
– አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
አዲስ አበባ፡- የካፒታል ገበያ የአገልግሎት ሰጪዎች ቁጥር መጨመር በኢትዮጵያ ጠንካራ የፋይናንስ ምህዳር ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ይፈጥራል ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ።
ሥራ አስፈፃሚው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት አዳዲስ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ወደ ገበያው መምጣት በኢትዮጵያ ውስጥ የበለጠ የአገልግሎት ብዝሃነት ያለው ጠንካራ የካፒታል ገበያ ለመፍጠር ያስችላል። እነዚህ ተቋማት ለህብረተሰቡ ከኢንቨስትመንት ባንክና ከማማከር አገልግሎት ጎን ለጎን የሰነደ ሙዓለንዋይ ግብይቶችን የማስፈጸምና የማከናወን ተግባራትን የሚያከናውኑም ናቸው።
እነዚህ አዳዲስ አገልግሎት ሰጪዎች ለገበያው ጥልቀት እና ቅልጥፍናን የሚጨምሩ ሲሆን ለተሻለ የካፒታል ማሰባሰብ እና የኢንቨስትመንት እድሎችም በር እንደሚከፍቱ ገልጸው፤ በተጨማሪም የኢንቨስተሮችን አመኔታ በማጎልበት፣ የገበያ ፍትሃዊነትን በማሳደግ እና የካፒታል ማሰባሰቢያ መሣሪያዎችን በማዘጋጀት ካፒታል ፈላጊ ተቋማትንም ሆነ ኢንቨስተሮችን በእጅጉ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላሉ ነው ያሉት። የካፒታል ገበያው ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆን የውጭ ባለሀብቶችም ግልፅ ሥርዓት በመፍጠር በሀገር ውስጥ የአክሲዮን ገበያ እንዲሳተፉ የሚያስችል ይሆናል። «የኢንቨስትመንት ባንክ እና የጸጥታ ንግድ ድርጅት ማካተት በስቶክ ልውውጥ፣ በግምጃ ቤት ቢል ወይም ቦንድ ላይ ኢንቨስት ላደረጉ ኩባንያዎች አክሲዮን ለመግዛት እና ለመሸጥ ያግዛል» ብለዋል።
“በተጨማሪም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ካፒታል ለማሰባሰብ ይረዳል” ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ከፍተኛ ተለዋዋጭ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ባንክ ሆኗል።
በተለይም ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዋን ተግባራዊ እያደረገች ባለችበት ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል መመሥረቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። አጠቃላይም አዲሶቹ አገልግሎት ሰጪዎች የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሴክተር ስኬትና ቀጣይነት በማረጋገጥ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አዲስ ፈቃድ የሰጣቸው ድርጅቶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ፣ ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ፣ ኢትዮ-ፊደልቲ ሴኩሪቲስ ፣ ኤችኤስቲ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ሰርቪስስ አማካሪ አገልግሎት እና ኢኩዥን የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ሲሆኑ ፤ ይህም አጠቃላይ ፍቃድ የተሰጣቸውን የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ቁጥር ከአራት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም