ከተመሠረተ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረው የሸገር ከተማ ስፖርት ክለብ በተለያዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ስኬታማ እየሆነ ይገኛል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በአትሌቲክስ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ነባሮቹን ክለቦች እየተፎካከረ የተለያዩ ስኬቶችን ማስመዝገብ የቻለው ሸገር ከተማ አሁን ደግሞ በእግር ኳስ ሌላ ስኬት አስመዝግቧል።
ሸገር ከተማ እግር ኳስ ክለብ እየተገባደደ በሚገኘው የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በሰበሰበው ነጥብ ከወዲሁ በቀጣዩ የ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል።
ከቀናት በፊት 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ባስተናገደው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ሀ” ጨዋታዎች ሸገር ከተማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል። የሀገሪቱ ሁለተኛ የሊግ እርከን ውድድር የሆነው እና ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀሉ ቡድኖች የሚለዩበት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ዘንድሮም በሁለት ምድብ ተከፍሎ በአዲስ አበባ እና በሃዋሳ ከተማ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
ውድድሩ ሊጠናቀቅ የጥቂት ሳምንታት ዕድሜ በቀረው በአሁኑ ወቅት በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ያለው የምድብ “ሀ” ውድድር ላይ ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ ሊጉን ያለ ተቀናቃኝ እየመራ የሚገኘው ሸገር ከተማ አስራ ስምንት ጨዋታ አድርጎ አርባ አምስት ነጥብ በመሰብሰብ የምድቡን መሪነት አጠናክሯል። ከትናንት በስቲያ ከእንጅባራ ከተማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 5-1 ማሸነፉን ተከትሎ በ18 ጨዋታ ነጥቡን 45 በማድረስ ከተከታዩ ቤንች ማጂ ቡና በ13 ነጥቦች ርቆ አራት ጨዋታ እየቀረው ወደ 2018 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል።
በወጣቱ አሠልጣኝ በሽር አብደላ እየተመራ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የመጀመሪያውን ዙር 11 ጨዋታ አድርጎ 29 ነጥቦችን በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ የቻለው መሪው ሸገር ከተማ፣ ሁለተኛውን ዙርም በጠንካራ ጉዞው ቀጥሎ ለሀገሪቱ ትልቅ የውድድር መድረክ በቅቷል። ሸገር ከተማ በቀጣይ ከቀናት በኋላ በኢትዮጵያ ዋንጫ ከባህርዳር ከተማ ጋር የሚገናኝ ይሆናል።
በሌላ በኩል በሌላኛው የከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ሊጠናቀቅ የአምስት ጨዋታዎች ጊዜ ቢቀረውም በቡድኖቹ መካከል ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት መካሄዱን ቀጥሏል። ምድቡን በሦስት ነጥብ ልዩነት የሚመራው ነገሌ አርሲ ጨምሮ ሃላባ ከተማ፣ ደሴ ከተማ እና ንብ በቀሪ ጨዋታዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት ሌላኛውን ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድግ አንድ ቡድን የሚለይ ይሆናል።
የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን አራት ቡድን አውርዶ ሁለት ቡድን በማሳደግ በቀጣይ ዓመት ከአስራ ዘጠኝ ቡድን ቀንሶ በአስራ ስድስት ቡድኖች መካከል እንደሚካሄድ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ የሆነው ጅማ አባ ጅፋር በሀገሪቱ ሦስተኛ እርከን ከሆነው ሊግ አንድ ውድድር መውረዱ እርግጥ ሆኗል። በ2009 ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ጅማ አባ ጅፋር በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያው በነበረው የ2010 የውድድር ዘመን የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል። ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግም እንዲሁ የተሳትፎ ታሪክ የነበረው ክለብ እንደሆነ አይዘነጋም።
ከዚህ ስኬት ማግስት ጀምሮ ከፋይናንስ አስተዳደር ጋር የተያያዙ የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሙት የዘለቀው ጅማ አባ ጅፋር በ2014 የውድደር ዘመን ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱም አይዘነጋም። በ2016 ደግሞ ወደ ሊግ አንድ መውረዱ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ጅማ አባ ጅፋር ዳግም ወደ ሀገሪቱ ውድድር ለመመለስ በኦሮሚያ የክልል ቻምፒዮና ተሳታፊ በመሆን በሚያስመዘግበው ውጤት መሠረት በክልል ክለቦች ቻምፒዮና ላይ ተሳታፊ ለመሆን ተገዷል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም