቷል። እነዚህ ምርቶች የደን ጭፍጨፋ ከተደረገበት መሬት አለመገኘታቸው የማስረዳት ኃላፊነት ላኪዎች ላይ ጥሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአውሮፓ ህብረት በተለየ ካስቀመጣቸው ምርቶች አንዱ ቡና ነው ይላሉ።
እንደሚታወቀው ቡና ከ30 እስከ 35 በመቶ ያለውን የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ድርሻ የያዘ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 30 በመቶ የሚሆነው ወደ አውሮፓ ገበያ የሚሄድ እንደመሆኑ ተጽኖው ከፍተኛ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአወሮፓ ህብረት መስፈርት ቡናን ጨምሮ የሌሎች ምርቶችን የኤክስፖርት አቅም ጥያቄ ውስጥ ያስገባል ሲሉ ይገልጻሉ። አነስተኛ አርሶ አደሮችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስለ ጉዳዩ በመገንዘብ በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል ሲሉ ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ህብረት ለኤክስፖርት ምርቶች ካስቀመጣቸው መስፈርቶች አንጻር በኢትዮጵያ የደን ሽፋን እየጨመረ በሌላ በኩል ደግሞ የደን ጭፍጨፋ እየቀነሰ መምጣቱ እንደመልካም እድል የሚወሰድ ነው ይላሉ።
ከ2000 እስከ 2013 ዓ.ም በተሠራ ጥናት በኢትዮጵያ 92 ሺህ ሄክታር መሬት ደን በዓመት ይጨፈጨፋል። በእነዚህ ዓመታት ሀገሪቱ ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት የደን ሽፋን አጥታለች። እ.አ.አበ2023 በተሠራ ጥናት የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል። በተጨማሪም የደን ጭፋጨፋውም በዓመት ወደ 27 ሺህ ሄክታር ዝቅ ለማለት ችሏል ሲሉ ያስረዳሉ። አብዛኛው ቡና አምራች ገበሬ የተመዘገበና የተደራጀ መሆኑን እንደተጨማሪ እድል የሚቆጠርና መረጃው የሚወሰደው ከሚታወቅ አምራች መሆኑም ጥሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
ያሉትን እድሎች በመጠቀም ከአውሮፓ ጋር የማግባባት ሥራ መሥራት ያስፈልጋል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ምናልባት የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ዲጂታላይዜሽን የመንግሥት አቅጣጫም ጭምር መሆኑ ሌላው መልካም አጋጣሚ ነው ይላሉ።
ከተሠራበት ግልጸኝነትን የሚጨምር እና ሀብታችንን ለማወቅ የሚያስችል እንደሆነም ይጠቅሉ። ሁሉም ባለድርሻ አካላት በግል እና ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ የወሰደውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ከቻለ ያን ያህል ለገበያው አስቸጋሪ የሚሆን ነገር እንደማይኖር ያስረዳሉ።
የግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዳለ ሀብታሙ በበኩላቸው እንዳስረዱት፤ የአውሮፓ ህብረት ያወጣው ሕግ የመነጨው ከኢንተርናሽናል ፕላንት ፕሮቴክሽን ኮንቬንሽን ነው። አሁን ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተለያዩ በሽታዎች ወደ ተለያዩ ሀገራት ይተላለፋሉ። ሀገራት ይህን እንዲቆጣጠሩ ኮንቬንሽኑ ያወጣው ሕግ እድል ሰጥቷል። ያወጣቸው ሕጎች አሁን አውሮፓ ህብረት ሊተገብረው የተዘጋጀውን ሕግ ብቻ ሳይሆን፤ ሀገራት የሚጠቀሙትን ማዳበሪያ እና ኬሚካል እንዲቀንሱ የሚያዝ ሕግ ጭምር ነው ይላሉ።
ሀገራት ማዳበሪያና ኬሚካል ሲቀንሱ ካላቸው ሥነምህዳር አንጻር ውጤቱ ይለያያል ያሉት አቶ ወንዳለ፤ ለምሳሌ ሲዊዲን፣ ዴንማርክ ፣ ኖሩዌይ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ስላላቸው የበሽታና የተባይ መከሰት እድሉ ዝቅተኛ ነው፤ ነገር ግን ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ከፍተኛ ሙቀት ወይም ከፍተኛ ቅዝቃዜ ስለሚኖር የበሽታ እና የተባይ የመከሰት እድሉ ከፍተኛ ነው።
በደን ጥበቃ የወጣው መመሪያም የዚሁ አካል ነው፤ በዚህም እያንዳንዱ አርሶ አደር የሚያመርተው ምርት ወደ አውሮፓ የሚላክ ከሆነ አጠቃላይ የአካባቢው ሁኔታ መገለጽ አለበት፤ ኢትዮጵያ ቡና የሚያመርት አምስት ሚሊዮን ገበሬ ቢኖራት፤ እያንዳንዱ አርሶ አደር መመዝገብ አለበት ሲሉ ያስረዳሉ።
እያንዳንዱን አርሶ አደር ለማሠልጠን ጊዜ የሚጠይቅና ወጪው እጅግ በጣም ከባድ ነው የሚሉት አቶ ወንዳለው፤ ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውሮፓ ህብረት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
በአውሮፓ ህብረት በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሠራው ተቋም ከባለሥልጣኑ ጋር ቀጥተኛ ግኑኝነት እንዳለው ጠቅሰው፤ በየጊዜው መረጃ እንደሚለዋወጡም ተናግረዋል። ይህን መሠረት በማድረግ ተቋሙ ጥናቶችን በመሥራት፣ ፕሮቶኮሎችን በማዘጋጀት፣ አሠራሮችን በማስተካከል፤ በአውሮፓ ህብረት የተቀመጡ መስፈርቶችን ለማሟላት በሚቻል መልኩ እየሠራ ይገኛል ብለዋል ።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም