ለ7ኛው አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል

-441 ሺህ ሄክታር መሬት ለተከላ ቦታ ተለይቷል

አዲስ አበባ፦ በ2017 ዓ.ም የክረምት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚከናወነው 7ኛው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ። ለ2017 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 441 ሺህ ሄክታር መሬት የችግኝ መትከያ ቦታ መለየቱም ታውቋል።

በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ ዐሻራና የተራቆቱ መሬቶች ማገገም ዴስክ ኃላፊ አቶ ጎራው በለጠ የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ተከላ ዝግጅት ሥራዎችን አስመልክተው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2017 ዓ.ም ክረምት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው 7ኛው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል። የታቀደውን ግብ ለማሳካት የዝግጅት ሥራው የሚጀምረው ደግሞ ከዘር ማሰባሰብ ነው። እስካሁንም 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል፡፡

ከእዚህ አኳያ በተያዘው በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለት ሺህ 247 ኩንታል የተለያዩ የችግኝ ዘሮች ማለትም የደን ዛፍ፣ የቀርከሐ እና ለጥምር ግብርና የሚሆኑ (ዘርፈ ብዙ አግሮ ፎረስተሪ) ተሰብስቦ ወደ ችግኝ ጣቢያዎች ገብቶ የችግኝ ማፍላት ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። እስካሁንም 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞችን ማፍላት ወይም ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ ከመጀመሩ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ45 ሺህ የማይልቁ ችግኝ ጣቢያዎች ብቻ እንደነበሩ ዴስክ ኃላፊው አውስተው፤ ልማቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ስድስት ዓመታት የችግኝ ጣቢያዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ አድጓል። አሁን ላይም ችግኞች እየተፈሉ ያሉት ከ120 ሺህ በላይ በሚልቁ የመንግሥት፣ የግል፣ የማኅበራት፣ የግብረ ሠናይ ድርጅቶችና የፕሮጀክቶች ችግኝ ጣቢያዎች ላይ እንደሆነ አስረድተዋል።

በ2017 ዓ.ም ለመትከል የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ችግኞችን ከወዲሁ በስፋት የማፍላት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ዴስክ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ዴስክ ኃላፊው አቶ ጎራው፤ ዘር ከመሰብሰብና ችግኝ ከማፍላት ባሻገር የተፈሉ ችግኞች የት ቦታ ያርፋሉ ወይም ይተከላሉ የሚለው አንዱ ዋነኛው የዝግጅት አካል እንደሆነ ጠቅሰው፤ የተተከሉ ችግኞች ምን ላይ እንዳረፉ፣ የት ቦታ ምን ያህል ችግኞች እንደተተከሉ አውቆ ቁጥጥርና እንክብካቤ ለማድረግ የተከላ ቦታዎች ካርታ እንደሚዘጋጅላቸው አስገንዝበዋል።

በዚህ መሠረት በ2016 ዓ.ም ችግኝ ተከላ ከተካሄደባቸው ቦታዎች ውስጥ 947 ሺህ ሄክታር መሬት ካርታ እንደተዘጋጀለትና ካርታ ከማዘጋጀት አኳያ ባለፈው ዓመት ጠንካራ ሥራ መከናወኑን ዴስክ ኃላፊው አመልክተው፤ በተመሳሳይ ዘንድሮም ይህንን ጥንካሬ በማስቀጠል የተከላ ቦታዎችን ለይቶ በማዘጋጀት ካርታ እየተዘጋጀ ይገኛል። ሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ የመትከያ ቦታዎችን ለይተው ካርታ እያዘጋጁላቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ለ2017 የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት 441 ሺህ ሄክታር መሬት የተከላ ቦታ መለየቱን የሚናገሩት ዴስክ ኃላፊው፤ ከእዚህ ውስጥ 50 በመቶ ወይም 220 ሺህ ሄክታር የተከላ ቦታ ካርታ (በካርታው መሠረት ጂኦ-ሪፈራንስ ይደረግለታል) ተዘጋጅቶለታል ብለዋል።

እርሳቸውም፤ የተከላ ቦታ ከመለየት ባለፈ በተለዩ የተከላ ቦታዎች ላይ በስፋት የተፋሰስ ወይም ሥነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይህም ችግኝ የሚተከልበትን የተራቆተ ቦታ እርጥበት እንዲያዝልና ለምነቱን እንዲጠብቅ ስለሚያደርገው፤ በቦታው የሚተከሉ ችግኞች መጠነ ፅድቀታቸው ከፍተኛ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

አንዳንድ አፈርና ውሃ ጥበቃ አይነቶች ሲከናወኑ ለችግኝ መትከያ የሚሆን ጉድጓዶች ጭምር አብረው እንደሚዘጋጁ ዴስክ ኃላፊው አመላክተው፤ ከወዲሁ በርካታ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ከተፋሰስ ልማቱ ጎን ለጎን እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ በ2011 ዓ.ም ከተጀመረ ጀምሮ የዘንድሮን ሳይጨምር ባለፉት ስድስት ዓመታት በዘርፉ (በችግኝ ማፍላት፣ ችግኝ አፍልቶ በመሸጥ፣ ዘር ሰብስቦ በመሸጥ፣ ችግኞችን በመንከባከብ፣ በለሙ ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በመሥራት ለአብነትም ንብ በማነብ፣ በከብት ማድለብና በመሳሰሉት) አንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዐድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ በ11 ክልሎች በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ወደ 132 ሺህ 800 የኅብረተሰብ ክፍሎች በአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በተመሳሳይ ተጠቃሚ እንደሆኑ ዴስክ ኃላፊው አቶ ጎራው ገልጸዋል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You