
አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ በ2018 ዓ.ም ካሜሩን ላይ በሚካሄደው 14ኛው የዓለም ንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ትሆናለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ::
ሚኒስትሩ ካሣሁን (ዶ/ር) የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድርን አስመልክተው ለብዙኃን መገናኛ እንደገለጹት፤ ድርድሩ በሰጥቶ መቀበል መርሕ፣ የሀገርን ጥቅምና ሀገራዊ ፍላጎትን ባስጠበቀ መልኩ የተከናወነ ነው:: ኢትዮጵያ ባካሄደችው 5ኛውን የዓለም ንግድ ድርጅት የሥራ ቡድን ስብሰባ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል መሆን እንደምትችል ተጨባጭ ተስፋ በመያዝ በስኬት ተጠናቋል ብለዋል::
በተለያዩ የድርድር ነጥቦች ዙሪያ ከ110 በላይ ጥያቄዎችን በመቀበል ምላሽ መሰጠቱን፣ በጽሑፍ ምላሽ ለሚሰጠውም ተዘጋጅቶ እንደሚላክ ካሣሁን (ዶ/ር) አመልክተው፤ ኢትዮጵያ በስብሰባው ላይ ስኬታማ ተሳትፎ ማድረጓን ተናግረዋል::
በድርድር ሂደቱ ብዙ ተስፋ ሰጭ ነገሮች መገኘታቸውን፣ ከ19 ሀገራት እና ከዓለም ባንክም ድጋፍ ማግኘቷም ገልጸው፤ የድርድር ሂደቱ የሚመራበት ግልጽ የሆነ የታዳጊ ሀገራት መመሪያ አለ:: እንደግዴታ የተቀመጡ ጉዳዮችም አሉ:: በድርድር ሂደት ሕግ እንድናሻሽል፣ ተጨማሪ ዕድሎች እንድንከፍት ጥያቄዎች ይቀርባሉና ግፊትም ይኖራል እንዲህ ዓይነቶቹን በጥበብና በብልሃት የሚመለሱ ናቸው ብለዋል::
እንደርሳቸው ገለጻ፤ ከዓለም የገበያ ትስስር ሥርዓት፤ በተለይም ከባለ ብዙ ወገን የገበያ ሥርዓት ኢትዮጵያ ተገልላ መቆየት የለባትም በሚል የተሠራው ሥራ አበረታች ነው:: ኢትዮጵያ በአባልነት ብትቀላቀል ለራሷ ሳይሆን ለዓለም ንግድ ድርጅት ተጨማሪ ገበያ ትሆናለች የሚል እምነት እና ተስፋ እንደጣሉም ነው የጠቆሙት:: አባል መሆኗ ለኢትዮጵያም የሰፋ ገበያ እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት::
ስድስተኛው እና ሰባተኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ የፊታችን ሐምሌ እና ኅዳር ወር ላይ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል:: ኢትዮጵያ በ2018 ዓ.ም ካሜሩን ላይ በሚካሄደው 14ኛው የዓለም ንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንደምትሆን እንደሚጠበቅም ተናግረዋል::
ኢትዮጵያ ያሳካቻቸው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚክ ማሻሻያዎች በዓለም ንግድ ድርጅት በኩል በበጎ ጎን መታየታቸውንም አንስተው፤ በ2003 ዓ.ም የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የኢትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ በመቀበል በታዛቢነት ዝርዝር ለመካተት መፈቀዱን ተናግረዋል::
የመጀመሪያዎቹን ዓመታትም በታዛቢነት በመቆየት ወደ ድርድር ለመግባት ከተፈቀደበት ጊዜ አንስቶ አራት የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባዎች መካሄዳቸውንና አስታውሰዋል::
ኢትዮጵያ ለዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ጥያቄ ካቀረበች 23 ዓመታት የቆየ ሲሆን፤ ድርጅቱ ከተመሠረተ 30 ዓመታት ያስቆጠረ ነው:: 38 ሀገራትም ተደራድረው የገቡበት እና 166 ሀገራት በአባልነት የያዘ መሆኑን አስረድተዋል::
ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 ሀገራት ለድርጅቱ የአባልነት ጥያቄ አቅርበው ይሁንታን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ስምንት ሀገራት እንዳሉበት ጠቁመዋል::
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም