የሴቶችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማጎልበት

በሀገራችን ለዘመናት ተንሰራፍቶ በኖረው ሴቶችን ለማጀት ወንዶችን ለአደባባይ የሚል የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ ሴቶች መብታቸውን እንዳይጠቀሙ ተደርገው ቆይተዋል። በዚህም ሴቶች ክፉኛ ተጎጂ ቢሆኑም፣ ሀገርና ሕዝብም ተጎድተዋል።

ይህን አመለካከት ለመስበር ባለፉት መንግሥታትም በአሁኑ መንግሥትም ዘርፈ ብዙ ተግባሮች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ። ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ተሳትፏቸው እንዲሁም በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የእኩል ተጠቃሚነት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ የተደነገገበትንም ሁኔታም ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህን ሥራዎች ተከትሎ ሴቶች የመብታቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ሲያደርጉ የኖሩ በኋላ ቀር አመለካከቶች ሙሉ በሙሉ ተወግደዋል ማለት ባያስደፍርም፣ ለውጦች ስለመኖራቸው ግን ይታወቃል። በመንግሥታዊ የአመራር ቦታዎች ላይ ሴቶችን በስፋት የማምጣት ጅምሮች ታይተዋል፤ በኢኮኖሚውም በማህበራዊው መስኮችም ሴቶች የሚያደርጉት ተሳትፎ ጎልቶ እየወጣ ይገኛል።

ይሁንና አሁንም ድረስ የሴቶች የተለያዩ መስኮች ተሳትፎ አሀዝ ከወንዶች ጋር የተስተካከለ በማድረግ በኩል ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር ይታወቃል። በተለይ በኢኮኖሚው መስክ የሚታዩ ችግሮች ሴቷ ከወንዶች እኩል አምራች፣ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዳትሆን ይልቁንም የወንድ ጥገኛ ሆና እንድትቀጥል የሚያደርጉ ናቸው።

ይህን የአንድ ወገን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማጥበብ እና የሁለቱንም ጾታዎች የእኩል ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ በመንግሥትም እንዲሁም በባለድርሻ አካላትም የሚሰጡ የግንዛቤ እና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች አሁንም ቀጥለዋል፤ ሌሎች ለሴቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረዋል።

ሴቶች ጎልተው ካልወጡባቸው የምጣኔ ሀብቱ መስኮች መካከል አንዱ በሆነው የኢንቨስትመንት መስክም እንዲሁ ሴቶችን ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ሰሞኑን ‹‹ሀቢታት ፎር ሂውማኒቲ›› የተሰኘ ድርጅት ‹ሴቶችን በኢንቨስትመንት ማብቃት› በሚል ባዘጋጀው መድረክ ላይም ይሄው ተጠቁሟል። በመድረኩ ከትናንት እስከ ዛሬ ባሉ የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፤ በዚህ ላይ በመመሥረትም ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል። ሴት ኢንቨስተሮች ተሞክሯቸውን አጋርተዋል። የመንግሥት ኃላፊዎችና አጋሮች ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

በውይይቱ ላይ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነው እንዳይወጡ፣ አቅማቸውን እና ችሎታቸውን እንዳይጠቀሙ አልፎ ተርፎም መብታቸውን እንዳይጠይቁ የሆኑበት ምክንያት በጥናታዊ ጽሑፍ ተመላክቷል።

ሴቶች ከቁጥር አኳያ ከወንዶች እኩል በሆኑባት ሀገር ወደ አንድ ወገን ያመዘነ ኢፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማንም የሚጠቅም እንዳይደለ በመድረኩ ተጠቁሞ፣ ሴቶች ወደ ሰፊው ሀብት የማፍራት መንገድ ገብተው ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ለሀገር ልማት መዋል እንደሚገባቸው ተመላክቷል። የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ሆነ ለጥቅማቸው መከበር ዋስትና የሚሆኗቸው የሕግ ማሕቀፎች መኖራቸው ፋይዳው የላቀ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በቀጣይም ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለባቸው ታምኖበታል።

በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሚል በእንግድነት ከቀረቡ እንስቶች መካከል ወይዘሮ ክብረት ዓለማየሁ አንዷ ናቸው። ባለሀብቷ ‹‹አሁን ላለሁበት የኢንቨስትመንት ደረጃ የበቃሁት ለሴት ልጅ ምቹ ባልሆነ ሕግና ማነቆ ውስጥ አልፌ ነው›› ሲሉም አስታውቀዋል። ‹‹ተስፋ ቆርጬ እንድቆም የሚያደርጉ አያሌ የአትችይም፣ የአይሳካልሽም አመለካከቶችን እንዲሁም ማጀት ውስጥ ብቻ እንድቀር የተፈረደብኝን ልማድ ጥሼ ነው ለእዚህ የደርስኩት›› ሲሉ አስገንዝበዋል። አሁንም ቢሆን ሴቶችን ወደፊት የማምጣቱ ነገር ከነችግሩ መሆኑንም አመልክተዋል።

‹‹ሴቶች እድሉ ከተሰጣቸው ማድረግ እና ትልቅ ቦታ መድረስ እንደሚችሉ በራሴ አረጋግጫለሁ። ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ ድረስ በተጽዕኖ ፈጣሪነት ዞሬያለሁ›› ያሉት ወይዘሮ ክብረት፣ ሴቶች ለአላማቸው ታማኝ እና አንድን ነገር ከጥግ ሳያደርሱ የማይቆሙ መሆናቸውን በጽኑ እንደሚያምኑበት አስታውቀዋል።

ሴቶች ከጓዳ ወጥተው ለህልማቸው በአደባባይ እንዲቆሙ እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ እንደ ወንዶች ሰፊ እድል ቢሰጣቸው፣ የተጠቃሚነት መብታቸው ቢጠበቅ፣ /መሬት ቢሰጣቸው፣ ቦታ እንዲሁም የመንቀሳቀሻ ድጋፍ ቢያገኙ/ የተሻለ በመፍጠር ውጤት እንደሚያመጡ ርግጠኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴሩ አቶ ደረጀ አበበ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሴት ባለሀብቶችን እያየን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል። የሕግ ማሕቀፎችን በማስተካከል፣ አመቺ ያልነበሩ አስተሳሰቦችን በማጥራት፣ ሴቶች ሀብት የማፍራት፣ የመወሰን፣ የማስተዳደር መብታቸውን እየተጠቀሙ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሴት ባለሀብቶችን ለማፍራት መንግሥት በልዩ ተጠቃሚነት ፖሊሲ ቀርጾ፣ አቅጣጫ አስቀምጦ በመሥራት ላይ ይገኛል። ለአብነትም በሲዳማ፣ በደቡብ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የበቁ እና ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ሴት ኢንቨስተሮችን የማብቃት ሥራ ተጀምሯል።

በተሻሻሉ ሕጎች፣ ለሴቶች ቅድሚያ በሚሰጥ መመሪያ፣ የሴቶችን የመሬት መብት በሚያረጋግጡ የሕግ ማሕቀፎች እንዲሁም ማበረታቻ ከመስጠት ጀምሮ በወንዶች የበላይነት ስር ያለውን የአንድ ወገን ተጠቃሚነት ወደሚዛናዊነት ለማምጣት አመርቂ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው ያመለከቱት።

አቶ ደረጀ እንዳስታወቁት፤ ለዚህ አዲስ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሀገሪቱ የቆዩ የንግድ ሕጎችን አሻሽላለች። የንግድ ሂደቱንም ዲጅታላይዝድ አድርጋለች። ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን በማውጣትም ለሴት ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታን ፈጥራለች። ሴቶችን በእውቀት፣ በልምድ፣ በሥልጠና በማብቃት የራሳቸውን እድል በራሳቸው እንዲወስኑ ከማድረግ ጀምሮ ለእዚህ በር የሚከፍቱ ስምምነቶችን ከሀገራት ጋርም ተፈራርማለች።

ሀገሪቱ ገና ብዙ ያልተነካ ድንግል ሀብት እንዳላት ጠቅሰው፣ ካላት ለእርሻ ተስማሚ መሬት ሃያ በመቶ ያህሉን ብቻ እየተጠቀመች መሆኗን ገልጸዋል። ይህም ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ቢሳተፉ ምላሽ የሚሰጥ አቅም እንዳለ አመላካች ነው ሲሉም አስገንዝበው፣ በሌሎችም ዘርፎች እንዲሁ አቅም እንዳለ ጠቁመዋል።

በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡት ሁሉም ሕጎች የሴትን ልጅ የእኩል ተጠቃሚነት መብት የሚደነግጉ፣ ሀብት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመወሰን መብት የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የቤተሰብ ሕጉም ወንድና ሴት እኩል ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚገልጽ መሆኑን ተናግረዋል።

በ‹‹ሃቢታት ፎር ሁማኒቲ የስታንድ ፎር ሄር›› ፕሮጀክት ማናጀር ወይዘሮ ናርዶስ እሸቱ፣ ‹‹ያለፈው ጊዜ ለሴቶች አስቻይ እና አበረታች አልነበረም። ከሕግ ባለፈ መሬት ላይ የወረደ የእኩል ተጠቃሚነት እምብዛም ነበር›› ሲሉ ያስታውሳሉ። ‹‹መቶ ሰላሳ ሚሊዮን ከደረሰ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው። የእነዚህ ሴቶች ከኢኮኖሚ መራቅ ለሀገር ከፍተኛ ጉዳት ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል።

‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ሴቶችን በማንቃት፣ የተሻለ መፍጠር እንደሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች እየሠራን እንገኛለን፣ ይሄ መድረክም የዛ አካል ነው› ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ብዙ ነገሮች ተስተካክለው ሴቶች ከራሳቸው እና ከቤተሰባቸው አልፈው ለሀገር እና ለዓለም የሚበቁበት እድል ተከፍቶላቸዋል። በዚህም ብዙ ሴቶች ነባሩን የአትችይም አስተሳሰብ ሰብረው በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ጭምር ጎልተው መታየት ጀምረዋል።

ሴቶች ስለመብታቸው፣ ስለተጠቃሚነታቸው፣ ሀብት የማፍራት እና በኢንቨስትመንቱ የመሳተፍ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው፣ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ መሆናቸውን እንዲያውቁ ድርጅታቸው ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀዋል። ድርጅቱ በሴቶች ጉዳይ ላይ ከሚሠሩ ባለድርሻ አካላት፣ ሴቶች ማህበራት፣ የሲቪል ማህበር ድርጅት ጋር ይህን የማንቃት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሴቶችን ወደ ኢንቨስትመንቱ ለማምጣት የሕግ ማሻሻያ ማድረግ ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል። በቅርቡ ተሻሽሎ የወጣው የመሬት አጠቃቀም ሕግ /ደንብ/ ሴቶችን በማንቃት፣ በማሠራት ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲሳቡ ለማድረግ መንገድ እንደሚከፍት አስታውቀዋል።

ሴቶችን ከማብቃት አኳያ የሌላ ሀገራት ተሞክሮ ምን እንደሚመስል ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዳስታውቁትም፤ በብዙ ሀገራት ሴቶች በተለያዩ መስኮች የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ይታያል፤ ከአፍሪካ ኬንያ የሴቶች የኢንቨስትመንት ማህበራትን በመመስረት ሴቶች በፋይናንስ እንዳይቸገሩ መንግሥት ድጎማ በማድረግ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።

ሥራ አስኪያጅዋ እንዳሉት፤ ብዙዎች እንደሚስማ ሙበት ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ትልቁ ችግር የገንዘብ አለመኖር ነው። እንደ ኬንያ ያሉ ሀገሮች የኢንቨስትመንት ማህበራትን በመጠቀም እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን በመቅረፍ ለብዙዎች የስኬት ዋስትና ይሰጣሉ።

በግብርና ሚኒስቴር ስር ያለው የኢንቨስትመንት ቢሮ የተሻሻሉ ፖሊሲዎች እና አቅጣጫዎችን በመተግበር የሴቶችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው። የፋይናንስ አቅርቦትን በማመቻቸት፣ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁኔታዎችን ምቹ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግም ጀምሯል።

በእንግሊዝም እንደዚሁ የሴቶችን ተሳትፎ የሚጨምሩ፣ ለብዙዎች መማሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከፋይናንስ አቅርቦት በተጨማሪ በቴክኒክ እገዛ፣ በሥልጠና እና በመሰል እንቅስቃሴዎች ሴቶች ላይ እንደሚሠራም አመልክተዋል።

ሀገራችን ለጀመረችው አዲስ የለውጥ ጉዞ ሴቶች ያስፈልጋሉ ሲሉም ጠቅሰው፣ መንግሥት ይሄንን አምኖበት በተለየ መንገድ ልዩ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንቅስቃሴ ላይ ነው ይላሉ። በተለይ በግብርና ሚኒስቴር ስር ያለው የኢንቨስትመንት ቢሮ ለጉዳዩ ትኩረት ከመስጠት ጀምሮ የውጭ ሀገራትን ተሞክሮዎች በመቅሰም በሴቶች ሕይወት ላይ አዲስ ንቅናቄ መጀመሩንም ነው ያመለከቱት።

ለሀገራችን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደ ችግር ከተነሱት መሀል ዋነኛው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ አለመኖር ነው። የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ እጅግ ወሳኝ ከሚባሉት መሀል ነው። አሁን ላይ ሀገራችን የግብርና ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ያስፈልጋታል በሚል አቋም ፖሊሲ እየተቀረጸ ይገኛሉ። በተለይ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ላለው ሥራ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው። ችግሮቿን በመቅረፍ፣ ጥያቄዎቿን በመመለስ፣ የሴቶችን የተጠቃሚነት መብት በማስከበር፣ ከክፍያ አኳያ ሚና እንዳለው ታምኖበታል።

የሀቢታት ፎር ሁማኒቲ ፖሊሲና አድቮኬሲ ማናጀር አቶ አደም አሎ ‹ሴቶች በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ መብታቸውን በማስከበር ተጠቃሚ እና ወሳኝ ሚና ያላቸው እንዲሆኑ ተቀናጅቶ መሥራት ወሳኝነት አለው› ይላሉ። የተቀናጀ ጥረት እኩልነትን በመፍጠር ኃይል እንደሚሆን ጠቅሰው፣ ጥያቄዎች ቶሎ ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በግብርና ሚኒስቴር ስር ባለው የኢንቨስትመንት ሴክተር ቢሮ የተካሄደ ጥናትን ዋቢ አድርገው እንደገለጹትም፤ ሀብት በማፍራት ረገድ የሴቶች ተሳትፎ እጅግ አናሳ የሚባል ነው። አሁን በመንግሥታዊ ተቋማትና እና ባለድርሻ አካላት እንቅስቃሴ ይሄን ውስንነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሠራ ይገኛል። በዚህም በንብረት፣ በውሳኔ ሰጪነት፣ በመሪነት በኩል ሴቷን ከወንድ እኩል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም በሁሉም ረገድ የበቁ እና የነቁ ሴቶች እውን የሚሆኑባት ኢትዮጵያ እየተፈጠረች ነው ሲሉም አመልክተዋል።

በድህነት እና በኋላ ቀርነት የሚታወቁ ሀገራት ለድህነታቸው ዋነኛ ምክንያት አርገው ከሚጠቀሷቸው ውስጥ አንዱ የሴቶች ተሳትፎ ውስንነት እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። ጫናዎችን ሰብረው በመውጣት ከራሳቸውም ከማህበረሰባቸውም አልፈው በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ሴቶች ሲታሰቡ፣ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ደግሞ ምን ያህል ሀገር እንደሚጠቅሙ መገመት አይከብድም።

ሀገር ሴቶችን ትፈልጋለች። ሴቶች ጠንካራ ውሳኔን በማሳለፍና ሁኔታዎችን ቀድሞ በመገንዘብ ረገድ ከወንዶች የተሻለ ተፈጥሮ እንዳላቸው ይገለጻል። በእውነት እና በጽናት ለአላማቸው በመቆምም ይጠቀሳሉ። በብልሀት እና በተሻለ የአፈጻጸም ብቃትም ድንቅ የሚባል ስም ያላቸው ናቸው።

የኢንቨስትመንት ዘርፉ ደግሞ ይሄን የሴቶችን ባሕሪ ይፈልጋል። ሴቶችን በኢንቨስትመንት መስኩ በስፋት ማሳተፍ ፋይዳው ሴቶችን ከመጥቀምም ይሻገራል፤ ለሀገር ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ እድገትም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።

የሴቶችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማጎልበት

ወይዘሮ ናርዶስ እንዳሉት፤ በተሻሻለው ሕገ ደንብ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በአፈርማቲቭ አክሽን ክልሎች ለሴቶች የተለየ ድጋፍ እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመው፣ ከላይ እስከታች ያሉ አመራሮች ይሄንን በኃላፊነት እንዲመሩ መደረጉንም ገልጸዋል።

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You